1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ ጳጉሜ 4 ቀን፣ 2011 ዓ.ም

ሰኞ፣ ጳጉሜን 4 2011

በዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ ኢትዮጵያ ወደ ቀጣዩ ዙር ስታልፍ፤ በአውሮጳ ዋንጫ ማጣሪያ ደግሞ ጀርመን ዛሬ ከባድ ግጥሚያ ይጠብቃታል። የዐርቡን ከባድ ሽንፈት ለመካስ የጀርመን ቡድን ኳስ ይዞ በማጥቃት ላይ መመስረት ይኖርበታል።

https://p.dw.com/p/3PJLG
EM-Qualifikationsspiel | Deutschland v Niederlande
ምስል Getty Images/M. Hitij

ባሕር ዳር ላይ ያለምንም ግብ የተለያየየው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን በመልሱ ግጥሚያ ከሌሶቶ ጋር አቻ ተለያይቶ ለቀጣዩ ዙር ማለፉ ከሳምንቱ ማሳረጊያ ዐበይት የስፖርት ክንውኖች ቀዳሚው ነው። ዋልያዎቹ አሁን ለቀጣዩ ማጣሪያ ከሚሳተፉት 40 ሃገራት አንዱ መኾን ችለዋል። የጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ለአውሮጳ ዋንጫ ማጣሪያ ዛሬ የምድቡ ቀዳሚን ይገጥማል። የዐርብ ዕለቱን ከባድ ሽንፈት ለመካስ የጀርመን ቡድን ኳስ ይዞ በማጥቃት ላይ መመስረት ይኖርበታል። በዶሃ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮን ጀርመንን ወክሎ ለመሮጥ ከተዘጋጀ ትውልደ-ኤርትራዊ ጀርመናዊ ጋር ቃለ-መጠይቅ አድርገናል። ራፋኤል ናዳል ለ19ኛ ጊዜ የዩናይትድ ስቴትስ የሜዳ ቴኒስ ፍጻሜ ባለድል ሲኾን፤ ብርቱዋ አሜሪካዊት ሴሬና ዊሊያምስ በፍጻሜው ለ19 ዓመቷ አዲስ አትሌት እጅ ሰጥታለች። 

Tennis US Open | Frauen Finale Bianca Andreescu und Serena Williams
ምስል AFP/T. A. Clark

ካታር ከሦስት ዓመት በኋላ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2022 በምታዘጋጀው የዓለም ዋንጫ ለመሳተፍ ፍልሚያው ተጧጡፏል። ኢትዮጵያ ሌሶቶን ጥላ ወደቀጣዩ ዙር ስታልፍ ያልተጠበቁ ውጤቶችም ተመዝግበዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ሌሶቶ ውስጥ የመልስ ጨዋታውን አንድ እኩል በመለያየት ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ ችሏል። ከአንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ባሕር ዳር ከተማ ውስጥ በተደረገው የመጀመሪያው ዙር የማጣሪያ ግጥሚያ የኢትዮጵያ ቡድን ግብ ሳይቆጠርበት መውጣቱ ዕድሉን አስፍቶለታል። እናም ከአገር ውጪ ግብ ባስቆጠረ በሚለው ሕግ፦ ምንም እንኳን ጨዋታው አቻ ቢጠናቀቅም የኢትዮጵያ ቡድን ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ ችሏል።

በርካቶችን እጅግ ያስደመመው ግጥሚያ የተከናወነው ባለፈው ሐሙስ ነበር። ለሦስት ዐሥርተ ዓመት በእርስ በእርስ ጦርነት እና አለመረጋጋት ከስፖርቱ ዓለም ርቃ የቆየችው ጎረቤት ሶማሊያ በምሥራቅ እና መካከለኛው አፍሪቃ እግር ኳስ ትልቅ ስፍራ የሚሰጣትን ዚምባብዌን ጉድ አድርጋለች። የዚምባብዌ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን በሶማሊያ ቡድን 1 ለ0 መሸነፉ በርካቶችን አስደንቋል። በፊፋ ደረጃ ዚምባብዌ 112ኛ ላይ ስትገኝ ሶማሊያ ልክ እንደ ኤርትራ ደረጃዋ 202ኛ ነው። እጅግ ያስደመመውም ሶማሊያ በደረጃ የምትርቃት ዚምባብዌን በድንቅ ግብ ማሸነፏ ነው።

EM-Qualifikationsspiel | Deutschland v Niederlande
ምስል Reuters/W. Rattay

የሶማሊያ ቡድን በጸጥታ ችግር የተነሳ ጎረቤት ጅቡቲ ውስጥ ባደረገው ግጥሚያ ብቸናዋን ግብ ያስቆጠረው የመሀል ተመላላሹ አህመድ ዓሊ ብሪታንያ ማንቸስተር ሲቲ ውስጥ የአሽከርካሪዎች አሰልጣኝ ነው። «በጣም ልብ የሚነካ ነው፤ በመላው ዓለም የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ጨዋታውን እንደሚመለከቱት ስታውቅ እጅግ በጣም ልዩ ስሜት ይፈጥራል» ብሏል ብቸኛዋን ግብ ያስቆጠረው አህመድ። ሳይድ ዓሊ በ86ኛው ደቂቃ ላይ አህመድ ኳሷን እንዲያቀብለው በእጁ ምልክት ሲሰጠው በድንቅ ኹኔታ አሻግሮለታል። አህመድም ተረጋግቶ እና አልሞ ኳሷን በጭንቅላቱ በመግጨት ከመረብ አሳርፏታል። ሶማሊያ ባለፈው ሐሙስ በአህመድ ዓሊ ማሃሙድ ባስቆጠረችው ብቸኛ ግብ ሰፊ ዕድል ይዛ ነው ነገ ዚምባብዌን በመልሱ ግጥሚያ የምትፋለመው።

ታንዛንያ እና ቡሩንዲ ትናንት ያደረጉት ጨዋታ 2 እኩል በመጠናቀቁ በተሰጠው የፍጹም ቅጣት ምት መለያ፦ ታንዛኒያ 3 ለ0 አሸንፋለች። ኢኳቶሪያል ጊኒ ደቡብ ሱዳንን 1 ለምንም ስታሸንፍ፤ ሴራሊዮን ላይቤሪያን አንድ ለባዶ ረትታለች። በመጀመሪያው ዙር ላይቤሪያ 3 ለ1 ድል በማድረጓ በድምር ውጤት 3 ለ2 አሸንፋ ወደቀጣዩ ዙር አልፋለች። ጅቡቲ ባለፈው ረቡዕ 2 ለ1 ያሸነፈቻት ኢስዋቲኒን በነገው ዕለት ትገጥማለች፤ ሞዛምቢክ ከሞሪሺየስ እንዲሁም ሶማሊያ ከዚምባብዌ ጋር የመልስ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።   ሞዛምቢክም ሶማሊያም በተመሳሳይ 1 ለ0 ስላሸነፉ ሰፊ ዕድል ይዘው ነው ወደ ሜዳ የሚገቡት። በመጀመሪያው ዙር 2 ለ1 የተሸነፈችው ኤርትራ ነገ ማታ ናሚቢያን ትገጥማለች። ሱዳን ከቻድ፤ ሩዋንዳ ከሲሼልስ፤ ጊኒ ቢሳዎ ከሳዎቶሜና ፕሪንሲፔ፤ ቶጎ ከኮሞሬን፤ አንጎላ ከጋምቢያ፤ እንዲሁም ማላዊ ከቦትስዋና በነገው ዕለት  ይጫወታሉ።

የአውሮጳ ዋንጫ ማጣሪያ

ከማጣሪያ ጨዋታዎች ሳንወጣ የአውሮጳ ዋንጫ ማጣሪያም አውሮጳ ውስጥ እየተከናወነ ይገኛል። ባለፈው ረቡዕ በሜዳው በኔዘርላንድ ከባድ ሽንፈት የገጠመው የጀርመን ቡድን ዛሬ ከምድቡ መሪ ሰሜን አየርላንድ ጋር ይፋለማል። ጀርመን ካለፉት 12 ዓመታት ወዲህ በሜዳዋ እንዲህ ከባድ ሽንፈት ስታስተናግድ የዐርብ ዕለቱ የመጀመሪያው ነው። ከረፍት መልስ አይለው ወደሜዳ የገቡት ኔዘርላንዶች 4 ለ2 ድል ማድረግ ችለዋል።

ጀርመን ለአውሮጳ ዋንጫ ማጣሪያ በሜዳው ሐምቡርግ ውስጥ መሸነፉን በተመለከተ የጀርመን እግር ኳስ የዓመቱ ኮከብ ማዕረግን የተቀዳጀው ማርኮ ሮይስ ለዶይቸ ቬለ አስተያየቱን ሰጥቷል። ኔዘርላንዶች ባሳዩት አቋም ማሸነፋቸው ተገቢ ቢኾንም፤ ቡድኑ በተለይ በተከላካይ መስመር በኩል ድክመት ማሳየቱ ለሽንፈታቸው ሰበብ መኾኑን ተናግሯል። በዛሬው ጨዋታም በዚህም አለ በዚያ ሰሜን አይርላንድን ማሸነፍ እንደሚጠበቅባቸው ገልጧል።  የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ዮኣሒም ሎይቭም በተመሳሳይ ከማሸነፍ ውጪ ምንም አማራጭ እንደሌለ አስረግጠው ተናግረዋል።

EM-Qualifikationsspiel | Deutschland v Niederlande - Joachim Löw
ምስል Getty Images/M. Hitij

«ሰሜን አየርላንዶች የደረጃ ሰንጠረዡ መሪዎች ናቸው። ያም በመኾኑ ብቸኛው ግባችን ጨዋታውን ለማሸነፍ የቻልነውን ኹሉ ማድረግ ነው። በእርግጥ ማስቸገሩ አይቀርም፤ ምክንያቱም ሰሜን አየርላንዶች የሚጫወቱት በሜዳቸው የሰውነት ጥንካሬያቸውን ተጠቅመው ነው፤ እናም  ያን ማድረግ ምንግዜም አስቸጋሪ ነው። ኾኖም ግባችን 3 ነጥብ ማግኘት ነው።»

የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ምናልባትም ዛሬ የአጨዋወት ስልት ለውጥ አድርጎ ኳስን በብዛት በቁጥጥር ስር በማዋል በማጥቃት ላይ የተመሰረተ ጨዋታ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል። ለዚህም ይረዳው ዘንድ በጉዳት ዛሬ በማይሰለፈው ኢካይ ጎንዶዋን ምትክ የ20 ዓመቱ ወጣት ኬይ ሀቨርትስን ሊያሰልፉ ይችላሉ። ኬይ ለሌቨርኩሰን ባለፈው የቡንደስሊጋ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 17 ግቦችን ከመረብ ያሳረፈ በበርካቶች ዘንድ የሚጠበቅ ወጣት ነው። አሰልጣኝ ዮአሂም ሎይቭ ምናልባትም ዛሬ ወደተለመደው የ4-2-3-1 አሰላለፍ ሊመለሱም ይችሉ ይኾናል። «ሰሜን አየርላንዶች በአንድ የመሀል አጥቂ ነው የሚጫወቱት ስለዚህ ሁለት የመሀል ተከላካይ ብቻ ነው የሚያስፈልጉን» ሲሉም ተደምጠዋል ወደ ቀድሞ አሰላለፋቸው ሊመለሱ እንደኾን ሲጠቁሙ። ዛሬ ማታ ከጀርመን እና ሰሜን አየርላንድ በተጨማሪ አምስት ጨዋታዎች ይከናወናሉ።

አትሌቲክስ

የተወለደው አሰብ፤ ኤርትራ ሲኾን በልጅነቱ አዲስ አበባ ከተማ እና ትግራይ ውስጥ ኖሯል። እዚህ ጀርመን ሀገር በስደት መጥቶ መኖር ከጀመረ 7 ዓመታት ተቆጥሯል።  አትሌት አማንአል ጴጥሮስ ይባል። ዘንድሮ ከጀርመን የአትሌቲክስ ቡድን ጋር በዶሃው የዓለም አትሌቲክስ ፉክክር ይሳተፋል። በስልክ አነጋግረነዋል። ወደ ጀርመን ከመምጣቱ በፊትም በተለያዩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ተሳታፊ ነበር፤ በተለይ ደግሞ በእግር ኳስ። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2012 ወደ ጀርመን ሀገር ከመጣ ወዲህ በተለያዩ ውድድሮች ተሳታፊ ኾኗል። በ2015 የጀርመን ዜግነት ከያዘ በኋላ ደግሞ ለጀርመን ቡድን ተሰልፎ በአውሮጳ ሃገራት ውጤት አስመዝግቧል። በዘንድሮው የዶሃ የዓለም አትሌቲክስ እና በቀጣዩ የቶኪዮ ኦሎምፒክ ተፎካካሪ ለመኾን ጠንክሮ በመሥራት ላይ ይገኛል። 

የሜዳ ቴኒስ

US Open Finale Nadal vs Medwedew
ምስል USA TODAY Sports/Robert Deutsch

በዩናይትድ ስቴትስ የሜዳ ቴኒስ የፍጻሜ ግጥሚያ ስፔናዊው ራፋኤል ናዳል ለ19ኛ ጊዜ ባለድል በመኾን፤ የ3.85 ሚሊዮን ዶላር ሽልማቱን ተቀብሏል። ለ4 ሰአታት ከ50 ደቂቃ በዘለቀው ግጥሚያ ራፋኤል ናዳል ያሸነፈው የሩስያው ተፎካካሪው ዳኒል ሜድቬዴቭን ነው። ከባድ ፉክክር የታየበት ግጥሚያ የተጠናቀቀው በ 7-5፤ 6-3፤ 5-7፤ 4-6፤ እና 6-4 ነው። ያለፉትን 12 የፍጻሜ ግጥሚያዎች ከአንዱ በስተቀር በተከታታይ ያሸነፉት ራፋኤል ናዳል፤ ሮጀር ፌዴሬር እና ኖቫክ ጄኮቪች ናቸው። በሴቶች ተመሳሳይ ውድድር የ37 ዓመቷ አሜሪካዊት በ23 ዋና ዋና ግጥሚያዎች ድልን ብትቀዳጅም በፍጻሜው ለ19ዓመቷ ወጣት እጅ ሰጥታለች። ካናዳዊቷ ወጣት ቢያንካ አንድሪስኩ ቅዳሜ ዕለት የመጀመሪያዋ በኾነው የዩናይትድ ስቴትስ የሜዳ ቴኒስ ፍጻሜ 6-3 እና 7-5 ድል አድርጋ በሚሊዮናት ዶላር ተንበሽብሻለች።

ማንተጋፍቶት ስለሺ   

እሸቴ በቀለ

 

 

ማንተጋፍቶት ስለሺ ሥዩም Mantegaftot Sileshi ዜና አዘጋጅ፤ መርኃ ግብር መሪ፤ የሳምንታዊ ስፖርት አዘጋጅ ነው፥ በአጭር ፊልም የበርካታ ዓለም አቀፍ ተሸላሚው ማንተጋፍቶት የቪዲዮ ዘገባዎችንም ያዘጋጃል።@manti