1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

የሰው ልጅ ጨረቃን የረገጠበት 50ኛ መታሰቢያ

ረቡዕ፣ ሐምሌ 10 2011

የሰው ልጅ ጨረቃን የረገጠበት 50ኛ ዓመት በዚህ ሳምንት በተለያዩ ሥነ-ስርዓቶች እየተከበረ ይገኛል። የጨረቃ ጉዞ እና የህዋ ታሪክ የበላይነት ፉክክር ሲነሳ የቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት እና ዩናይትድ ስቴትስ በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ። በህዋ ጉዞ የበላይነትን ለመጨበጥ የነበረውን እሽቅድምድም የቀዝቃዛው ጦርነት ፍጥጫ አንዱ መገለጫም ነበር።

https://p.dw.com/p/3MDaa
Mond Buzz Aldrin vor US-Flagge
ምስል picture-alliance/Photoshot/Neil A. Armstrong

የሰው ልጅ ጨረቃ የረገጠበት 50ኛ መታሰቢያ

ቦታው በአሜሪካ ፍሎሪዳ ግዛት ኬፕ ካናቭራል የሚገኘው የኬኒዲ የህዋ ማዕከል ነው። በማዕከሉ እና አካባቢው በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አፍንጫውን ወደ ሰማይ ያቀናውን “አፖሎ 11” የተሰኘውን መንኮራኮር በጉጉት ይመለከታሉ። ልክ እንደ እነርሱ ሁሉ ሚሊዮኖች በቴሌቪዥን መስኮቶቻቸው ፊት ተኮልኮለው ሁነቱን በቀጥታ ተከታትለዋል። ሦስት ጠፈርተኞችን የያዘው መንኮራኮር ያለምንም እንከን ወደ ህዋ ሲወነጨፍ ጭብጨባው ደመቀ። 

አፖሎ 11 መንኮራኮር ከ102 ሰዓታት እና 45 ደቂቃዎች ጉዞ በኋላ ከጨረቃ ሲያርፍ ለሰው ልጅ እስከዚያን ጊዜ ህልም የነበረው ጨረቃ ላይ የመድረስ እቅድ እውን ሆነ። ከደቂቃዎች በኋላ ከሦስቱ ጠፈርተኞች አንዱ የሆነው ኔል አርምስትሮንግ ጨረቃን በመርገጥ የመጀመሪያው ሰው በመሆን ታሪክ ሰራ። ባልደረባው በዝ አልድሪንም ተከተለው። የዓለምን ታሪክ ከቀየሩ ጉልህ ክስተቶች አንዱ የሆነው የመጀመሪያው የተሳካ የጨረቃ ጉዞ ትላንት 50ኛ ዓመቱን ደፈነ።

Flash-Galerie 40 Jahre Mondlandung
ምስል AP

ኔል አርምስትሮንግ ጨረቃን ከመርገጡ አስቀድሞ የወቅቱ ልዕለ ኃያል የነበሩት ሶቭየት ህብረት እና ዩናይትድ ስቴትስ ህዋን ቀድሞ ለመቆጣጠር ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ፉክክር ውስጥ ቆይተዋል። አሜሪካ በጨረቃ ጉዞ ታሪክ ብትጽፍም ሮኬቶችን እና መንኮራኩሮችን በተደጋጋሚ በማምጠቅ ግን የቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት ቀዳሚነቱን ይዛለች። ሶቭየቶች “ስፑትኒክ” ሲሉ የሰየሙትን ሳተላይት በጎርጎሮሳዊው 1957 ዓ. ም ወደ ህዋ በማምጠቅ አለምን አስደመሙ። 

የእጅ ኳስ መጠን ያላት “ስፑትኒክ” ለ98 ደቂቃዎች በተሳካ ሁኔታ ምድርን መዞር ችላ ነበር። “ስፑትኒክ” ተራ የራዲዮ ማስተላለፊያ እና መቀበያ ብቻ የተገጠመላት ብትሆንም ከዚያ ተከትሎ ለመጣው የቴክኖሎጂ እና ሳይንሳዊ እድገት እንዲሁም ለፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ማሻሻያዎች እንደ መነሻ በማገልገል ከፍተኛ ሚና ተጫውታለች። 
ያኔ የነበረው አስተሳሰብ ህዋን የተቆጣጠረ በምድርም ኃያል መሆን ይችላል የሚል ነበር። የ“ስፑትኒክ” ስኬት አሜሪካ ከህዋ ሊሰነዘርባት ይችላል ተብሎ ለተሰጋው አዲስ አደጋ መከላከያ እንድታበጅ ጫና ፈጥሮባታል።

የመጀመሪያው የጨረቃ ተጓዥ አርምስትሮንግ ወቅቱን እንዲህ መለስ ብለው ያስታውሱታል። “በ1957 ስፑትኒክ የህዋ ዘመን እንደተጀመረ ብታመላክትም ዩናይትድ ስቴትስ ወደ ኋላ ቀርታ ነበር” ይላሉ። አሜሪካ ለ“ስፑትኒክ” ምላሽ ያዘጋጀችው ይበልጥ ውስብስብ የሆነ ሳተላይት መስራትን ነበር። ሳተላይቱንም “ኤክስፕሎረር 1” ስትል ሰየመችው። በጊዜው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የነበሩት ድዋይት ዴቪድ አይዘናወር ከዚህም ተሻግረው የአሜሪካ የጠፈር ምርምር ተቋም (በምህጻሩ ናሳ) እንዲቋቋም አደረጉ። የአሜሪካ ግብ የሰው ልጅን ወደ ህዋ መላክ ነበር።

Sputnik Satellit
ምስል AP

ፕሬዝዳንት አይዘናወር በዚያን ጊዜ ባሰሙት ንግግር ይህንኑ የሀገራቸውን እቅድ በግልጽ አስቀምጠውታል። “ለዘመናዊው ሰው ከተሰጡ ስራዎች መካከል ከሁሉም የላቀ አስቸጋሪውን የተጋፈጥነው። ስርዓተ ፀሐይን ለማሰስ እና ሳይንሳዊ መረጃዎችን ለመሰብሰብ የሚያስችሉ የህዋ ተሽከርካሪዎችን ሰርተን እናመጥቃለን። የሰው ልጅ ወደ ህዋ ለሚበርበት ጊዜ ዝግጅት እናደርጋለን” ብለው ነበር ፕሬዝዳንቱ። 

የአሜሪካ የዘርፉ ባለሙያዎች ይህን ማሳካት እንደሚቻል እርግጠኞች ነበሩ። ቬርንር ፎን ብራውንን የመሰሉ ባለሙያም ከጎናቸው መኖራቸው የልብ ልብ ሰጥቷቸዋል። እኚህ የኤሮስፔስ የምህንድስና ባለሙያ ጀርመን በናዚ አስተዳደር ወቅት በነበረችበት ጊዜ ለሰራቻቸው ሮኬቶች ጉልህ ሚና የተጫወቱ ነበሩ። የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲጠናቀቅ ወደ መቶ የሚጠጉ ምርጥ የሙያ አጋሮቻቸውን አስከትለው ወደ አሜሪካ የተሰደዱ ናቸው።

በአሜሪካ ቆይታቸው በሚሳኤል ግንባታ መርኃ ግብር ስር ሲሰሩ የቆዩት ፎን ብራውን እና ቡድናቸው፤ ሶቭየቶች ሳተላይት ወደ ህዋ ማምጠቃቸውን ተከትሎ ወደ ሳተላይቶች ግንባታ ፊታቸውን አዞሩ። ከሶቭየቶች የተሻሉ ሳተላይቶችን ለመስራት አልመው የተነሱት ባለሙያዎች እንዳሰቡት ተሳካላቸው። ስለ ስኬታቸው በወቅቱ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት ፎን ብራውን “ከሩሲያውያኑ ትልልው ተሽከርካሪዎች ይልቅ በአነስተኛ ተሽከርካሪዎቻችን የበለጠ ሳይንሳዊ ዕውቀት ማግኘት ችለናል” ብለው ነበር።  

ባለሙያዎቹ የተሻለ ነገር እንደሰሩ በኩራት ቢናገሩም መንኮራኮሮቹን እንዲፈትሹ የተመደቡ አሜሪካዊ ጠፈርተኞች ግን የሰውን ልጅ ወደ ህዋ ለመላክ በተያዘው እቅድ እምብዛም ደስተኛ አልነበሩም። እንዲህ አይነት አመለካከት ከነበራቸው ጠፈርተኞች አንዱ ዋልተር ስኪራ ነበሩ። “በሮኬቱ ጫፍ ባለው ክፍል ውስጥ እንዴት ያለችግር መግባት እንደሚቻል እየገለጹ ሊያሳምኑኝ ጣሩ። ‘ይሄማ አይሆንም! በሰርከስ ላይ ከመድፍ ጫፍ የሚቀመጠውን እንስሳ ላኩ። እኛን እርሱን’ አልኳቸው። ‘ችግር አይኖረውም። መጀመሪያ ዝንጅሮዎች እና ቺምፓንዚዎችን ነው የምናስቀምጠው’ ሲሉ ሊያሳምኑኝ ቢሞክሩም ሳስብ የነበረው ‘ከእዚህ መውጣት እፈልጋለሁ’ እያልኩ ነበር። ለነገሩ በጣም ጥሩ ያልሆነ አመለካከት ነው የነበረኝ” ሲሉ በሳቅ ታጅበው ያስረዳሉ። 

Ham, erster Affe im Weltall
ምስል picture-alliance/Everett Collection

ጠፈርተኛው ስኪራ በዚህ አቋማቸው አልጸኑም። ናሳ በጎርጎሮሳዊው 1959 ጠፈርተኞችን ወደ ህዋ ለመላክ መወሰኑን ባስታወቀበት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ለህዝብ ከተዋወቁ ሰባት ጠፈርተኞች አንዱ ሆኑ። ናሳ “ሜርኩሪ” ሲል በሰየመው በዚህ ፕሮጀክት ጠፈርተኞችን ወደ ህዋ መላክ ከመጀመሩበፊት ሶቭየት ህብረት ዓለምን ያስገረመ ሌላ ዜና ይዛ መጣች። ሶቭየት ህብረት አሁንም አሜሪካንን ቀድማ ዩሪ ጋጋሪ የተሰኘውን ጠፈርተኛዋን በጎርጎሮሳዊው 1961 ወደ ህዋ በመላክ ታሪክ ሰራች። ጠፈርተኛው ስኪራ ሂደቱን እና ያኔ የተሰማቸውን ሲያስታውሱ “ዝንጀሮዎች እና ቺምፓንዚዎችን ማምጠቅ የጀመረውን እኛ ነን። ነገር ግን እነርሱ ዩሪ ጋጋሪን ወደ ጠፈር ላኩ። በዚህ በጣሙኑ ደንግጠን ነበር” ይላሉ። 

የሶቭየት እርምጃ ለአሜሪካ ሌላ ፖለቲካዊ መልዕክት ነበር። በወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የነበሩት ጆን ኤፍ ኬኔዲ ከእርሳቸው በፊት በመሪነት ስልጣን ላይ እንደነበሩት አይዘናወር ሁሉ ከሶቪየቶች በቴክኖሎጂ በልጠው ለመገኘት የቆረጡ ነበሩ። ፕሬዝዳንት ኪኔዲ ይህን አቋማቸውን በንግግሮቻቸው አንጸባርቀዋል። “ይህ ሀገር የያዝነው አስርት ዓመት ከመገባደዱ በፊት አንድ ግብ ለማሳካት ቁርጠኛ መሆን ይኖርበታል። ግቡም የሰው ልጅን በጨረቃ ላይ ማሳረፍ እና ወደ ምድር ደህንነቱ እንደተጠበቀ መመለስ ነው” ብለው ነበር። 

ፕሬዝዳንት ኬኒዲ በሌላ ንግግራቸው “በአስር ዓመት ውስጥ ወደ ጨረቃ ለመጓዝ የወሰንነው ቀላል ስለሆነ ሳይሆን ከባድ በመሆኑ ነው” ሲሉ በጉዳዩ ላይ ያላቸውን ቁርጥ አቋም አጽንኦት ሰጥተዋል። ኬኒዲ ይህን ያሉት ሀገራቸው ከሶቪየት ጋር ባላት የህዋ ቴክኖሎጂ እሽቅድምድም የት ጋር እንደደረሰች ስለሚያውቁ ነበር። አሜሪካ ከሩሲያው ዩሪ ጋጋሪ የህዋ ጉዞ አንድ ወር ዘግይቶ አለን ሼፐርድ የተሰኘውን ጠፈርተኛዋን ወደ ህዋ መላክ ችላለች። በቀጣይ ስምንት ዓመታትም ከሩሲያ ሁለት እጥፍ የላቁ መንኮራኮሮችን አምጥቃለች። አሜሪካ ይህን መሰሉ የህዋ ተልዕኮ አልጋ በአልጋ አልነበረም። በጎርጎሮሳዊው 1967 በሙከራ ላይ የነበረ መንኮራኮር ፈንድቶ የሶስት ጠፈርተኞቿን ህይወት ቀጥፏል። ይህ አደጋ አሜሪካ በጊዜው ከነበራት እቅድ 21 ወራት ወደ ኋላ እንድትዘገይ ቢያደርጋትም ከዓመት በኋላ ግን ናሳ ጨረቃን የምትዞር ሳተላይት አምጥቋል። “አፖሎ 8” በተሰኘችው መንኮራኮር ወደ ህዋ የተጓዙት ጠፈርተኞች ለመጀመሪያ ጊዜ ጨረቃን በቅርብ ርቀት መመልከት ችለዋል። ከዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሶስት ጠፈርተኞችን ጭና ወደ ጨረቃ የተወነጨፈችው “አፖሎ 11” በጎርጎሮሳዊው 1969 በዚህን ወቅት በጨረቃ ላይ በማረፍ በታሪክ መዝገብ ላይ ሰፍራለች። በሰው ሳትደፍር ርቃ የቆየችውን ጨረቃም፤ ጠፈርተኞቹ እነ ኔል አርምስትሮንግ፤ ጊዜያቸውን ጠብቀው ተረማምደውባታል። 

40 Jahre Mondlandung
ምስል AP

ተስፋለም ወልደየስ

አዜብ ታደሰ