1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሕግ እና ፍትሕአፍሪቃ

ለምክር ቤት የቀረቡት ሁለት ረቂቅ አዋጆች ጭብጥ

ረቡዕ፣ ሰኔ 5 2016

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት «በወንጀል ተግባር የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረትን ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ» እና «የንብረት ማስመለስ» የተባሉ ሁለት ረቂቅ አዋጆች ትናንት ቀርበውለታል። ምክር ቤቱ እነዚህን ረቂቅ አዋጆች ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች ለዝርዝር እይታ መርቷቸዋል።

https://p.dw.com/p/4gxor
የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዲስ አበባ
የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዲስ አበባምስል Solomon Muche/DW

ለምክር ቤት የቀረቡት ሁለት ረቂቅ አዋጆች ጭብጥ 

በወንጀል ተግባር የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረትን ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ረቂቅ አዋጅ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት «ሽብርተኝነትን እንዲሁም የጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎችን ብዜት በገንዘብ የመርዳት ወንጀል የኢኮኖሚ ደህንነት ሥጋት ብቻ ሳይሆን፤ የፋይናንስ ሥርዓቱን የሚያናጋ ወንጀል በመሆ»" ይህንን ለመከላከል ታሳቢ ተደርጎ የተረቀቀ የተባለው ረቂቅ ላይ መክሯል። የመሰል ወንጀሎችን ምርመራ በተመለከተ ረቂቅ አዋጁ «አስቸኳይ ሁኔታ ባጋጠመ ጊዜ «መርማሪ» ተብሎ የተጠቀሰው አካል የዐቃቤ ሕግ የበላይ ኃላፊ ሲፈቅድ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ የወንጀል ፍሬን ተከታትሎ ለመለየት በባንክ ሒሳቦች እና በሌሎች ተመሳሳይ ሒሳቦች ላይ ክትትል ለማድረግ፣ የኮምፒውተር መረቦችን እና ሰርቨሮችን ለመለየት፣ መገናኛዎችን በክትትል ሥር ለማዋል ወይም ለመጥለፍ ፣ የደብዳቤ ልውውጦችን መጥለፍ እና ለመያዝ» እንዲችል መርማሪ ተብሎ ለተገለፀው አካል ሥልጣን ይሰጣል።

በሰባት ክፍሎች እና በ 55 አንቀጾች የተደራጀው ይህ ረቂቅ አዋጅ «የወንጀል ፍሬ» የሚለውን ሀረግ «በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ከወንጀል ድርጊት የተገኘ ማንኛውም ንብረት» በማለት ትርጉም ይሰጠዋል።

በረቂቅ አዋጁ ክፍል ሦስት «ማንኛውም ሰው ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ ወይም ከኢትዮጵያ ሲወጣ የያዛቸውን ገንዘብ፣ ላምጭው የሚከፈሉ የክፍያ ሰነዶችን፣ የከበሩ ድንጋዮችን ወይም ንብረቶችን ለጉምሩክ ኮሚሽን የማሳወቅ ግዴታ» እንደሚኖርበት ደንግጓል።

ዓለም አቀፍ ትብብርን በሚመለከተው ክፍል ውስጥ ደግሞ «በወንጀል የተገኘ ንብረት ሕጋዊ ማስመሰል እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳት ለዚህ አዋጅ አፈፃፀም አላማ እንደ ፖለቲካ ወንጀል፣ ከፖለቲካ ወንጀል ጋር ግንኙነት እንዳለው ወንጀል ወይም በፖለቲካ ፍላጎት በመገፋፋት እንደተፈፀመ ወንጀል አይቆጠርም» ሲል ደንግጓል።

 

ቅጣትን በሚመለከት ረቂቁ ምን ይላል?

 

ይህንን ወንጀል በፈፀመ ሰው ላይ የሚቀርብ ክስ እና የሚጣል ቅጣት እንዲሁም ንብረት መውረስ «በይርጋ አይታገድም» ሲልም ይደነግጋል። «በወንጀል የተገኘ ንብረት ሕጋዊ ማስመሰል ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘ ሰው የንብረቱ መወረስ እንደተጠበቀ ሆኖ ከ 10 እስከ 15 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እሥራት እና ከ ብር 500 ሺህ በማይበልጥ መቀጭ ይቀጣል፣ ይህንኑ ወንጀል የሚፈጽምን ሰው ለመርዳት «ደመ፣ የደገፈ፣ ያመቻቸ ወይም ያማከረ ከ4 እስከ 10 ዓመት ጽኑ እሥራት ይቀጣል» በሚል ደንግጓል። ቅጣቱ ከ 15 እስከ 25 ዓመት ጽኑ እሥራት ሊከብድ የሚቻባቸው ሁኔታዎችም በረቂቁ ተመላክተዋል።

በጉዳዩ ላይ የጠየቅናቸው ጠበቃ በኃይሉ ሰለሞን «ወንጀልን ከመከላከል አንፃር ተገቢነት ያለው ሕግ ነው» ብለዋል።

የፍትህ ተምሳሌታዊ ምስል
የፍትህ ተምሳሌታዊ ምስልምስል Damien Meyer/AFP/Getty Images

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ 

 

ምክር ቤቱ «የወንጀል ፍሬ የሆኑ ንብረቶችን እና ገንዘቦችን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመያዝ፣ ለማገድ፣ ለመውረስ ወይም ለማስተዳደር የሚያስችል» የተባለለት ሌላ «የንብረት ማስመለስ አዋጅ» ረቂቅምቀርቦለት ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መትሮታል። «ማንም ሰው ከሕገ - ወጥ ድርጊት ማናቸውንም አይነት የኢኮኖሚ ጥቅም እንዳያገኝ ለማድረግ» ያለመ ሆኖ የተዘጋጀ ነው የተባለው ይህ ረቂቅ ሕግ «የኢኮኖሚ ወንጀል በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ በመሆኑ» ወንጀሉን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር መውጣቱ ተነግሯል።

በስምንት ክፍል እና በ 57 አንቀጾች የተዋቀረው ይሄኛው ረቂቅ አዋጅ «በወንጀል ሕጉ መሠረት በጥፋተኝነት ላይ የተመሠረተ የንብረት መውረስ የሚደረግ ቢሆንም በወንጀል ሕጉ መሠረት ተከሰው ንብረታቸው የማይወረስ የሕግ ሰውነት ያላቸው ተቋማት በፈፀሙት ሕገ - ወጥ ድርጊት ጥቅም ካገኙ ወይም ለሌላ ሰው ካስገኙ ወይም በሌላ ሰው ጥቅም ላይ ጉዳት አድርሰው ሲገኙ በጥፋተኝነት ላይ ያልተመሰረተ የንብረት መውረስ ክስ ሊቀርብባቸው የሚችልበት አዲስ ሥርዓት ተዘርግቷል» ይላል።

አንድ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የሕግ ባለሙያ በረቂቅ ሕጎቹ ላይ «ጥርጣሬ» እንዳላቸው እና መንግሥትን የሚቃወሙትን ለመጉዳት ጥቅም ላይ እንዳይውል ሥጋታቸውን ገልፀዋል። ጠበቃ በኃይሉ ሰለሞን ግን የተለየ ሀሳብ አላቸው። 

«አሁን አድቫንስ ያደረገው ምንድን ነው - በቀጥታ ገንዘቡ ከተገኘ የወንጀል ፍሬ ነው፤ ይወረሳል። አሁን ግን የወንጀል ፍሬ የሆነውን ነገር ሕጋዊ አስመስለህ ገበያ ውስጥ ብታሰራጭ እሱ ድረስ ይወረሳል። የወንጀል ፍሬ እንደሆነ እያወቀ ያንን ገንዘብ ያሰራጨውም ሰው ይጠየቃል።»

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ ከመንግሥት እና ሕዝባዊ ድርጅት ሠራተኞች ውጭ ባለ ማንኛውም ሰው ላይ - በግል ዘርፍ ላይም ተጠያቂነት የሚያስከትል ሕግ መሆኑ በግልጽ ተቀምጧል። ሕጉ ከተፈጥሮ ሰው በተጨማሪ የሕግ ሰውነት ባላቸው ድርጅቶች ላይም ተፈፃሚ እንደሚሆንም ተካቷል።

 ሰለሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ