ሶማሊያ፥ የአዲስ መንግሥት ምሥረታ ሒደትና ፈተናዉ
ሰኞ፣ ነሐሴ 28 2004
በታንክ፣ መድፍ ድምድምታ፣ በመትረየስ ጠመንጃ ካካታ፣ በተፋላሚ ሐይላት ጦር ጫጫታ እንደታበጠች፣ አስከሬን፣ ቁስለኛዋን እንዳስቆጠረች ሃያ-አንድ ዘመን ተቀብላ የሸኘዉ ሞቃዲሾ ሃያ አንድ ዓመት የማታዉቀዉን ለማወቅ አንድ ሁለት ማለት ከጀመረች ወር ደፈነች።በዩጋንዳና በብሩንዲ ጦር ታጅበዉ የወደብ ከተማይቱን አንድ መንደር ያደመቁት የሶማሊያ ፖለቲከኞች፣ የጎሳ መሪዎች ሙግት፣ ክርክር፣ የዉጪ ዲፕሎማቶች፣ምክር-ዝክር የቆየዉን የታንክ፣ መድፍ፣ የቦምብ ጥይት መቅሰፍት ቀይሮታል።ክርክር ዉይይቱ ከሽኩቻና ከሥልጣን ሽሚያ አለመፅዳቱ፣ምክር ዝክሩ ብዙ ሰሚ የማጣቱ ሐቅ የሞቃዲሾን የወደፊት ጉዞ በተስፋ ቀቢፀ ተስፋ ማቃረጡ ነዉ ሥጋቱ። የሶማሊያ ሰሞናዊ ፖለቲካ ሒደት መነሻ፣ ዳራዉ ማጣቀሻ፣ የሥጋቱ ሰበብ መድረሻችን ነዉ ላፍታ አብራችሁ ቆዩ።
በዓላማ መርሕ እንደተሳሰረ ወዳጅ ባንድ አብረዉ፣ የጄኔራል መሐመድ ዚያድ ባሬን አምባ ገነናዊ መንግሥትን በጋራ ወግተዉ ያስወገዱት የያኔዎቹ የሶማሊያ ሸማቂ ቡድናት መሪዎች እርስ በርስ ለመቆራቆስ ከጨካኝ ገዢዉ አገዛዝ ያላቀቁት ሕዝባቸዉ ደስታ ተስፋዉን በቅጡ እስኪገልጥ እንኳን አልታገሱም ነበር።
ጥር 1991 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) የፕሬዝዳትነቱን ሥልጣን የያዙት ዓሊ መሕዲ መሐመድ ለሥልጣን ካበቋቸዉ ከእዉቁ ጄኔራል ከመሐመድ ፋራሕ አይዲድ ጋር ሲጋጩ ከኢትዮጵያ ይልቅ አሜሪካን ሙጥኝ ማለቱን፣ ከሳሊም አሕመድ ሳሊም ይበልጥ የቡትሩስ ቡትሩስ ጋሊን ምክር «አሜን» ማለቱን ነበር የመረጡት።
ቱጃሩ ፖለቲከኛ ኢትዮጵያን ርቀዉ አሜሪካን፣ ሳሊም አሕመድ ሳሊምን አግልለዉ ቡትሩስ ቡትሩስ ጋሊን መወዳጁቱን የመረጡት የፖለቲካ ትርፍ ኪሳራዉን በቅጡ አጢነዉ ነዉ ማሰኙ አልቀረም ነበር።
በርግጥም መሕዲ ሐይለኛዉን ጠላታቸዉን አይዲድን አሸንፈዉ የያዙትን ሥልጣን እንደያዙ ለመቀጠል ከደካማይቱ ኢትዮጵያ ይልቅ ከሐያል ሐብታሚቱ አሜሪካ፣ ከደሐዉ የአፍሪቃ ማሕበር ይልቅ፣ ከግዙፉ የዓለም ድርጅት፣ በግብፃዊዉ የድርጅቱ ዋና ፀሐፊ በኩል ከካይሮ፥ በበካይሮ በኩል ከሐብታሞቹ አረቦቹ በሚያገኙት ድጋፍ እርግጠኛ መስለዉ ነበር።
መሕዲ እንደተመኙት ከአሜእካኖች እቅፍ ገብተዉ፣ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በግልፅ፣ ከአረብ ሊግ በስዉር ድጋፉ ሲንቆረቆርላቸዉ፣ ጄኔራል አይዲድ፣ ኢትዮጵያንና አፍሪቃዉያንን ሙጥኝ ከማለት ሌላ ምርጫ አልነበራቸዉም።የቀድሞዉ የኢትጵያ ጠቅላይ ሚንስትር አቶ መለስ ዜናዊ የሶማሊያን ፖለቲካዊ ጉዞ ከሚዘዉሩት የዉጪ መሪዎች «የሾፌሬን ወንበር» የያዙትም ያኔ ነበር።
እንደ ጎረቤት ሐገር መሪ፣ እንደ ኢጋድ፣ እንደ አፍሪቃ ሕብረት ተወካይ በሽምግልናዉም፣ በማሾም-ማሻሩም፣ እንደ አሜሪካኖች ታማኝ፣ እንደ ፀረ-ሽብር ተዋጊ፥ ጦር በማዝመት ማዋጋቱም ከሶማሊያ ፖለቲካ ያልተለዩት አቶ መለስ ዜናዉ ሰሞኑን ሞቃዲሾ ላይ በተያዘዉ ፖለቲካዊ ሒደት ነባር ጠንካራ ተፅዕኗቸዉን ለማሳረፍ አልታደሉም።ሞት ቀደማቸዉ።
የኢትዮጵያ የዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ እንደሚሉት ግን ጠንካራዉ ሰዉ ቢሞቱም የጠንካራ መንግስታቸዉ መርሕ አይለወጥም።
በብሪታንያዉ የኦሪየንታል ጥናት ዩኒቨርስቲ የሶማሊያ ጉዳይ አጥኚ ዶክተር ላዉራ ሐሞንድ በአምባሳደር ዲና ሙፍቲ አስተያየት ይስማማሉ።ይሁንና ዶክተር ሐሞንድ እንደሚሉት የኢትዮጵያ፥ የኬንያ፥ የዩጋንዳ ይሁን የሌሎቹ ወይም የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ጣልቃ ገብነት የሶማሌዎችን ጥርጣሬ የሚያስወገድ፥ በሶማሊያ ዘላቂ ሠላም ለማስፈን ያለመ መሆን አለበት።
«ከጥቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ሞት በሕዋላ ኢትዮጵያ ሥለ ሶማሊያ የተለየ መርሕ ትከተላለች ብዬ አልጠብቅም።የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ሥለ ሶማሊያም ሆነ ሥለመንግሥታዊ አስተዳደር ባጠቃላይ ተመሳሳይ መርሕ ነዉ ያላቸዉ።ሥለዚሕ ኢትዮጵያ ሥለ ሶማሊያ በምትከተለዉ መርሕ ለዉጥ ይኖራል ብዬ አላስብም።ኬንያም ሆነች ሌሎቹም በሶማሊያ ጉዳይ በያዙት መርሕ ይቀጥላሉ ብዬ ነዉ-የማስበዉ።»
በ1991 ማብቂያ የያኔዉ ጊዚያዉ ፕሬዝዳንት ዓሊ መሕዲ የሠሩት ስሕተት፣ የጄኔራል አይዲድ ጦረኝነት፣ የአሜሪካኖች እብሪት፣ የቡትሩስ ቡትሩስ ጋሊ «ጅልነት» ምናልባት የአፍሪቃ ሕብረት በተለይም የኢትዮጵያ ቸልተኝነት ተራዉን ሶማሌ ያለበሳዉ አስፈጀ እንጂ ላንዳቸዉም አልበጀ።
የአሜሪካ፣ የፓኪስታንና እና የሌሎችም ሐገራት ወታደሮችን ደም-አስከሬንን ከሶማሌዎች ደም አስከሬን የቀየጠዉ ጥፋት አይዲድን በወገኖቻቸዉ ዘንድ የታላቅ ጀግነት ክብር አጎናፅፎ ሲያስገድላቸዉ፣ መሕዲን በከሐዲነት አዋርዶ ፖለቲካዊ ሕወታቸዉን ቀበረዉ።ከሁሉም በላይ የሶማሊያን የልቂት በር በረገደዉ።
ከሃያ-ዓመት የእልቂት ፍጅት ጉዞ በሕዋላ ዘንድሮ በሶማሊያ ቋሚ መንግሥት ለመመስረት የተደረገዉና የሚደረገዉ ጥረት ከዉጤት ቢደርስ እንኳን የሚመሠረተዉ ቋሚ መንግሥት ብዙ መንግሥታትንና ድርጅቶችን ያነካካዉን የሶማሊያን ዉስብስብ ፖለቲካዉ ቀዉስ ሙሉ በሙሉ ያስወግዳል ተብሎ አይጠበቅም።
ሒደቱ ግን ዶክተር ሐሞንድ እንደሚሉት የሃያ-አንድ ዓመቱን እልቂት ፍጅት ለማስወገድ ትንሽ ግን ጥሩ እርምጃ ነዉ።
«ይሕን ሒደት በተገቢዉ አቅጣጫ የሚደረገዉ ጉዞ-ትንሽ እርምጃ እንደሆነ አድርገን ማየት አለብን።ካለፈዉ በተሻለ ሁኔታ ብዙዎችን ያሳተፈ አዲስ ምክር ቤት መሰየሙን፥የምክር ቤት አፈ-ጉባኤም መመረጡን አይተናል።ይሕ እነሱ (ሶማሌዎች) አዲስ አመራር ለመቅረፅ የመፈለጋቸዉን መልዕክት ያስተላልፋል።»
በ2000 ጀቡቲ ላይ የተሰየመዉ የሶማሊያ የጦር አበጋዞች፥ የጎሳ መሪዎችና የምሑራን ጉባኤ የሶማሊያን ሕዝብ የፈጀ፥ ያሰደደ፥ ሶማሊያን ለሁለት፥ ምናልባት ለሰወስት የገመሠ፥ ያወደመዉን ጦርነት ለማስቆም ጥሩ ተስፋ አጭሮ ነበር።
የመሰለዉ-እንደመሰለ ለመቅረት ግን አፍታም አልፈጀ።ጉባኤዉ በሽግግር ፕሬዝዳትነት የመረጣቸዉ ዶክተር አብዲ ቃሲም ሳላድ ሐሰን ገና ከጅቡቲ ሳይወጡ የዓሊ መሕዲ መሐመድን አቋም፥ ሥሕተትም ደገሙት።
ሶማሌዎችን እንድትሸመግል በያኔዉ የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት የተወከለችዉ ኢትዮጵያም ሆነች ሌሎች አፍሪቃዉያን በነበሩበት ነበሩ። ቡትሩስ ቡትሩስ ጋሊን የተኩት ኮፊ አናን፥ ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ ቀዳማዊን የተኩት ቢል ክሊንተን ግን ከየቀደማዎቻቸዉ ብዙ የተለየ ነገር ለማድረግ አልፈቀዱም ወይም አልቻሉም ነበር።
ሳይቆም የተሽመደመደዉን የሳላድን የሽግግር መንግሥት በ2004 የተካዉ የፕሬዝዳት አብዱላሒ የሱፍ አሕመድ የሽግግር መንግሥት ከዓሊ መሕዲም፥ ከሳላድም መንግሥታት ብዙ የተሻለ፥ መስሎ ነበር።ይሁንና ፕሬዝዳት አብዱላሒ የሱፍ፥ ጠቅላይ ሚንስትር ዓሊ ጌዲም ሆኑ አፈ-ጉባኤ ሸሪፍ ሐሰን ከመሕዲ ጥፋት፥ ከነሳላድ ስሕተት ብዙም የተማሩ አልመሰሉም።
ኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥቱን ከያኔዉ የሸሪዓ ፍርድ ቤቶች ሕብረት ጥቃት ለመከላከል በአሜሪካኖች ፍቃድና ይሁንታ ወደ ሶማሊያ ጦር ማዝመቷ ደግሞ ወትሮም ያልተረጋጋችዉን ሶማሊያን ይበልጥ አመሰቃቅሏታል።ዶክተር ሐሞንድ እንደሚሉት ጎረቤት ሐገራት አሁን በሶማሊያ ጉዳይ መሳተፋቸዉ ጥሩ ነዉ። ተሳትፎዉ ግን ያለፈዉን ዓይነት መሆን የለበትም።
«ጎረቤት ሐገራት በሶማሊያ ጉዳይ መሳተፋቸዉ ጥሩ ነዉ።ትልቁ ፈተና የሚሆነዉ ግን አንዳዴ ከልክ ማለፉ ነዉ።ይሕን ካለፈዉ ታሪክ አይተናል።ሶማሌዎች ደግሞ ጎረቤቶቻቸዉን ጭምር ማንም በዉስጥ ጉዳያቸዉ ጣልቃ እንዲገባ አለመፍቀዳቸዉ ነዉ።ሥለዚሕ አብነቱ በተቻለ ፍጥነት በሶማሊያ መንግሥት መመስረትና ሶማሌዎች የራሳቸዉን ፀጥታ እራሳቸዉ እንዲቆጣጠሩ ማድረግ ነዉ።»
በ2009 «ሽግግር» እንደተባለ አምስት-ዓመት ያስቆጠረዉ የፕሬዝዳት አብዱላሒ የሱፍ መስተዳድር፥ ከቀድሞዉ የሸሪዓ ፍርድ ቤቶች ሕብረት ያፈነገጡ ፖለቲከኞች ተቀይጠዉበት ባዲስ መልክ ተደራጀ።አብዱላሒ የሱፍም በሼክ ሸሪፍ ተተኩ። የሸክ ሸሪፍ መንግሥት ከቀዳሚዎቹ መሻሉ ብዙ ተመስክሮለታል።
የዉጪዉ ዓለም ለሽግግር መንግሥቱ የሰጠዉ ድጋፍ መጠናከሩም አላጠያየቀም።ለሶማሊያ ሠላም ግን በሙስና የተዘፈቁት ባለሥልጣናቱም ሆኑም ደጋፊዎቻቸዉ ከተስፋ በስተቀር በርግጥ የተከሩት ነገር የለም።ሶሞኑን ሞቃዲሾ ላይ የተያዘዉ፥ በዶክተር ላዉራ ሐሞንድ አገላለፅ የትንሹ ግን የጥሩዉ አቅጣጫ ሒደት ባለጉዳዮች ካለፈዉ ስሕተት የመማራቸዉ ምልክት፥ ለሶማሊያ፥ ላካባቢዉም ሠላም ሌላ የጥሩ ተስፋ ጭላንጭል መፈንጠቁ አልቀረም።
አምባሳደር ዲናም ተስፋዉን ይጋራሉ።
የሞቃዲሾዉን ጉባኤ እዚያዉ ሞቃዲሾ ሆነዉ የሚከታተሉት የአፍሪቃ ቀንድ የፖለቲካ ጉዳይ አስተንታኝ ፕሮፌሰር ሮናልድ ማርሻል እንደሚሉት ግን የእስካሁኑ ሒደት፥ ጉባኤተኞች ካለፈዉ መማራቸዉን የሚያጠራጥር፥ የተስፋዉን ጭላንጭልም የሚያዳፍን መመስሉ ነዉ ቀቢፀ ተስፋዉ።
«ለኔ ብጤዉ የሶማሊያን ፖለቲካ ለረጅም አመታት ለተከታተለ (ሒደቱ) ትንሽ ተስፋ አስቆራጭ ነዉ-ማለት ይቻላል።ሰዎቹ (ሶማሌዎች) ካለፈዉ ስሕተት ብዙ ለመማር የሚፈልጉ አይመስሉም። ለሁሉም ጉዳይ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብን ማዉገዙ ነዉ የሚቀላቸዉ።እነሱ ራሳቸዉ ግን ያለፈዉ ስሕተት ከመስራትና ከመድገም ሌላ ሕጋዊ ጉዳዮችን፥ ተገቢ ሥርዓቶችን ዘንግተዋቸዋል»
ሕጋዊዉ ደንብ፥ ተገቢዉ ሥርዓት ተከበረም አልተከበረ የወደፊቱን ፕሬዝዳት ለመምረጥ የተያዘዉ ቀጠሮ ለሁለተኛ ጊዜ ተላልፎ በመጪዉ ሳምንት ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።ለፕሬዝዳትነት ለመወዳደር ከተመዘገቡት ወደ ሰላሳ ከሚጠጉ እጩዎች አብዛኞቹ ባለፈዉ ሃያ-አንድ ዓመት ከሶማሊያ ፖለቲካ ያልተለዩ፥ ምናልባትም በእስካሁኑ ስሕተት የሚወቀሱ ናቸዉ።
ከነዚሕ እጩዎች መካካል ደግሞ ያሁኑ የሽግግር ፕሬዝዳት ሼኽ ሸሪፍ ሼክ አሕመድ፥ ጠቅላይ ሚንስትር አብዲ ወሊ መሐመድ ዓሊ፥ የቀድሞዉ ጠቅላይ ሚንስትር መሐመድ አብዱላሒ ፈርማጆ፥ እና ከሁለት ሺሕ አራት እስከ ሁለት ሺሕ ሰባት፥ ከሁለት ሺሕ ዘጠኝ ወዲሕ ደግሞ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የአፈ-ጉባኤነትቱን ሥልጣን ይዘዉ የነበሩት ሸሪፍ ሐሰን ሼክ አደን ይገኙበታል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዘገባ እንደሚያመለክተዉ እነዚሕ ፖለቲከኞች በ2009 እና 2010 ለጠፋዉ በመቶ ሚሊዮን ለሚቆጠር ገንዘብ ተጠያቂዎች ናቸዉ።ግን ደግሞ ከነሱ አንዳቸዉ ለፕሬዝዳትነት መመረጣቸዉ ሌሎቹ በሚንስተርነት መሾማቸዉ የሚቀር አይመስልም።«እና» ይላሉ ፕሮፌሰር ማርሻል የወደፊቱ የሶማሊያ ቋሚ መንግሥት ከእስካሁኑ የተለየ አይሆንም።
«ብዙዎቹ የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ አባላት የተለየ ነገር ይሆናል ብለዉ ለማመን ቢሞክሩም፥ የወደፊቱ ሥርዓት ከእስካሁኑ የሽግግር መንግሥት የተለየ አይሆንም።ምናልባት በአንድና በሁለት ዓመት ዉስጥ ሁኔታዉ ተሻሽሎ የተለየ ነገር እናይ ይሆናል።ለሶማሌዎች የቀረዉ ብቸኛ ተስፋም ይሆዉ ነዉ።»
ሶማሌ ተስፋ አይቀርጥም።ዓለምም።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።
ነጋሽ መሐመድ
ተክሌ የኋላ