1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለምዕራብ ኦሮሚያ ሰላም የሰላም ጥሪ

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 20 2015

አቶ ድሪቢ በኦሮሚያ ከምን ጊዜውም የከፋ የፀጥታ ሁኔታ በተለይም በምዕራብ ኦሮሚያ መስፋቱ አሳስቦን መግለጫውን አውጥተናልም ነው ያሉት፡፡ “ነገሩ በጣም እየከፋ ነው ያለው፡፡ በምዕራብ ኦሮሚያ በኪረሙ፣ ጃርደጋጃርቴ፣ ጉቲን፣ እዚህ ሜታ ሮቢ አዲስ አበባ አቅራቢያ እንኳ ሰዎች ይገደላሉ ይፈናቀላሉም

https://p.dw.com/p/4LY41
Äthiopien | Binnenvertriebene in Oromia
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

የወላጋዉ ግድያ እንዲቆም የሚደረገዉ ጥሪና ጥያቄ እንደቀጠለ ነዉ

                       
ምዕራብ ኦሮሚያ በተለይም ወለጋን የሚያዉከዉን ግጭትና ግድያን ሰላማዊ መፍትሔ እንዲፈለግለት የሚደረገዉ ጥሪ እንደቀጠለ ነዉ።ከዚሕ ቀደም የተለያዩ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች፣ የኦሮሞ የምክር ቤት እንደራሴዎችና የሐገር ሽማግሌዎች በርካታ ሰላማዊ ሰዎች የተገደሉበት ጥቃት እንዲቆም በተደጋጋሚ ጠይቀዉ ነበር።አሁን ደግሞ አንጋፋዉ የመጫና ቱለማ የልማትና የመረዳጃ ማሕበር ጉዳዩ አፋጣኝ መፍትሔ ያስፈልገዋል ብሏል።ሥዩም ጌቱ ዝርዝር ዘገባ አለዉ
“እኛ ስጋት ያደረብን አሁን አይደለም፡፡ ከትግራይ ጦርነትም አስቀድሞ በምዕራብ ኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና አማራ ክልል ቅማንት ማህበረሰብ አከባቢ ግጭቶች የመስፋፋት አዝማሚያ ሲያሳይ ነው መጮህ የጀመርነው፡፡ በተለይም ሰውን ከሰው የሚለያይ አደገኛ ንግግሮች ይሰራጩ ስለነበር መንግስት መፍትሄ እንዲያበጅለት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ጭምር ደብዳቤ ጽፈን በአጭር እንዲቀጭ ጠይቀናል፡፡ ዛሬ የተመለከትነው ውስብስብ የፀጥታ ችግር እንደሚፈጠር ሰግተን ነው ያንን ያደረግነው፡፡ አሁንም ምናልባት ችግሩ በሰላም እልባት ያገኝ እንደሆነ ብለን ነው ደግመን ለማሳሰብ መግለጫ ያወጣነው፡፡”
በኦሮሚያ በተለይም በምዕራቡ የክልሉ አከባቢዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ የፀጥታ ሁኔታው ሲወሳሰብ እንጂ እልባት ሲያገኝ አላስተዋልንም በማለት የመጫና ቱለማ ልማትና መረዳጃ ማህበር ሰሞኑን መግለጫ ማውጣቱን ተከትሎ የማህበሩ ፕሬዝዳንት አቶ ድሪቢ ደምሴ ለዶይ ቬለ ከሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ ነው፡፡ አቶ ድሪቢ በኦሮሚያ ከምን ጊዜውም የከፋ የፀጥታ ሁኔታ በተለይም በምዕራብ ኦሮሚያ መስፋቱ አሳስቦን መግለጫውን አውጥተናልም ነው ያሉት፡፡ “ነገሩ በጣም እየከፋ ነው ያለው፡፡ በምዕራብ ኦሮሚያ በኪረሙ፣ ጃርደጋጃርቴ፣ ጉቲን፣ እዚህ ሜታ ሮቢ አዲስ አበባ አቅራቢያ እንኳ ሰዎች ይገደላሉ ይፈናቀላሉም፡፡ ሰው የመንግስት ደጋፊ እና የተቃዋሚ ደጋፊ እየተባለ ነው የሚሰቃየው፡፡ ኦሮሞ የለም አማራ ሁሉም ዘመድ ሞተብኝ ብለው ሀዘን ተቀምጠው እያስተዛዘን ነው፡፡ እኛ እንደ መፍትሄም ያቀረብነው መሳሪያ መታጠቅ ያለበት በእዝ ሰንሰለት በህጋዊ መንገድ የተደራጀ የፀጥታ አካል ብቻ ነው እንላለን፡፡ ያ አለመሆኑ ነው አንዱም ችግሩን ያባባሰው” ብለዋል አቶ ድሪቢ፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ የተደረሰው የሰላም ስምምነት የሚደገፍ ነው ያሉት የመጫና ቱለማ ማህበር ፕሬዝዳንቱ በኦሮሚያም ተመሳሳይ እርምጃ መውሰድ ያሻል ባይ ናቸው፡፡ “የትግራዩ ጦርነት ብዙ ህይወት ቀጥፎና ንብረት አውድሞ ከመሸ የመጣ የሰላም ድርድርም ብሆን እሰዮ ያስብላል፡፡ ነገር ግን ችግሩ ያንን ብቻ በመፍታት የሚቆም አይመስልም፡፡ በሌሎችም አከባቢ በተለይም በኦሮሚያ ጫካ ገብቶ የሚዋጋው ኃይል ምን ምክኒያት ብኖረው ነው ብሎ መጠየቅን ይሻል” ብለዋል፡፡ 
ከዚህ ቀደም በኦሮሚያ ውስጥ ላለው የፀጥታ ችግር መንግስት ሸነ ያላቸው እና እራሳቸውን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብለው የሚጠሩትን ታጣቂዎች ለማጥፋት እና በክልሉ ሰላም ለማስፈን መንግስት እቅድ አውጥቶ ውጥኑንም በተደጋጋሚ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ አቶ ድሪቢ ግን ሀቀኛ ድርድር ተደርጎ ፍርዱ ለህዝብ ካልተተወ ያ የሰራ አይመስልም ባይ ናቸው፡፡ “መንግስት በቀና አመለካከት መደራደር ካለበት አካል ጋር ተደራድሮ መፍትሄ ይመጣል የሚል እምነት ነው ያለንም” ብለዋል፡፡
ማህበሩ ጥሪውን ያስተላለፈው ለሁሉም ተፋላሚ ወገን ነው ያሉት የማህበሩ ፕሬዝዳንት አቶ ድሪቢ ደምሴ፤ እንደ አገር ሽማግሌ እና ድርጅትም ኦሮሚያ ውስጥ ላለው የሰላም እጦት እልባት ለማፈላለግ በተደጋጋሚ የተደረው ጥረት ፍሬ አላፈራል ሲሉ አስተያየታቸውን አክለዋል፡፡ “በህጋዊ መንገድ ችግሩን ለመፍታት ይቀለዋል ብለን ያመነው መንግስት እንደመሆኑ በተደጋጋሚ ተመላልሰን ጠይቀናል፡፡ ጫካ አለ ከሚባል አካል ጋር ግን የመገኛኘት እድሉም ህጋዊ መሰረቱም ስለሌለ ያን ማድረግ አልቻልንም” ያሉት አቶ ድሪቢ የሆነ ሆኖ ግን መንግስት መንገዱን በማቃናት የሰው ልጅ ሞት እና ቤት መቃጠልን የመሳሰሉ ውድመቶችን ለማስቆም የሰላም አማራጩን ብመለከት ብለን ለማሳሰብ ነው የወደድነው በማለትም መፍትሄ ያሉትን ሀሳብ አስቀምጠዋል፡፡
የመጫ እና ቱለማ ልማትና መረዳጃ ማህበር በ1956 የተመሰረተ ሲሆን የተለያዩ ውጣ ውረድን በማሳለፍ ለዓመታት ተዘግቶ ቆይቷል፡፡ ማህበሩ ከ2010ሩ መንግስታዊ ለውጥ በኋላ ግን ዳግም በአዲስ አበባ ቢሮ ከፍቶ ወደ እንቅስቃሴ ተመልሷል፡፡
ስለምዕራብ ኦሮሚያ ከዚህ በፊት የተለያዩ በኦሮሚያ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶችም እንደ መጫና ቱለማ ማህበር ሁሉ የሰላም ጥሩን ሲያቀርቡ መክረማቸው ይታወሳል፡፡ በኦሮሚያ ታጥቆ የሚንቀሳቀሰው መንግስት ሸነ ያለው እና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦርም ከዚህ ቀደም የበሰላም እንደራደር ጥያቄን ለመንግስት አቅርቦ ያውቃል፡፡ ጥያቄው የሚቀርብለት መንግስት ግን በኦሮሚያ ውስጥ ላለው ችግር ሰላማዊ እልባት መስጠትን አዳጋች የሚያደርገው የታጣቂዎች ግልጽ የፖለቲካ ርዕይ አለመያዝና በማዕከል የሚመሩ አለመሆናቸው ነው ሲል ማጣጣሉ አይዘነጋም፡፡  

Äthiopien | Binnenvertriebene aus der Oromia Region in Debre Birhan
ምስል North Shewa Zone communication Office
Äthiopien | Wahlen | Oromia

ሥዩም ጌቱ

ነጋሽ መሐመድ

እሸቴ በቀሌ