1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ቦረና ዞን ጎሮዶላ ወረዳ የቀጠለው አለመረጋጋት

ሰኞ፣ ጥቅምት 5 2016

ከአዲስ ዞን መዋቅር በኋላ መረጋጋት በራቃት ጎሮዶላ ወረዳ እስካሁን ትምህርት አለመጀመሩ አሳስቦናል ሲሉ ተማሪዎች እና ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ገለጹ፡፡ ምሥራቅ ቦረና በሚል በአዲስ በተዋቀረው የኦሮሚያ 21ኛ ዞን ውስጥ መካተታቸውን የተቃወሙት የጎሮዶላ ነዋሪዎች በአከባቢው የእንቅስቃሴ ገደብም እንደተጠናከረ ነው ይላሉ፡፡

https://p.dw.com/p/4Xabj
ፎቶ ከማኅደር፤ አካባቢዎች የሚያመላክት የኢትዮጵያ ካርታ
በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ቦረና ዞን ጎሮዶላ ወረዳ አለመረጋጋት እንደቀጠለ መሆኑን ነዋሪዎች እየገለጹ ነው። ፎቶ ከማኅደር፤ አካባቢዎች የሚያመላክት የኢትዮጵያ ካርታ

በምስራቅ ጉጂ ጎሮዶላ ወረዳ አለመረጋጋት የማህበራዊ አገልግሎት መስጫዎችን አሰናክሏል

 

ከአዲስ ዞን መዋቅር በኋላ መረጋጋት በራቃት ጎሮዶላ ወረዳ እስካሁን ትምህርት አለመጀመሩ አሳስቦናል ሲሉ ተማሪዎች እና ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ገለጹ፡፡ ምሥራቅ ቦረና በሚል በአዲስ በተዋቀረው የኦሮሚያ 21ኛ ዞን ውስጥ መካተታቸውን የተቃወሙት የጎሮዶላ ነዋሪዎች በአከባቢው የእንቅስቃሴ ገደብም እንደተጠናከረ ነው ይላሉ፡፡ በወረዳው አዲስ የዞን መዋቅር ተቃውሞ ስለገጠመው የመንግስት ተቋማት በሚፈለገው ደረጃ አገልግሎት እየሰጡ አለመሆኑንም ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡

ወጣት ፈልመቱ ቀቤሳ የ18 ዓመት ታዳጊ ስትሆን ነዋሪነቷን በቅርቡ ምስራቅ ቦረና ወደተባለው ዞን የተጠቃለለው የቀድሞ ጉጂ ዞን ወረዳ ጎሮዶላ ሀርቀሎ ከተማ ውስጥ አድርጋለች፡፡ የ11ኛ ክፍል የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ እንደሆነች የምትገልጸው ፈልመቱ እስካሁን ድረስ መረጋጋት ተስኖታል በተባለው በዚህ ወረዳ ምንም አይነት የትምህርት ማስጀመር እንቅስቃሴ ባለመኖሩ ትምህርቷንም ሳትጀምር መቀመጧን ነው የምታስረዳው፡፡በኦሮሚያ በዞን መዋቅር የተነሳው ውዝግብ ቀጥሏል

«አሁን እንደው ቤተሰብ ስራ እያገዝኩ ብቻ ተቀምጫለሁ፡፡ ደመወዝም የለም እንጀራ እየጋገርን ባለው ነገር ቤተሰቦቼን እረዳለሁ፡፡ በዚህ ትምህርት የለም፡፡ የቻለና የተሻለ ገቢ አሊያም ዘመድ ያለው ቤተሰብ ልጆቹን ወደ ሌሎች ሰላማዊ አከባቢዎች በመላክ ያስተምራሉ፡፡ ለኛ ግን እንኳን ልንማር ኑሮም ከብዶናል፡፡»

በንግድ ስራ ተሰማርተው ካሳደጓት እናቷ እና  በመንግስት ስራ ከተሰማሩ አባቷ መወለዷን የምትገልጸው ታዳጊዋ  አለመረጋጋቱ በፈጠረው ችግር ከትምህርቷ ጋር ለመቆራረጥ ከመገደዷም ባሻገር የንግድ ስራም ተቀዛቅዞ የሰራተኞች ደመወዝ በዚህ ተቋርጧልና የምንገፋው ኑሮ ከባድ ነው ስትልም ታስረዳለች፡፡ “የንግድ ሥራ አሁን ተቀዛቅዟል፡፡ አባቴም አሁን ሥራ አቆሟል ደመወዝ የለም፡፡ አስቸጋሪ ህይወት ውስጥ ነን” ትላለች፡፡

ጉጂ ዞን ነዋሪዎች ቅሬታቸውን በስብሰባ ሲያሰሙ
ፎቶ ከማህደር ፤ ከአዲስ ዞን መዋቅር በኋላ መረጋጋት በራቃት ጎሮዶላ ወረዳ እስካሁን ትምህርት አለመጀመሩ አሳስቦናል ሲሉ ተማሪዎች እና ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ገለጹ፡፡ ምስራቅ ቦረና በሚል በአዲስ በተዋቀረው የኦሮሚያ 21ኛ ዞን ውስጥ መካተታቸውን የተቃወሙት የጎሮዶላ ነዋሪዎች በአከባቢው የእንቅስቃሴ ገደብም እንደተጠናከረ ነው ይላሉ፡፡ምስል Private

ታምራት ብሩ በሚል ስማቸው የተዋወቁን ሌላው የጎሮዶላ ወረዳ ነዋሪ ለወራት መረጋጋት ተስኖታል ባሉት ወረዳቸው ህይወት አስቸጋሪውን ገጽ ተላብሳለች ብለውናል፡፡ “በጎሮዶላ ያለው አሁናዊ ሁኔታ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ነን፡፡ መረጋጋት የለም፡፡ ከዚህ የተነሳም ትምህርት እና የጤና አገልግሎት እንኳ በዚህ ወረዳ እየተሰጠ አይደለም፡፡ ይህ ሁሉ ውስብስብ ሁኔታ ውስጥ የገባነው መንግስት ባለፈው ዓመት አዲስ የዞን መዋቅር ብሎ ሳያወያየንና ህዝብ ሳያምንበት አዲሱን መዋቅር ወደ ስራ ማስገባቱን ተከትሎ ነው፡፡ በሌሎች የፀጥታ ችግሮች እና በተራዘመው ድርቅ ፈተና ውስጥ በከረምንበት ሁኔታ ነው ይህ ፈተና በተደራቢነት የመጣብን፡፡ ከዚህ የተነሳ በገጠመን የጸጥታ ችግር በወረዳችን ከ42 ሺኅ በላይ ተማሪ ከትምህርት ገበታ ውጪ ነው ባሁን ወቅት፡፡ ካለው የኑሮ ውድነት ወላጅ ወደ ሻኪሶ እና አዶላ እንኳ በመላክ ልጅ ለማስተማር ፈታኝ ነው፡፡”አዲስ የተቋቋመው በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ቦረና ዞን ያስነሳው ቅሬታ

ከወረዳ አስተዳዳሪው ጀምሮ ቀደም ሲል ወረዳውን ሲያስተዳድሩ የነበሩ አብዛኛው አመራሮች አዲሱን የዞን መዋቅር በመቃወማቸው መታሰራቸውንም ያስረዱን እኚህ አስተያየት ሰጪ፤ አሁን ላይ በወረዳው የጠራ የሲቪል አስተዳደር እንደማይስተዋል አንስተውልናል፡፡ “የቀድሞ አስተዳዳሪዎች ከታሰሩ በኋላ እዚህ ተመድመው የማስተዳደር ስራውን የከወነ የለም፡፡ በአዲሱ መዋቅር የተመደቡም ቢሆን ከህዝብ ይሁኝታ ስለላላገኙ የማስተዳደር ሚናቸውን አልተወጡም፡፡”

ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ ሌላውም የወረዳው ነዋሪ አስተያየታቸውን ቀጠሉ፡፡ “የለው ሁኔታ ያስፈራል ከተማው ዝግ ነው፡፡ አራ ወር በሙሉ ለመንግስት ሰራተኛ ደመወዝ አልተከፈፈለም፡፡ ተማሪዎች ትምህርት ባለመጀመሩ ወላጆቻቸውን እያጨናነቁ ነው” ብለዋል፡፡ አስተያየት ሰጪው ዛሬ የወረዳው ከተማ ከእንቅስቃሴ ውጪ ሆኖ የዋለበትን ምክኒያት ሲያስረዱም ከአዲሱ ዞን መዋቅር የመንግስት ባለስልጣናት ወደ ወረዳው ይመጣሉ የሚባል ጭምጭምታ መሰማቱን ተከትሎ ህዝብ ተቃውሞውን ለመግለጽ ዛሬ የገቢያ ቀን ቢሆንም ከተማውን እንቅስቃሴ አልባ አድርጎት መዋሉን አስረድተዋል፡፡

በጉጂ ዞን በተከሰተ አለመረጋጋት በጉዞ ላይ የነበረ የጭነት ተሽከርካሪ ጥቃት ደርሶበታል
ፎቶ ከማህደር ፤ በወረዳው አዲስ የዞን መዋቅር ተቃውሞ ስለገጠመው የመንግስት ተቋማት በሚፈለገው ደረጃ አገልግሎት እየሰጡ አለመሆኑንም ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ምስል Private

አስተያየት ሰጪዎቹ ወረዳው አዲሱን የዞን መዋቅር በመቃወም መረጋጋት ከተሳነው ወዲህ መሰረታዊ መገልገያዎችን ማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ የወረዳው አስተዳደራዊ መዋቅር ከዞን ጋር መላላቱ የመንግስት ሠራተኞች ደመወዝ እንዲቋረጥ በማድረጉ ጤና ጣቢዎችን ጨምሮ በርካታ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በወረዳው ሥራ ማቋረጣቸው ፈታኝ ሁኔን ፈጥሯልም ባይ ናቸው፡፡የፀጥታ ስጋት ሆኖ የቀጠለው የጉጂ እና ምሥራቅ ቦረና ዞን መዋቅር

ዶይቼ ቬለ የምሥራቅ ቦረና ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ታጁራ ኦዳን ጨምሮ የአከባቢውን ባለስልጣናት በጉዳዩ ላይ ለማነጋገር ያደረገው ተደጋጋሚ ጥረት አልሰመረም፡፡ በወረዳው ትምህርት አለመጀመርን አስመልክቶ ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት እና ስጋት ላይም የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ አመራሮችን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረትም ለዛሬ አልተሳካም፡፡ ከዚህ ቀደም የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ ባለሥልጣናት ምሥራቅ ቦረና የሚል አዲስ የዞን መዋቅር ማደራጀት ያስፈለገው የመልካም አስተዳደርን ለማሳለጥ እና በአካባቢው የጸጥታ ስጋቶችን ለመቆጣጠር እንዲያመች ነው በማለት ውሳኔውን የማይቀለበስ ማለታቸው አይዘነጋም፡፡

ሥዩም ጌቱ

ታምራት ዲንሳ

አዜብ ታደሰ