አዲሱ ዉጊያና የዲፕሎማሲዉ ጥረት
ማክሰኞ፣ መስከረም 10 2015
ኢትዮጵያን ከኤርትራ ጋር በሚያዋስኑት አካባዎች መጠነሰ ሰፊ ዉጊያ መቀስቀሱን የተለያዩ ምንጮች እየዘገቡ ነዉ።አዲስ ዉጊያ መጀመሩ የተዘገበዉ ለሁለት ዓመት ጥቂት ሳምንታት የቀረዉን ጦርነት ለማስቆም የሚደረገዉ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት መጠናከሩ በሚነገርበት ወቅት መሆኑ ነዉ።ተፋላሚ ኃይላትን ለመሸምገል እስካለፈዉ አርብ ድረስ አፍሪቃ ቀንድ የነበሩት የዩናይትድ ስቴትስ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር ጥረታቸዉን እንደሚቀጥሉ የዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር አስታዉቋል።አንድ የፖለቲካ ተንታኝም ዲፕሎማሲያዊዉ ጥረት ለፍሬ የሚበቃ ይመስላል ይላሉ።
ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው፣ልዩ መልዕክተኛው ሰሞኑን በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ፣ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ ከሌሎች የሃገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ተወያይተዋል።
በአትላንቲክ ካውንስል ከፍተኛ ተመራማሪ አቶ ገብርኤል ንጋቱ፣ጉዳዮን አስመልክቶ ለዶይቸ ቨለ እንደተናገሩት፣የሠላም ውይይት የመጀመር ተስፋ ይታያል።
የልዮ ልዑኩን የኢትዮጵያ ቆይታ በዝርዝር በገለጸበት መግለጫው፣ አምባሳደር ሐመር፣በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ጉዳይ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድን እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንን አግኝተው ተወያይተዋል ብሏል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ።
ልዮ መልዕክተኛው፣በአዲስ አበባ የአሜሪካ ኤምባሲ ጉዳይ ፈጻሚ ከሆኑት ትሬሲ አን ጃኮብሰን ጋር በመሆን ነው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣናትን ማወያየታቸው የተገለጸው።
በዙሁ ወቅትም፣በሰሜን ኢትዮጵያ እንደ አዲስ ስላገረሸው ውጊያ እና ኤርትራ ወደ ግጭቱ ተመልሳ ስለመግባቷ አሜሪካ ስላላት ስጋት እንዲሁም ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በአፍሪካ ህብረት አማካይነት የሚካሄደው ጥረት ስለሚጠናከርበት ሁኔታ መነጋገራቸውን መግለጫው አመልክቷል።
ማይክ ሐመር፣ከአፍሪክ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት፣ከኢትዮጵያ የፍትሕ ሚኒስትር ዶክተር ጌዴዎን ጢሞቲዮስ፣ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ሬዲዋን ሁሴን ጋርም መወያየታቸው ተጠቅሷል።
መግለጫው እንዳለው፣አምባሳደር ሐመር ከትግራይ ክልል አመራሮች ጋርም የተወያዩ ሲሆን፣ከሁለቱም ወገን ጋር በተደረገው ውይይት፣ወደትግራይ አፋርና ዐማራ ክልሎች ያልተገደበ ሰብዓዊ ዕርዳታ ስለሚቀርብበት ሁኔታ መክረዋል።
ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ እንዲደረግ፣የሰብዓዊ መብት እንዲከበር ከተፈጸሙ ጭፍጨፋዎች ጋር በተያያዘ ተጠያቂነት እንዲኖር፣ለሰለባዎችና ከጥቃት ለተረፉት ፍትሕ ስለሚያገኙበት ሁኔታ እንዲሁም ብሔር ተኮርን እስር በተመለከተ የሚወጡ ሪፖርቶችን በተመለከተ በውይይቱ የተነሱ ነጥቦች ናቸው።
ልዩ መልዕክተኛው፣በአዲስ አበባ ቆይታቸው፣በአፍሪካ ህብረት ተሰይመው ጦርነቱን ለማስቆም ጥረት ከሚያደርጉት የህብረቱ ከፍተኛ ተወካይ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴጉን ኦቦሳንጆ ጋር በተደጋጋሚ በመገናኘት፣ሰላም ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ውስጥ አሜሪካ ማድረግ በምትችለው ድጋፍ ዙሪያ ተወያይተዋል።
ከኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት፣የአፍሪቃ ህብረት ተወካዮች እና ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር ወደፊት መወሰድ ስላለባቸው ዕርምጃዎች ከመከሩ በኃላ፣አምባሳደር ማይክ ሐመር ባለፈው ዓርብ መስከረም ስድስት ቀን 2015 ዓ.ም ወደ ዋሽንግተን መመለሳቸውን የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መግለጫ አብራርቷል።
በትናንትናው ዕለት፣ኒውዮርክ ውስጥ ከተጀመረው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ጎን ለጎን፣አምባሳደር ሐመር የጀመሩትን የዲፕሎማሲ ጥረት እንደሚቀጥሉ ተጠቁሟል።
ሁኔታውን በቅርበት የሚከታተሉት፣በአትላንቲክ ካውንስል ከፍተኛ ተመራማሪ አቶ ገብርኤል ንጋቱ፣በተፋላሚ ኀይላቱ መኻከል የዕርቅ መጀመር ተስፋ ያለ ይመስላል ይላሉ።
"ማይክ ሐመርም በአንድ ጎኑ እየገፋ ነው።እነሱም በጠየቁት መሠረት ኡሁሩ ኬንያታ ከኦባሳንጆ ጋር ሆኖ አብሮ እየረዳ ዕርቁን ዝግጁነቱ ታውቋል።የዛሬ ሳምንት ናይሮቢ ነበርኹና የአሜሪካ ምክትል የአፍሪቃ ኃላፊ ሞሊ ፊ እዚያ መጥታ ነበር፣እርሷም ገፋፍታና አሳምና፤ አዲሱ የኬንያ ፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶ፣ኡሁሩ ኬንያታን ሾመውታል እርሱም ተቀብሏል።እና አሁን ባለው ሁኔታ የዕርቁ ንግግር ከበድ ያሉ ነገሮች ላይ ሳይሆን መጀመሪያ በስርዓቱ አደራዳሪው እንግዲህ ተወስኗል፣ቦታው የትም ሊሆን ይችላል።አጀንዳው ምን ይሆን? መጀመሪያ የትኛዎቹ ነጥቦች ይነሱና እንደራደር ከዚያ የትኛው ይቀጥል የሚለው እና እዛ ላይ ስምምነት እየተደረሰ ከስር ከስር እየተሸረፈ ነው።እህልና ዕርዳታ መግባቱን ይቀጥላል።ሰላሙ በዚሁ ከቀጠለ መሠረታዊ አገልግሎት የሚባሉት መብራት ውኃ የመሳሰሉት በሂደት የሚገቡበት ሁኔታ አለና የዕርቁ መጀመር ዋናው የመጀመሪያው ዕርምጃ ነው።መንግስትም ሲለው የቆየው ይህንን ነው።በሁሉም በኩል በዚህ ላይ የተስማማ ይመስላል።እንግዲህ በአጭር ጊዜ የሚሆነውን እናያለን።"
በዚህ ሂደት አሜሪካ በኦሊሴጉን ኦባሳንጆ አማካይነት በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር በሚካሄድ የአደራዳሪነት ጥረት ላይ የአጋዥነት ሚና እንደምትጫወት ከፍተኛ ተመራማሪው ተናግረዋል።
ይሁንና፣በአፍሪቃ ቀንድ የኘሬዚዳንት ጆሴፍ ባይደን አስተዳደር የውጭ ፖሊሲን በመቃወም፣ በነጩ ቤተመንግስት ፊት ለፊት ብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን፣ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ባለፈው እሁድ ታላቅ ትዕይንተ ሕዝብ አካሄደዋል።ይህንኑ እንቅስቃሴ አሜሪካኖቹ ፀረ ምዕራብ ንቅናቄ አድርገው ያዩታል የሚሉት አቶ ገብርኤል፣በተቻለ መጠን እንዲዳከም እየጣሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
በተቻለ መጠን ይሄ ነገር እንዲዳከም እየጣሩ ነው፣ጥረዋልም፤ ከዚህ በፊት አሁንም እየጣሩ ነው።ነገር ግን ነገሩ ደግሞ የበለጠ ድጋፍና ዝና እያተረፈ የመጣ ነው።አሁን ባለው ሁኔታ አሜሪካ በረዳትነት ነው።ረዳት አለ ሌላ ደግሞ ረዳት አለ።የአሜሪካ ረዳትነት ጡንቻ ያለው ረዳትነት ነው።ምንም እንኳን ራሱን ረዳት ቢልም ትንሽ ተጽእኖ የማድረግ ኃይል አለው አሜሪካ" ብለዋል።
ታሪኩ ኃይሉ
ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዬ ለገሰ