1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኪነ ጥበብ

ሕገ-ወጥ አዳኞች (ገቢር 2 ከትዕይንት 1 እስከ 4)

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 14 2010

ወንጀል ተፋላሚዎቹ! አዲስ ተከታታይ ድራማ ጽሑፍ በፌስ ቡክ። በፈጣን የሴራ ፍሰት፥ በአጫጭር ትእይንቶች የተገነባው ድራማ በአይነቱ ለየት ያለ ነው። ይኽ የድራማ ጽሑፍ በዶይቸ ቬለ የአማርኛው ክፍል የፌስቡክ ገፅ የሚቀርብ ሲኾን፤ ለሽልማት የሚያበቃ ነው። ስለ ተሳትፎ እና ውድድሩ ፌስቡክ ገጻችን ላይ በዝርዝር ይገኛል።

https://p.dw.com/p/2d5rk
09.2015 Crime Fighters MQ amharisch

ሕገ-ወጥ አዳኞች (ገቢር 2 ትዕይንት 1)

የእንስሳት ሐኪሙ ጳውሎስን ማን ገደለው? መርማሪ ዓለሙ እስካሁን መልስ ያላገኘለት ውስብስብ ጥያቄ። ባልደረባው መርማሪ ከበደ በበኩሉ «ሚስተር ጂ» በሚል ቅጽል የሚታወቀውን አደገኛ ወንጀለኛ መያዝ አልተሳካለትም።  

«እህሣ! ይኼ ውስብስብ የግድያ ወንጀል እምን ደረሰ?»

«ተወኝ ባክህ! ሟች ጳውሎስም፤ ዋነኛ የግድያ ተጠርጣሪዋ ባለቤቱ ሉሲም ገና ከትምህርት ቤት ጀምሮ ጓደኞቼ ናቸው። በዛ ላይ የጳውሎስ እህት ሙና ለአጭር ጊዜ ፍቅረኛዬ ነበረች።»

ሟችም ተጠርጣሪም የመርማሪ ዓለሙ ጓደኞች ቢሆኑም ምርመራውን ያለአድልዎ እንደሚቀጥልበት መርማሪ ከበደ ሙሉ እምቱ ነው።

«ግን እስኪ ስለ እኔ ይብቃ! የአንተ ከምን ደረሰ?»

«ሚስተር ጂ ደኑ ውስጥ እያደነ ነው ተብለን ብንደርስ ጥርሶቻቸው የተነቀሉ ዝኆኖችን ተረፍርፈው አናገኝም! ብቻ  አሁን ከዶክተር ሰናይት ጋር ቀጠሮ አለኝ። ማን ያውቃል፥ ፍንጭ አገኝ ይኾናል።»

***     

ሕገ-ወጥ አዳኞች (ገቢር 2 ትዕይንት 2)

መርማሪ ዓለሙ፦ አብሮ አደግ ጓደኛው ሉሲ እንዲህ ተመሳቅላ አይቷት አያውቅም። አንጀቱን በላችው።

«አብሮ አደጎች ስለሆንን ድምጽሽን አልቀርጸውም። እንድረዳሽ ግን ስለ ጳውሎስ አሟሟት የምታውቂውን ሁሉ ንገሪኝ።»

በዝምታ ትንሰቀሰቃለች።

«እኔ አልገደልኩትም! እባክህ እመነኝ ዓለሙ!»

«ታዲያ የዛን ቀን እኛን ስታዪ ለምን ለማምለጥ ሞከርሽ?»

እንዳቀረቀረች ትንሰቀሰቃለች።

«እሺ ሉሲ በቃ ትንሽ ቆይተን እንቀጥላለን። አሁን እረፍት ውሰጂና እራስሽን ለማረጋጋት ሞክሪ።»

***     

ሕገ-ወጥ አዳኞች (ገቢር 2 ትዕይንት 3)

የዱር እንስሳት ተንከባካቢዋ ዶ/ር ሰናይት ጽ/ቤት ውስጥ። መርማሪ ከበደ በቀጥታ ወደመጣበት ጉዳይ ይገባል።

«ያው እንደሚያውቁት ትልቅ ራስ ምታት የሆነብን ሚስተር ጂ የሚባለው ወንጀለኛ ጉዳይ ነው።»

«አዎን! ስለዛ ዕጸ መሰውር አለው ስለሚባለው ስለሚስተር ጂ እኔም ሰምቻለሁ።»

«ሚስተር ጂን ከነግብረአበሮቹ በድንገት ከበን ለመያዝ ነበር።»

ዶ/ር ሰናይት ሕገ-ወጥ አደንን ለመከላከል መርማሪ ከበደ እና መምሪያው ለሚያደርጉት ከፍተኛ ጥረት አድናቂ ናቸው። የድንገተኛ ከበባው ዕቅድ ግን ሳያስገርማቸው አልቀረም።  

«ያን አደገኛ ወንጀለኛ በድንገተኛ ከበባ ለመያዝ!?»   

«አዎን! ያን ለማድረግ ግን የድርጅታችሁን ሄሊኮፕተር እንድታውሱን ለመጠየቅ ነበር አመጣጤ።»

«ምንም ችግር የለም፤ ግን ይህን መወሰን የሚችለው ቦርዱ ነው። ተነጋግሬ አሳውቅሀለሁ።»

«በጣም አመሰግናለሁ! ሰላም ይዋሉ ዶክተር»

«ሰላም ዋል!»

***   

ሕገ-ወጥ አዳኞች (ገቢር 2 ትዕይንት 4)

ንፋስ የሚያመሳቅላቸው ቅጠሎች ኮሽታ እና የወፎች ጭውጭውታ ጥቅጥቅ ላለው ጫካ ልዩ ድባብ ሰጥቶታል። ሁለት ሕገ-ወጥ አዳኞች መሣሪያቸውን እንደደገኑ ቅጠል ለብሰው ተሸሽገዋል። 

«ያንት ያለህ! ተመልከት እዛ ጋ ምን የሚያካክሉ ዝኆኖች ናቸው? ኧረ! ያ ኮርማውማ…»

«እሽሽሽ! ዝም በል ታስበረግጋቸዋለህ»

ዝኆኖቹ ጥሩምባቸውን እያሰሙ በየአቅጣጫው ሰክ ሰክ ይላሉ።

«ምን አይነቱ ጣጣቴ ነው ባካችሁ! አየህ የሠራኸውን?»

«ይቅርታ!»

«ይቅርታውን ለሚስተር ጂ አቆይለት! ያ ግድንግድ ዝኆን እንዳመለጠን ቢሰማ ምን ሊያደርገን እንደሚችል ይገባሀል? በል ና አሁን ዱካቸውን ተከትለን ስንደርስባቸው በሬዲዮ እናሳውቀዋለን።»

ለመሆኑ ይኼ ሚስተር ጂ ማን ነው? ጳውሎስንስ ማን ገደለው? ሉሲ አለያስ ሌላ ሰው?

***  

የድራማውን ቀጣይ ክፍል ማለትም ገቢር 3  አራት ትእይንቶች ይኽን ሲጫኑ ያገኛሉ።

የድራማውን አራተኛ ክፍል ማለትም ገቢር 4 አራት ትእይንቶች ይኽን ሲጫኑ ያገኛሉ።

የድራማውን የመጀመሪያ ክፍል ማለትም ገቢር 1 አራት ትእይንቶች ይኽን ሲጫኑ ያገኛሉ። 

የድራማውን አምስተኛ ክፍል ማለትም ገቢር 5 አራት ትእይንቶች ይኽን ሲጫኑ ያገኛሉ።

የድራማውን የመጀመሪያ ክፍል ማለትም ገቢር 6 አራት ትእይንቶች ይኽን ሲጫኑ ያገኛሉ።

የድራማውን የመጀመሪያ ክፍል ማለትም ገቢር 7 አራት ትእይንቶች ይኽን ሲጫኑ ያገኛሉ።

የድራማውን ቀጣይ ክፍል ማለትም ገቢር 8 አራት ትእይንቶች ይኽን ሲጫኑ ያገኛሉ።

ጀምስ ሙሃንዶ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ማንተጋፍቶት ስለሺ ሥዩም Mantegaftot Sileshi ዜና አዘጋጅ፤ መርኃ ግብር መሪ፤ የሳምንታዊ ስፖርት አዘጋጅ ነው፥ በአጭር ፊልም የበርካታ ዓለም አቀፍ ተሸላሚው ማንተጋፍቶት የቪዲዮ ዘገባዎችንም ያዘጋጃል።@manti