የኅብረተሰቡ መተፈንሻ የሆነዉ ኪነ-ጥበብ ለምን ይታፈናል?
ሐሙስ፣ ጥር 9 2016ኅብረተሰቡ ስሜቱን እና ፍላጎቱን የሚገልፅበት መድረክ፤ የኪነጥበብ መድረክ ነዉ። ገዥ መደቦች ደግሞ ሁልግዜም፤ አይፈልጉትም። ነገርግን ብልሆቹ እንደመማርያ ያዩታል። ምክንያቱም ኪነጥበብ የህብረተሰቡ ዉስጣዊ ስሜት ታሽቶ እና ተጨምቆ የሚወጣበት የሚገለጽበት በመሆኑ ነዉ።
የኮሚኒኬሽን ባለሞያ እና ጋዜጠኛ ኦሃድ ቤንዓሚ ከሰጠን አስተያየት የተወሰደን ነበር ያደመጥነዉ። ኪነ-ጥበብም የሰው ልጅ ስሜቱን፣ እምነቱን፣ ስርዓቱና አኗኗሩን የሚገልጽባቸው፤ የማኅበረሰብን እፀጽ ነቅሶ የሚያሳይባቸዉ፤ መሳሪያ መሆኑን በተለይ የዘርፉ ባለሞያዎች ይናገራሉ። ባለፈዉ ሰሞን እያዩ ፈንገስ ... "ቧለቲካ" የተሰኘው የአንድ ሰው ቲያትር መታገዱ የጥበብ አፍቃሪዎችን አስቆጥቷል፤ አሳዝኗልም። ይህ አይነት ነገር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሌሎች መድረኮችንም እየነካ ነዉ ያሉ አስተያየት ሰጭዎች ጥቂቶች አይደሉም። የመንግስት የፀጥታ አካላት፤ ለዓለም ሲኒማ የስራ ኃላፊዎች ባስተላለፉት ትእዛዝ ከጥር 2 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ፤ የእያዩ ፈንገስ "ቧለቲካ" ቴአትርለህዝብ እንዳይታይ ተከልክሏል፤ ቴአትር ቤቱም ይህንኑ የመንግስት የፀጥታ ኃላፊዎች ትእዛዝ ለቴአትሩ አዘጋጆቹ በማሳወቅ ውሉን ማቋረጡን ገልጿል፤ ይላል መረጃዉ። በአንድ ማህበረሰብ ዉስጥ፤ ስልጣን ባላቸዉ እና ስልጣን በሌላቸዉ ማኅበረሰቦች መካከል የማያቋርጥ ፍትግያ መኖሩ ከጥንት ጀምሮ በሰዉ ልጆች ታሪክ የሚታይ ነዉ የሚሉ ምሁራን ኪነ-ጥበብ ሲሞት፤ ማህበረሰብ መበስበስ መጀመሩንም ይገልፃሉ። የኪነ-ጥበብ ፤ የስነ-ጥበብ ብሎም የቅርስ ጥበቃ ባለሞያዎች ጥበብን እንዴት ይገልጹታል? ጥበብ ለማኅበረሰብ ብሎም ላለዉ አስተዳደር የሚሰጠዉ ጠቀሜት እንዴት ይገመገማል ? የኮሚኒኬሽን ባለሞያ እና ጋዜጠኛ ኦሃድ ቤንዓሚ እንደሚለዉ ኪነ-ጥበብ የአንድ ማኅበረሰብ ተስፋና ዉጤቱን የሚገልፅበት መሳርያዉ መሆኑን ይናገራል።
«ኪነጥበብ የአንድ ኅብረተሰብ የአኗኗሩ፤ የፍላጎቱ፤ ቱፊቱን የተስፋዉን እና ስብራቱን የሚገልፅበት የፈጠራ ዉጤት ነዉ። ይሄ ደግሞ የሰዉ ልጅ ኪነ-ህንጻን, በኪነ-ጥበብን፤ ሥነ-ጥበብን ብሎም በግጥም፤ በዜማ ሊሆን ይችላል ይህን ሁሉ ተጠቅሞ፣ ፍላጎቱን ስብራቱን ተስፋዉን ይገልጻል። ኪነ-ጥበብ እራሱን ከዉጭ የሚያይበት፤ ብሎም የሚተነፍስበት መሳርያዉ ነዉ። ኪነጥበብ የትዝብት የመማማርያ፤ የመተራረምያ መድረክ ነዉ።
ኪነጥበብ በአንድ ማኅበረሰብ ባህልን በታሪክ ሁለንተናዊ ግስጋሴ ውስጥ ህብረተሰቡ የፈጠራቸውና ወደ ፊት የሚፈጥራቸውን ቁሳዊና መንፈሳዊ ፋይዳዎችን አካቶ የሚያድግና የሚዳብር የአንድን ማህበረሰብ የትናንት፣ የዛሬና የነገን ማንነት የሚያስተሳስርና የሚያሳይ መስተዋት ነዉ ሲሉ የኪነ-ጥበብ አድናቂዉ አቶ አለባቸዉ ደሳለኝ አክለዋል። እርሶስ ምን ይላሉ? የማኅበረሰብ መስታወት ብሎም መተንፈሻ የተባለዉ ኪነ-ጥበብ ብሎም የተለያዩ ባህልና ቱፊቶች ከመንግሥታት ጫና ምን ያህል ነፃ ናቸዉ? አስተያየታችሁን ጻፉልን።
ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።
አዜብ ታደሰ
ታንራት ዲንሳ