1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አንፃራዊ ሰላም ማግኘቷ የሚነገርላት ሶማሊያ

ሐሙስ፣ ግንቦት 2 1999

በሶማሊያ መዲና ለቀናት ዘልቆ የሰነበዉ የመንግስት ወታደሮችና ደጋፊዎቻቸዉ በአንድ ወገን ሸማቂዎች በሌላ ወገን ሆነዉ ያጋጋሉት ዉጊያ አሁን ተንፈስ ብሏል። መዲናይቱም አንፃራዊ ሰላም አግኝታለች ተብሏል። ሆኖም ዛሬም ፍንዳታና ጉዳቱ ገና አላበቃም።

https://p.dw.com/p/E0YN
መዲናዋን የሚቃኙት ወታደሮች
መዲናዋን የሚቃኙት ወታደሮችምስል AP

በዛሬዉ ዕለት የነጎደዉ የተቀበረ ፈንጂ እስካሁን የሶስት ሰዎችን ህይወት አጥፍቷል። ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ቡድን ዛሬ ባወጣዉ መግለጫ የራዲዮ ጋዜጠና የነበረዉ ሞሃመድ አብዱላሂ ኻሊፍ ካልካዮ ላይ መገደሉን ጠቅሷል።

የሶማሊያ መዲና ስትታመስ ከሰነበተችበት የሸማቂዎችና የመንግስት ኃይል ዉጉያ ተንፈስ ብላለች ብትባልም ሁኔታዋ እስከምን ድረስ ሊዘልቅ እንደሚችል እያነጋገረ ነዉ። ሰብዓዊ ቀዉሱ ጦርነቱን ሸሽተዉ ከቤት ንብረታቸዉ የተፈናቀሉትን ወገኖች በየዛፍ ጥላዉ ስር እንዲጠለሉ በማስገደዱ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች የዝናቡ ወቅት በመቅረቡ የከፋ ችግር ሊገጥማቸዉ ይችላል የሚለዉን የድረሱላቸዉ ጥሪ እያስተጋቡ ነዉ። ይህ በአንድ ወገን ሆኖ ዛሬም ምድሪቱ ያለመርጋቷ ምልክት እየታየ ነዉ። ትናንት የደህነት ኃይሎች ሸደር የተከናነቡ ሱማሊያዉያን ሴቶችን ለአደጋ ጣዮች መጠቀሚያ ይሆናል በሚል መግፈፍ ሲጠነክርም ማቃጠላቸዉ ተሰምቷል። በርግጥ ይህ ተፈፅሞ ከሆነ መነሻዉ ምን ይሆን?

«አዎ ትክክል ነዉ! ትናንትና ከትናንት ወዲያ ነዉ የተደረገዉ። በርካታ ሴቶች የፊታቸዉን መሸፈኛ ሸደር እንዲያወልቁ ተገደዉ የመንግስት ወታደሮች አቃጥለዉታል። መንግስት የሚለዉ የእስላማዊ ሸንጎዉ ርዝራዦች የሴቶችን ሸደር ለብሰዉ በመዲናዋ የመንግስት ይዞታዎችን ሊያጠቁ ይችላሉ ነዉ። ይህ መንግስት ለድርጊቱ የሰጠዉ ምክንያት ነዉ። ሆኖም በርካታ ሴቶችና ሰላማዊ ዜጎች ሂጃባቸዉ ሲቃጠልና በአሁን ሰዓት በየስፍራዉ በሚገኙ የመንግስት ወታደሮች ሰብዓዊ መብታቸዉ ሲጣስ በጣም እየተሰቃዩ ነዉ።»

ለወራት መቃዲሾን ተቆጣጥረዉ የከረሙት የሸሪዓ ፍርድ ቤቶች ህብረት መሪዎች በወቅቱ ሴቶቹ ሸደር እንዲለብሱ ደንግገዉ ነበር ተብሏል። በአንፃሩ መቃዲሾ ዉስጥ የሚገኙት ከፍተኛ የፖሊስ መኮንን አሊ ኑር ለዘጋቢዎች እንዳሉት በአሁኑ ሰዓት እያንዳንዱ ፖሊስና የመንግስት ወታደር ይህን እንዲቀማ ትዕዛዝ ተሰጥቶታል። እንደእሳቸዉ አባባል ከሆነ ከመዲናዋ የተባረሩት ሙስሊም ሚሊሺያዎች ወገን ተራፊዎቹ በጦርነቱ ወቅት እንደሴት ሸደር ለብሰዉ አደጋ አድርሰዋል የተያዙም አሉ።

ካለፈዉ ጋ ሲተያይ አንፃራዊ ሰላም እንደሰፈነባት የሚነገረዉ መቃዲሾ ዛሬ ደግሞ በተቀበረ ፈንጂ የሁለት ሰዎች ህይወት ጠፍቶባታል፤ ሌሎችም ተጎድተዉባታል። ወደደቡባዊ መቃዲሾ በአጀብ ይጓዙ የነበሩት የእስር ቤት አዛዥ አብዱላሂ ማዕሊም መኪና ሲያልፍ የነጎደዉ ፈንጂ አዛዡን ባይጎዳም ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት አድርሷል ነዉ የሚሉት የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ሞሃመድ ኦስማን ዳግቱር። የአይን ምስክሮች የሁለት ሰዎች አስከሬን በፖሊስመኪና ሲጫን መመልከታቸዉን ቢጠቅሱም በፖሊሶች ኃይሎች ላይ ጉዳት ስለመድረሱ ያረጋገጡት ነገር የለም። በስፍራዉ የሚገኘዉ ጋዜጠኛ እንደሚለዉ ከተማዋ አንጻራዊ ሰላም ሰፍኖባታል ቢባልም የመንግስትን ወታደሮች በመቃወም ፍንዳታዎች ቀጥለዋል፤

«ፍንዳዎች፤ በመዲናዋ የሚገኙትን የፖሊስና የመንግስት ወታደሮች በመቃወም የተቀበሩ ፈንጆዎችና የቦንብ ፍንዳታዎች በየስፍራዉ ይታያሉ። ሌላዉ ደግሞ በኢትዮጵያና በዑጋንዳ ወታደሮች በሚደገፉት የመንግስት ኃይሎች ከሰዉ ቤት ሰራሽ ፈንጂዎችን ጨምሮ የተለያዩ መሳሪያዎች ተሰብሰበዉ ለጋዜጠኞች መቃዲሾ ላይ ታይተዋል። ሁኔታዉ ተረጋግቷል። በእርግጥ የሚካሄድ ጦርነት የለም። ሆኖም አንዳንዴ ፍንዳታዎች በመዲናይቱ ይሰማሉ። በዚያ ላይ መንግስት ሰዎችን እየያዘ ነዉ። ትናንት ያልታወቁ ታጣቂዎች በርካታ ቦምቦችን መዲናይቱ ዉስጥ በሚገኙ የመንግስት ይዞታዎች ላይ መወርወራቸዉን ተከትሎ ወደአንድ መቶ የሚጠጉ ሰዎች ታስረዋል። መንግስት ይዞታዉን ለማጥቃት የሞከሩትን አሳዶ እንደሚይዝ ዝቷል።»

የመንግስት ወታደሮችም በከተማዋ ህገ ወጥ ያሏቸዉን በጎዳና ዪገኙ ኪዮስኮች ማፈራረሳቸዉንም ጋዜጠኛዉ ጨምሮ ገልጿል።

በሌላ በኩል በተረጋጋችዉ የሶማሊያዋ ራስ ገዝ ፑንት ላንድ ሁለት የግብረ ሰናይ ድርጅት ሰራተኞች ታግተዋል። ቀደም ሲል የፑንት ላንድ መንግስት በህገ ወጥ መንገድ አሳ የሚያሰግሩ ጀልባዎችን ይይዝ እንደነበር ቢናገርም የኬር ዓለም ዓቀፍ ሰራተኞች የሆኑት ኬንያዊና አየርላንዳዊ ዜጎች እገታ እጁ እንደሌለበት ነዉ ያስታወቀዉ። አጋቾቹ ምናልባት የታጠቁ ገንዘብ ፈላጊዎችወይም ሌላ አጀንዳእ ያላቸዉ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተገምቷል። ሰዎቹን ለማስለቀቅ የሚደረገዉ ሂደት ምን እንደሚመስል አዌይስ ሲገልፅ

«ከጎሳ መሪዎችና ከፑንትላንድ አስተዳዳሪዎች ጋ ግንኙነት እያደረግን ነዉ። እነሱም አጋቾቹን ሰዎቹን በሚለቁበት መንገድ ላይ እንደሚያነጋግሩ ገቃል ገብተዋል። ሰዎቹ እስከ አሁን በአጋቾቻቸዉ እጅ ነዉ የሚገኙት።»