ሶማሊያ ለሞቱት የኬንያ ወታደሮች ስንብት
ሐሙስ፣ ጥር 19 2008የኬንያ መንግሥት የሟቾቹን ቁጥር ባይጠቅስም በፅንፈኛዉ ቡድን ጥቃት ላለፉ ወታደሮቹ ትናንትበብሄራዊ ደረጃ የመጨረሻዉን ስንብት አድርጓል።
ኬንያ በደቡብ ምዕራብ ሶማሊያ በምትገኘዉ ኤል አደ የጦር ሰፈር አሸባብ ባደረሰዉ ጥቃት ለሞቱት ወታደሮቿ የመጨረሻዉን የስንብት እና ጸሎት ሥርዓት ያካሄደችዉ፤ እዚያ የነበረ ቀሪ ወታደራዊ ኃይሏን ወደድንበሯ አቅራቢያ አዛዉራ ካሰፈረች በኋላ ነዉ። ጥቃቱ የደረሰዉ ከሁለት ሳምንታት በፊት ነዉ። የኬንያ ባለስልጣናት እስካሁን ፅንፈኛዉ ቡድን ድንገት በወታደሮቹ ላይ በሰነዘረዉ ጥቃት የሞቱትም ሆነ የተማረኩትን ቁጥር ይፋ አላደጉም። የሀዘን እና ስንብት ሥርዓቱ የተደረገዉ በተጠቀሰዉ ስፍራ ህይወታቸዉን ካጡት አብዛኞቹ ወታደሮች በመጡባት ከናይሮቢ በስተምዕራብ በምትገኘዉ ኤልዶርት ከተማ ነዉ።
ትናንት ከሟቾቹ የአንዳንዶቹ አስከሬን ከሶማሊያ ወደኬንያ ሲገባም የኬንያ ባለስልጣናት «የወደቁ ጀግኖች» በማለት ላሞካሿቸዉ ወታደሮች የመታሰቢያ እና የስንብት ሥርዓት አካሂደዋል። በሥነሥርዓቱ ላይ ፕሬዝደንት ዑሁሩ ኬንያታ ባደረጉት ንግግር አሸባብን ከፍተኛ ዋጋ ለማስከፈል ዝተዋል።
«ይህ እጅግ ፈታኝ ጊዜ መሆኑን ሁላችንም ማመን አለብን። የወደቁት ሰዎች የእኛን ደህንነት ለመጠበቅ ከቤታቸዉ ብዙ ርቀዉ እጅግ በአስቸጋሪ ሁኔታ ዉስጥ ሲያገለግሉ ነበር። እነሱን የገደሉ እነዚያ ፈሪዎች እያንዳንዳቸዉ ከያሉበት ታድነዉ ለፍርድ ይቀርባሉ። የወታደሮቻችን ደም በከንቱ ፈሶ አይቀርም።»
ስነሥርዓቱ ከመጀመሩ በፊትም በሀዘን ለተጎዱት የሟቾቹ ቤተሰቦች የማፅናኛ እና የምክር አገልግሎት ተካሂዷል። ኬንያ በጎርጎሪዮሳዊዉ 2011ዓ,ም ነዉ እስላማዊ ፅንፈኛ ታጣቂዎች ድንበሯን እየተሻገሩ በሀገር ጎብኚዎች ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት ለመከላከል በሚል ወታደሮቿን ወደሶማሊያ ያዘመተችዉ። አሸባብ በወቅቱ ርምጃዋን በመቃወም በኬንያ ግዛቶች ዉስጥ ተጨማሪ ጥቃቶችን ለማድረስ ዝቶ ነበር። ጥቃቱን ለመከላከል ኬንያ ድንበሯ ላይ ግዙፍ ግንብ ለማቆም አቅዳ ነበር። ምንም እንኳን አሸባብ ከዋና ዋናዎቹ የሶማሊያ ከተሞችና መንደሮች ተገፍቶ ቢወጣም ቡድኑ አሁንም በደፈጣ ዉጊያ እና ጥቃቱን በመላ ሀገሪቱ ማድረሱን አላቋረጠም። አሸባብ በተደጋጋሚ የሚያደርሰዉ ጥቃትም የአፍሪቃ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ወታደሮች፤ የሶማሊያ መንግስት ባለስልጣናት እና የዉጭ ዜጎች ላይ ያነጣጠረ ነዉ።
ኬንያ ትናንት በአሸባብ ጥይት ለወደቁ ወታደሮቿ ባካሄደችዉ የመታሰቢያ ሥርዓት ላይ የናይጀሪያ እና ሶማሊያ ፕሩዝደንቶች ተገኝተዋል። ፅንፈኛዉ ቡድን የሚሰነዝረዉን ጥቃት በዉጭ ኃይሎች ድጋፍ የሚከላከለዉ የሶማሊያ መንግሥት ፕሬዝደንት ሀሰን ሸኽ ሞሀሙድ፤ በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ከጎናቸዉ ሆኖ የሚዋደቀዉን የኬንያን የጦር ኃይል በማመስገን ለዚህም ሀገራቸዉ ባለዕዳ መሆኑኗን ተናግረዋል።
«እዚህ ኬንያ ዉስጥም ሆነ እዚያ በሶማሊያ ለምታደርጉት ለዚህ በጎነት ሶማሊያ ሁሌም ባለዕዳ እንደሆነች ትኖራለች። በጋራ የምንዋጋዉ ይህን እኩይ ኃይል የሰብዓዊነት ጠላት ነዉ፤ ድል እናደርጋቸዋለን። ቀድሞ ድል አድርገናቸዉ ነበር፤ በየቀኑም እያሸነፍናቸዉ ነዉ እናም በመጨረሻም በዚህኛዉ የዓለም ክፍል ድል እናደርጋቸዋለን። ሽብርተኝነት ድንበር የለዉም፤ ጎሳ የለዉም እንዲሁም ፍፁም ሃይማኖት የለዉም። አመሰግናለሁ ኬንያ፤ እናም ኬንያ አመሰግናለሁ፤ አመሰግናለሁ ኬንያ።»
ሀገራቸዉ ከተመሳሳይ ሙስሊም ፅንፈኛ ቡድን ቦኮሀራም ታጣቂዎች ጋር የምትዋጋዉ የናይጀሪያ ፕሬዝደንት ቡሀሪም በሰርጎ ገቦች ጥቃት የተጎዱትን ኬንያዉያን ሀዘን ተካፍለዋል። ፕሬዝደንት ቡሀሪ ፅንፈኞችን ድል ለማድረግ ሀገራቸዉ ከኬንያም ሆነ ከሌሎች የአፍሪቃ ሃገራት ጎን እንዲሁም ከዓለም ኅብረተሰብ ጋር በትብብር እንደምትቆም አመልክተዋል።
«እንደሀገር ናይጀሪያም የቦኮሀራምን የከፋ ጥቃት ስትቀበል ቆይታለች። በአፍሪቃ የተለያዩ አካባቢዎች እንዲሁም በመካከለኛዉ ምሥራቅ እና በመላዉ ዓለም አሸባሪዎች ንፁሀን ሲቪሎች እና የፀጥታ ኃይሎች ላይ ስቃይ እና ሀዘን ማድረሳቸዉን ቀጥለዋል። ሁላችንም ወደሽብር በሚያመሩት ባለመቻቻል ባህል፤ ጥላቻ እና ፅንፈኝነት ላይ በጋራ መነሳት ይኖርብናል። ፅንፈኝነት ላይም ጠንካራ አቋም ሊኖረን ይገባል፤ ማንም ቢሆኑ እና የትም ቢገኙ አሸባሪዎችን መዋጋት አለብን።»
ጄምስ ሺማኑይላ/ ሸዋዬ ለገሠ
አርያም ተክሌ