በኦሮሚያ ክልል የዞን መዋቅር ውዝግብ የትምህርት ዘርፍ መፈተን
ማክሰኞ፣ ጥር 6 2017በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ቦረና በሚል በ2015 ዓ.ም. መጨረሻ በተዋቀረው ዞን ስር መተዳደርን በመቃወም ውዝግብ ተቀስቅሶ በነበረው የጎሮዶላ ወረዳ ውስጥ ትምህርት መቋረጡ ተገለጠ ። ትምህርት ሙሉ በሙሉ ከተቋረጠ አንድ ወር መሆኑን ተማሪዎች እና የተማሪ ወላጆች ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል ። ተቃውሞው ዳግም ሊያገረሽ የቻለው የዘንድሮ 12ኛ ክፍል ተማሪዎች በምስራቅ ቦረና ስም የመጣላቸውን የብሔራዊ ፈተና ቅጽ እንዲሞሉ ከመጠየቃቸው ጋር መያያዙም ተጠቅሷል ። በዞኑ መዋቅር የተነሳ በአካባቢው ካለፉት ሁለት ዓመታት አንስቶ ተቃውሞ ሲስተጋባ ነበር ። የአዲስ አበባ ወኪላችን ሥዩም ጌቱ ዝርዝር ዘገባ አለው ።
በኦሮሚያ ክልል በቅርቡ በአዲስ መልክ በተዋቀረው ምስራቅ ቦረና ዞን ስር እንዲተዳደር በዞኑ ስር የገባው ጎሮዶላ ወረዳ ላለፉት ሁለት ዓመታት ግድም መዋቅሩን በመቃወም የከፋ ውዝግብ ውስጥ ከገቡ የቀድሞ ጉጂ ዞን ወረዳዎች በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡ ከሁሉም የወረዳው መንግስታዊ መዋቅሮች ደግሞ እንደ ትምህርት ዘርፍ የተፈተነ አለመኖሩም በትምህርት ማኅበረሰብ ይገለጻል፡፡
የትምህርት መቋረጡ መነሻ
ተማሪ በዳሳ በወረዳዋ ዋና ከተማ ሀርቀሎ የ12ኛ ክፍል ተማሪ ነው ፡፡ አምናም በዞን መዋቅሩ ተቃውሞ በዚህች ወረዳ የትምህርት አሰጣጡ በመስተጓጎሉ የ11ኛ ክፍል ትምህርቱን ወደ አጎራባች የጉጂ ዞን ወረዳ አዶላ ሄዶ ለመከታተል መገደዱን ያነሳል፡፡ ዘንድሮ ግን በታኅሳስ ወር መጀመሪያ አከባቢ ትምህርት እስከተቋረጠበት ጊዜ የ12ኛ ክፍል ትምህርቱን ወደ ቤተሰቦቹ ተመልሶ በዚሁ ጎሮዶላ ወረዳ ለመከታተል ሲወስን ምክንያቱን በማስረዳት ነው፡፡
«ዘንድሮ እስከ 4ኛ ወር መጨረሻ ብንማርም አሁን ትምህርት ካቋረጥን 1 ወር ሆኖታል ። መጀመሪያ ወደ ትምህርት ቤት ስንመለስ አምና በዞን መዋቅሩ ተቃውሞ ምክንያት ወደ ተለያዩ ወረዳዎች ተበታትነን ስንማር ስለነበር የትምህርት ማስረጃችሁ በጉጂ ዞን ነው የሚሆነው ብለው አሳምነውን ነበር ። አሁን ለ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ፎርም ልንሞላ ስንል ምስራቅ ቦረና ዞን በሚል ነው የምትሞሉ በማለት የመንግስት አካላት በአባገዳዎች ጭምር መስከረም ላይ ያሳመኑንን ነገር ወደገ ጎን ትተው በዚሁ ነው የሚሞላ አሉን ፡፡ እኛ በዚህ አንሞላም እንግዲያውስ መልቀቂያ ስጡን ብንላቸው ከለከሉን ፡፡ እናም ትምህርቱን ከርሞ እንመለስበታለን ብለን ሁላችንም አቋርጠናል» ሲል አስተያየቱን አጋራን ።
ይህ ጉዳይ በወረዳው የሚገኙ ከ50 ሺህ በላይ ተማሪዎች ተረጋግተው እንዳይማሩ ለሁለተኛ ተከታታይ ዓመት ፈትኖታል ያለን ተማሪው፤ በጎሮዶላ እየተስተዋለ ያለው የትምህርት ሙሉ በሙሉ መቋረጥ ወደ ሌሎች የጉጂ ዞን ወረዳዎችም እየተዛመተ ነው ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
የወላጆች ጭንቀት
ይህ የወረዳው የትምህርቱ ዘርፍ ችግር ከተማሪዎችም በላይ ወላጆችን እያስጨነቀ ነው፡፡ ሁለት ልጆቻቸውን በዚሁ ወረዳ ማስተማር ላይ የነበሩት ወላጅ በሰጡን አስተያየት አዲሱ የዞን አወቃቀር ማኅበራዊ ቀውስ በመፍጠር በብርቱ እንደፈተናቸው አስረድተዋል ። «በአዲሱ የዞን አወቃቀር ህዝቡ ቅሬታ አለው፡፡ ትምህርት ለሁለት ዓመታት ቆሞም ነበር፡፡ ግን በድጋሜ ተማሪዎችን፣ የአገር ሽማግሌዎች እና ማኅበረሰቡን በማወያየት ትምህርቱም በጉጂ ዞን ስር እንዲሰጥ ቃል በመግባት የተጀመረ ብሆንም የብሔራዊ ፈተና ፎርም በቦረና ስም ስመጣ ተማሪው በሙሉ ወደ ትምህርት ማቋረጥ ሄዱ» ሲሉ አሰርተያየታቸውን ሰጥተዋል ፡፡
የተማሪው ወላጁ አክለውም ይህ የልጆቻቸው ከትምህርት ቤት ውጪ መሆን እጅጉን ቢያሳስባቸውም «የዞን አወቃቀሩ ማንነትን ያላከበረ ነው» በሚል በመላው ማኅበረሰብ ስለሚታመን መንገስት እልባት እንዲያመጣ እንጠብቃለን ሲሉ አስተያየታቸውን አክለዋል፡፡
ያወዛገበው የዞን መዋቅር ፈተና
አስተያየት ሰጪው ወላጅ ከትምህርትም በሻገር በርካታ መንግስታዊ አገልግሎቱች በዚህች ወረዳ እየተስተጓጎለ ነው ባይ ናቸው፡፡ «አገለግሎት እየተሰጠ ያለው በወረዳ ከተማ ላይ ብቻ ነው ፡፡ ሌሎች ቦታ ላይ የጤና፣ ግብርና እና ፀጥታ አገልግሎቶች ተስተጓጉሏል» ብለዋል፡፡
ሌላም የተማሪ ወላጅ አስተያየታቸውን ቀጠሉ፤ «ወላጅም ፍላጎት የለውም፡፡ የሰው ልጅ በዚህ ምድር ላይ ነጻነቱን ይሻል ፡፡ ሰው እንደ ሰው ጎሳ አለው ፡፡ በራስህ ሳይሆን በእገሌ ስም እየተጠራህ ትተዳደራለህ ስንባል ጉጂ ሆኖ የተፈጠረ ሁሉ ይህን የዞን መዋቅር ተቃውሞ የማይደግፍ የለም» ሲሉ አስተየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ዶይቼ ቬለ ጉዳዩ ላይ የምስራቅ ቦረና ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱራዛቅ ሁሴን እና የጎሮዶላ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አሪቲ ጃርሶን ተጨማሪ መረጃ ለመጠየቅ በእጅ ስልኮቻቸው ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርብም አልተሳካም፡፡
የተባበሩት መንግስታት የህጻናት አድን ድርጅት (UNICEF) በቅርቡ ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ ዘጠኝ ሚሊየን ህጻናት በሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው ውጪ እንደሚገኙ ዐሳውቆ ነበር ፡፡ እንደ ሰብአዊ ድርጅቱ መግለጫ 4.4 ሚሊየን ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ከራቁበት አማራ ክልል ቀጥሎ ኦሮሚያ ክልል በትምህርት ላይ መሆን የነበረባቸው 3.3 ሚሊየን ተማሪዎች በትምህርት ላይ አይደሉም፡፡
ሥዩም ጌቱ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ