1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከደቡብ አፍሪካው የሰላም ንግግር ምን ይጠብቃሉ?

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 19 2015

የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት እና የህወሓት መካከል የሰላም ንግግር ነገ እሁድ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል። በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ከሰላም ንግግሩ አዎንታዊ ውጤት ይጠብቃሉ። የዓረና ትግራይ፣ ዓሲምባ እና ባይቶና አመራሮች ተፋላሚ ኃይሎች ያለ ቅድመ ሁኔታ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ጥሪ አቅርበዋል።

https://p.dw.com/p/4Ipf5
Südafrika Pretoria | Friedensgespräche zu Äthiopien, Tigray
ምስል Phill Magakoe/AFP/Getty Images

ተፋላሚ ኃይሎች ከተኩስ አቁም እንዲደርሱ ፖለቲካ ፓርቲዎቹ ጥሪ አቅርበዋል

የዓረና ትግራይ ለዲሞክራሲ እና ሉዓላዊነት ፓርቲ አመራር አቶ ዓምዶም ገብረስላሴ ጦርነት መፍትሔ ሊሆን እንደማይችል ባለፊት ሁለት ዓመታት በግልፅ ታይቷል፤ ብቸኛ አማራጩ ሰላም ብቻ ነው ይላሉ። አቶ ዓምዶም "በሁለቱ ተዋጊ ሀይሎች በኩል ሲታይ የተደራጀ ወታደራዊ አቋም አለ። የትግራይ ሀይል ከነሙሉ አቅሙ ነው ያለው። የኢትዮጵያ እና ኤርትራ መንግስት ጦሮች ደግሞ በርካታ ሰራዊት እና ትጥቅ ይዞ ነው እየመጣ ያለው። በዚህ አንዱ ያሸንፋል ተብሎ አይገመትም። ጦርነቱ ከቀጠለ የትግራይ ህዝብ ክፉኛ ይጎዳል። በተጓዳኝ ደግሞ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚም እየተራቆተ ይሄዳል" ሲሉ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል። 

ሌላው ያነጋገርናቸው የዓሲምባ ዴሞክራሲያዊ ፖርቲ ሊቀ መንበር አቶ ሐጎስ ወልዱ "ቀድሞንም ሁሉ ነገር በሰላማዊ ንግግር እንዲፈታ ስንጠይቅ ነበር" ያሉ ሲሆን በሁለቱ ተፋላሚ ሀይሎች የተጀመረ 'ድርድር' ፖርቲያቸው እንደሚደግፍ ገልፀዋል።

አቶ ሐጎስ "እኛ ነገሮች በድርድር፣ በሰላማዊ ሂደት ማለቅ አለባቸው ብለን የምናምነው፥ የህወሓትን ዕድሜ ለማራዘም አልያም የብልፅግና ፖርቲ ዕድሜ ለማራዘም አይደለም። ዋናው ዓላማችን የትግራይ ህዝብ ሰቆቃና ስቃይ በአጭር ግዜ እንዲቋጭ ነው" የሚሉ ሲሆን እየተደረገ ካለው የሰላም ንግግር ጦርነቱ እንዲቆም የሚያስችል መፍትሔ እንደሚጠብቁ ተናግረዋል። 

በትግራይ በተቃዋሚነት የሚንቀሳቀሰው የባይቶና ከፍተኛ አመራር አቶ ክንፈገብርኤል ገብረዮሐንስ በበኩላቸው ከተፋላሚ ሀይሎቹ ንግግር "የተኩስ አቁም ውሳኔ ላይ እንዲደረስ እንዲሁም የኤርትራ ጦር እንዲወጣ መግባት ላይ እንዲደርሱ" እንደሚጠብቁ ይገልፃሉ።

"የአንድ ሰው ሕይወት ቢሆን ማትረፍ ከተቻለ ድርድር አስፈላጊ ነው" ያሉት አቶ ክንፈገብርኤል ጦርነቱ በማባባስ፣ በትግራይ የጦር ወንጀሎች በመፈፀም የኤርትራ ጦርን ከሰዋል። ጦርነቱ በቀጠለባት ትግራይ ያለው ህዝብ በደቡብ አፍሪካ ተጀመረ ከተባለው የሰላም ንግግር አወንታዊ ውጤቶች ይጠብቃል።

ሚሊዮን ኃይለስላሴ 
እሸቴ በቀለ