1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሶማሊያ፤ የጉባኤ- ጦርነት-የርዳታ-የረሐብ ምድር

ነጋሽ መሐመድ
ሰኞ፣ ግንቦት 7 2009

ጁቡቲ ላይ የተባለ፤ የታቀደ፤ ቃል የተገባዉ ሁሉ በነበር ቀረ።ከጅቡቲዉ እስከ ሐሙሱ ጉባኤ ድረስ ከጅቡቲ-ሁለት እስከ ናይሮቢ፤ ከካይሮ እስከ ብራስልስ፤ ከአዲስ አበባ  እስከ ለንደን 23 ጉባኤዎች ተደርገዋል።ለንደን ዉስጥ ብቻ በ2012 እና በ2013 ሁለት ጉባኤዎች ተደርገዋል።

https://p.dw.com/p/2d0t6
Großbritannien Somalia-Konferenz in London
ምስል Reuters/H. McKay

ሶማሊያ፤ የጉባኤ- ጦርነት-የርዳታ-ረሐብ ምድር

የሶማሊ-ላንድ የቀድሞ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አብዱላሒ መሐመድ ዱዋሌ በ2009 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) መላዋ ሶማሊያ ለሕዝቧ «ትልቅ እስር ቤት ናት» ብለዉ ነበር።ድዋሌ ያሉትን ከማለታቸዉ ከብዙ ዓመታት በፊት የሶማሌዎችን መገዳዳያ «ትልቅ እስር ቤት» ጥሩ ሐገር ለማድረግ ብዙ ተሞክሮ ነበር።ያኔም አልተቋረጠም። ዉጤቱ ግን በርግጥ ባዶ ነዉ።አሁንም የዓለም ፖለቲከኞች ይሰበሰባሉ፤ ቃል ይገባሉ፤ ይዝታሉም።የጨረሻዉ ጉባኤ፤ ቃል፤ ዛቻ ከቀድሞዋ የሶማሊያ ቅኝ ገዢና የበላይ ጠባቂ ርዕሠ-ከተማ ተሰማ።ለንደን። 

                              

የቀድሞዉ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚንስትር ዊንስተን ቸርችል የብሪታንያ የቅኝ ግዛት ጉዳይ  ሚንስትር ደ ኤታ በነበሩበት ዘመን የሶማሊላንድን የወደብ ከተማ በርበራን ጎብኝተዉ ነበር።1907።የወደፊቱ ጠቅላይ ሚንስትር ሶማሊያን ሲጎበኙ ብሪታኒያዎች «እብድ» ሶማሌዎች «ሰይድ» የሚሏቸዉ የሶማሊያ የነፃነት ተዋጊ፤ አዋጊ፤ ገጣሚና መንፈሳዊ መሪ መሐመድ አብድሌ ሐሰን የሚመሩት ሕዝባዊ ሠራዊት በብሪታን ቅኝ ገዢ ጦር ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰበት ወቅት ነበር።

ቸርችል ሶማሊያን ከመጎብኘታቸዉ ከዓመታት በፊት እንደ ወተዳራዊ ዘጋቢ ወደ ዛሬዋ ፓኪስታን ዘምተዉ የሐገራቸዉ ቅኝ ገዢ ጦር የጎሳና የሐይማኖት መሪዎች ካስተባበሩት ከሐገሬዉ ሠራዊት ጋር ያደረገዉን ዉጊያ በቅርብ ተመልክተዉ ነበር።እንደ ወታደር ሱዳን ዘመተዉ ለሱዳን ነፃነት የሚፋለሙ አማፂያንን ወግተዋል።እንደ ሚንስትር ሶማሊያ ሲገቡም  ፓኪስታንም ሱዳኑም የሐገራቸዉን ጦር ሲወጉ ያዩቸዉ ሙስሊሞች ቅኝ ገዢ ጦራቸዉን ሲወጉ አዩ።

Großbritannien Somalia-Konferenz in London
ምስል picture-alliance/Photoshot

የብሪታንያ የኋላ ተወዳጅ ጠቅላይ ሚንስትር ለየቅኝ ተገዢዎቹ ሐገራት መዉደም ተጠያቂዎቹ ቅኝ ገዢዎች ሳይሆኑ እስልምና ነዉ ብለዉ አረፉ።ይህንን እምነታቸዉን ዘ-ሪቨር ዎር ባሉት መፅሐፋቸዉ በሰፊዉ አተተቱት።እንደ ሚንስትር ደኤታ ከጉብኝት መልስ ባቀረቡት ዘገባም ብሪታንያ የሚጠቅሟትን ወደቦች የሚጠብቅ ጦር ብቻ አሥፍራ በተቀሩት አካባቢዎች የሸመቁ ጠላቶችዋን የሚወጋላት ኃይል ከሐገሩ ሕዝብ እንድትመለምል፤ እንድትረዳና እንድታስታጥቅ አበክረዉ አሳሰቡ።የቸርችል ጥቆማ የመሪዎቻቸዉን ድጋፍ አግኝቶ የብሪታንያ ቅኝ አገዛዝ መርሕ አካል በሆነ በአንድ መቶ አስረኛ ዓመቱ ዘንድሮ ብሪታንያ ሥለ ሦማሊያ የመከረዉን ጉባኤ ለሰወስተኛ ጊዜ አስተናገደች።

ባለፈዉ ሳምንት ሐሙስ ለንደን ላይ የመከረዉን ዓለም አቀፍ ጉባኤ የመሩት ጠቅላይ ሚንስትር ቴሬሳ ሜይ የቸርችል ፓርቲ መሪ ናቸዉ።ምናልባት ፖለቲካዊ ሥብዕናቸዉንም አድናቂ ሊሆኑ ይችላሉም ለጉባኤተኞች የነገሩት ግን የሶማሊያ ቀዉስ በጣም እንዳሳሰባቸዉ ነዉ።የረጅም ጊዜ መፍትሔ መሻት ነዉ።

 «አሁን ካለዉ አልፈን ሥለወደፊቱ ማሰብ አለብን።ይሕ ጉባኤ አስፈላጊ የሚሆነዉም ለዚሕ ነዉ።ለወደፊቱ የበለፀገች እና ይበልጥ የተረጋጋች ሶማሊያን መገንባት አለብን።ይሕን ያክል የዓለም ማሕበረሰብ ተወካዮች እዚሕ አዳራሽ መገኘታቸዉም (ሶማሊያን ማረጋጋት) አስፈላጊ እንደሆነ ሥላመኑበት ነዉ።ተገቢዉን እርምጃ እንደምንወስድ ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን ለወደፊቱ የምንገነባዉም የረጅም ጊዜም ትንሳኤ፤ ተስፋ እንደሚሆን ማረጋገጥ አለብን።»

ሰኔ 1991 ጁቡቲ ላይ እንዲሕ እንዳሁኑ በሶማሊያ ጉዳይ ላይ የተነጋገረ ጉባኤ ነበር።ዓላማዉ ለሶማሊያን ማዕከላዊ መንግሥ መመሥረት፤ ሐገሪቱን ማረጋጋት፤ ሕዝቧን መርዳት የሚል ነበር።ልክ እንደ ዘንድሮዉ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እስከ አዉሮጳ ሕብረት፤ ከአፍሪቃ አንድነት ድርጅት እስከ አረብ ሊግ ያሉ ማሕበራት፤ ከአሜሪካ እስከ አፍሪቃ፤ ከአዉሮጳ እስከ መካከለኛዉ የሚገኙ መንግሥታት ዓላማዉን አድንቀዉ ለገቢራዊነቱ ቃል ገብተዉም ነበር።

Somalia Al-Shabaab Kämpfer
ምስል picture alliance/AP Photo/M. Sheikh Nor

የፕሬዝደንት ዓሊ መሕዲ መሐመድ የመልዕክተኞች ቡድን ሞቃዲሾ በገባ ማግሥት ጁቡቲ ላይ የተባለ፤ የታቀደ፤ ቃል የተገባዉ ሁሉ በነበር ቀረ።ከጅቡቲዉ እስከ ሐሙሱ ጉባኤ ድረስ ከጅቡቲ-ሁለት እስከ ናይሮቢ፤ ከካይሮ እስከ ብራስልስ፤ ከአዲስ አበባ  እስከ ለንደን 23 ጉባኤዎች ተደርገዋል።ለንደን ዉስጥ ብቻ በ2012 እና በ2013 ሁለት ጉባኤዎች ተደርገዋል።

የአሜሪካ ጦር፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጦር፤ የኢትዮጵያ ጦር፤ የአፍሪቃ ሕብረት ጦር፤ የአዉሮጳ ባሕር ኃይል፤ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ባሕር ኃይል ሶማሊያና ሶማሊያ ጠረፍ ሰፍሯል።ዉጤቱ የእልቂት-ፍጅት አዙሪት።ዉጤቱ አንዲቷን ሐገር የሶማሊያ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ፤ የሶማሊ ላንድ፤ የፑንት ላንድ፤የጋልሙዱግ፤ የአዛኒያ ወደሚባሉ ትናንሽ ሐገር ወይም መንግሥትነት መከፋፈል ነዉ።

የለንደኑ ጉባኤ ከመጀመሩ በፊት በዋዜማዉ የለንደኑ ወኪላችን ድልነሳ ጌታነሕ የሶማሊያ ፕሬዝደንትን ለማነጋገር ቀጥሮ እንዲያዝለት እዚያዉ ለንደን ወደሚገኘዉ የሶማሊ ሚሽን ወደሚባለዉ ቆንስላ ፅሕፈት ቤት ደዉሎ ነበር።ቸርችል ዘላን ባሉት ሐገር የብሪታንያን ጥቅም ለማስከበር ወደቦችን ማስጠበቅ፤ «ወዳጅ» የሚሏቸዉን  ሶማሌዎች ጠላት ባሏቸዉ ላይ ማዝመት ሲመክሩ ሕዝብን ከመከፋፈል ሌላ አላደረጉም።ከ1991 ጀምሮ የተደረገዉ ጉባኤ፤ ሥብሰባ፤ የጦር ዘመቻ ርዳታ በጥፋት ዉጤት የተጣፋዉም ሶማሌዎች ሠላም ሥለማይፈልጉ አይደለም።ሶማሌዎች የዉጪዉን ድጋፍ ሥለሚጠሉም አይደለም።

Somalia kenianische Soldaten der Afrikanischen Union
ምስል Getty Images/AFP/AU-UN Ist Photo/S. Price

ብዙ ታዛቢዎች እንደሚሉት ሁሉም ጉባኤ ሁሉንም ሶማሌዎች የሚያሳትፍ ባለመሆኑ-አንድ፤ ሁሉም ጉባኤ የየጉባኤዉን መሪዎች ጥቅምና ፍላጎት ለማስከበር ቅድሚያ የሚሰጥ መሆኑ-ሁለት፤ ኃያሉ ዓለም ቃሉን ሥለማያከብር ሰዎት።ሶማሊ ላንድ ከቀድሞ ቅኝ ገዢዋ ዋና ከተማ ለንደን ዉስጥ ቆስላ ከፍታለች።ብሪታንያ ግን ለሶማሊላንድ እዉቅና አልሰጠችም።

አንድ ሰሞን የዩናይትድ ስቴትስ ጦር የሶማሊላንድ  ወደብን በግልፅ ይጠቀም ነበር።የአረብ ሐገራት ከሶማሊላንድ ጋር ከጦር ሰፈር-እስከ ንግድ የሚደርስ ግንኙነት አላቸዉ።ኢትዮጵያ በሶማሊ ላንድ ወደቦች ሸቀጥ ታስገባለች፤ ታስወጣለችም።ዩናይትድ ስቴትስ፤አረቦችም ሆኑ  ኢትዮጵያ ሶማሊ ላንድን እንደ መንግሥት አያዉቁትም።

አብረዋት ለሚሰሯት ሐገር የመንግስትነት እዉቀና ያልሰጡበት ምክንያት በርግጥ ያነጋግራል።ሥለ ሶማሊያ የሚነጋገር ጉባኤ ላይ እንደ ሶማሊ ላንድ የመሳሰሉት ገሚስ ሶማሌ የሠፈረባቸዉ አካባቢዎች ተወካዮች ሳያሳትፉ ለሶማሊያ ሠላም እና መረጋጋት ማምጣት እንዴት ይቻላል? የለንደን ጉባኤተኞች ይቻላል ባይ ናቸዉ።እንደገና ድልነሳ ጌታነሕ።

                       

 የሶማሊያ መንግስት የጦር መሳሪያ ይታጠቃል።የአፍሪቃ ጦር ያቃተዉን አሸባብን ይወጋል።ድል ይገኛል ነዉ-እቅዱ።አሸባብ በርግጥ አሸባሪ ነዉ።አባላቱ ሶማሌዎች፤ ምሽጉ ሶማሊያ መሆኑ ግን ሊዘነጋ አይገባም።ሶማሌን ሠላም ለማድረግ ከሶማሌዎች መሐል የመሐመድ አብዱላሒ መሐመድ መንግሥትን መርጦ-ወዳጅን ማስታጠቅ፤ አሸባብን ነጥሎ በሞቃዲሾ መንግሥት ማስመታት ነዉ።አብነቱ።ከዚሕ በፊት ከ2006 ጀምሮ ተሞክሮ-መክሸፉ፤ እንደገና ተደግሞ እንደገና መጨናገፉ እንጂ ድቀቱ።

ለተከታታይ ዓመታት ጦርነትና ድርቅ ባልተለያት ሐገር የመጀመሪያዉ የለንደን ጉባኤ በ2012 ከመደረጉ ከወራት በፊት ሶማሊያ ዉስጥ ከ260 ሺሕ በላይ ሕዝብ በረሐብ ረግፏል።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተረሽ እንደሚሉት ዘንድሮም ረሐብ እያንዣበበ ነዉ።

Somalia Krise - Hungersnot und Cholera
ምስል picture-alliance/AA/abaca

«ቀዉሱ ከ6,2 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ለምግብ እጥረት አጋልጧል።ከአራት መቶ ሺሕ በላይ ለረሐብ ተጋልጧል።ከ275 ሺሕ የሚበልጡ ሕፃናት ደግሞ ለሕይወታቸዉ በሚያሰጋ ረሐብ እየተሰቃዩ ነዉ።መጪዎቹ ወራት ደግሞ ዝንባ የማይጥልበት ወቅት ነዉ።ተጨማሪ ሕዝብ መራቡ አይቀርም።ዝናብ ከቀረ እሕል አይኖርም።»

የበለፀገዉ ዓለም ዘግይቶም ቢሆን ረሐብተኛዉን ሕዝብ እንደሚረዳ በለንደኑ ጉባኤ ላይ ቃል ገብቷል።ለተራበዉ በርግጥ ጥሩ ተስፋ ነዉ።ከምንም ይሻላልና።ከሶማሌዎች መሐል ታማኝ ሶማሌዎች የተጋበዙበት ጉባኤ ያሳለፈዉ ዉሳኔ የጦርነት-ረሐብ፤ ዑደቱን ማስቀረት መቻሉ ግን ሲበዛ አጠራጣሪ ነዉ።የቀድሞዉ የሶማሊላንድ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አብዱላሂ መሐመድ ዱዋሌ «እኛ ጨቅላ ዴሞክራሲን እየተንከባከብን ነበር» ይላሉ ዓለም ግን ጀርባችንን ይዠልጠናል።ሶማሊያ የጦርነት፤ ረሐብ፤ የእልቂት ስደት ቋት። ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ