ኢትዮጵያንና ኬንያን የጎዳው ከባዱ ድርቅ
ቅዳሜ፣ ጥር 21 2014የተመ የሰብዓዊ እርዳታዎች ማስተባበሪያ ቢሮ በእንግሊዘኛ ምህጻሩ ኦቻ እንዳለው ደቡብና ምስራቅ ኢትዮጵያን በመታው ድርቅ ሰበብ ቢያንስ 6 ሚሊዮን ሰዎች በዚህ ዓመት የህይወት አድን እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። የሶማሌ ክልልን እና ምሥራቅና ደቡብ ኦሮምያን ይበልጥ ባጠቃው በዚህ ድርቅ አብዛኛዎቹ ተጎጂዎች አርብቶ አደሮች ናቸው።በነዚህ አካባባዎች በሶስት የዝናብ ወቅቶች ዝናብ አልጣለም።ኦቻ በጎርጎሮሳዊው 2022 መጀመሪያ ላይ ባቀረበው የሰብዓዊ ቀውስ ዘገባ የጠቀሰው የሶማሌ ክልል የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ቢሮ፣ በክልሉ በሚገኙት ፋፋን እና ሲቲ በተባሉት ዞኖች ይመረታል ተብሎ ይጠበቅ የነበረው የሰብል መጠን በእጅጉ ቀንሷል። እንደቢሮው ከተጠበቀው የማሽላና የበቀሎ ምርት 70 በመቶው አልያዘም፤በተመሳሳይ ሁኔታ የስንዴ ምርትም በ30 በመቶ ቀንሷል። በደቡብ ኦሮምያም በአማካይ 70 በመቶ ሰብል መጥፋቱን 267 ሺህ የቀንድ ከብቶች በመኖና በውኃ እጥረት መሞታቸውን አስታውቋል።በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሌሎች የቀንድ ከብቶች በመኖና ውኃ እንዲሁም በክትባት እጦት ህይወታቸው አደጋ ላይ ነው።በተለይ በኦሮምያ ቦርና ዞን ችግሩ የከፋ ነው።የቦረናን ሁኔታየኦሮምያ ክልል ግብርና ቢሮ ና የእንሰሳት ሀብት ልማት ዘርፍ ሃላፊ ዶክተር ቃሲም ጉዮ ሰሞኑን ለዶቼቬለ ተናግረዋል።
በድርቁ ምክንያት ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች ከአካባቢያቸው መፈናቀላቸውን ኦቻ በዘገባው አስፍሯል። በሶማሌ ክልል የሚገኙ 2.3 ሚሊዮን በደቡብ ኦሮምያ ደግሞ 870 ሺህ ሰዎች በውኃ ችግር እየተሰቃዩ ነው።በድርቁ ምክንያት ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸውና የትምህርት ቤቶች የምገባ መርሃ ግብር በመቅረቱ በሶማሌ ክልል የ99 ሺህ በደቡብ ኦሮምያ ደግሞ የ56 ሺህ ተማሪዎች ትምህርት ተስተጓጉሏል ይላል የኦቻ ዘገባ። ዶክተር ቃሲምም ድርቁ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እያስከተለ መሆኑን በትምህርትም ላይ ተጽእኖ ማድረጉን ተናግረዋል።የውኃና የእንሰሳት መኖ ችግርም ከአቅም በላይ መሆኑን አስረድተዋል።
በኦቻ ዘገባ መሠረት በኢትዮጵያ ድርቅ ባጠቃቸው አካባቢዎች የሚገኙ ከ6.4 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በጎርጎሮሳዊው አዲስ ዓመት 2022 የምግብ እርዳታ ይሻሉ።ከመካከላቸው 3 ሚሊዮን በሶማሌ ክልል 2.4 ሚሊዮን በምስራቅ ኦሮምያ አንድ ሚሊዮኑ ደግሞ በደቡብ ኦሮምያ ይገኛሉ።በኦሮምያ ክልል የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር ሙስጠፋ ከድር ለዶቼቬለ እንደተናገሩት በአጠቃላይ በኦሮምያ እርዳታ የሚሰጠው ሰው ቁጥር ወደ አምስት ሚሊዮን ይጠጋል።በክልሉ እምነት ድርቁ የሰው ሕይወት ያጠፋል የሚል ስጋት የለም።
ይሁንና ኮሚሽነሩ እንደሚሉት በአካባቢው በድርቅ ለተጎዱ ከብቶች መኖ ማቅረብ ከባዱ ፈተና ሆኗል።
ኦቻ እንደሚለው ይህን ችግር ለመቋቋም ውኃ ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ አስቸኳይ ሰብዓዊ እርዳታዎች መቅረብ አለባቸው። ለመድረስ አሰቸጋሪ በሆኑ አካባቢዎችም ተንቀሳቃሽ የጤናና የምግብ ስርዓት ተከታታይ ክሊኒኮች እንዲቋቋሙ ሃሳብ አቅርቧል።
እንደ ኢትዮጵያም ባይሆን በኬንያም ድርቅ ተመሳሳይ ችግር አስከትሏል። ሰሜን ኬንያ ውስጥ በሚገኘው ማርሳቢት በተባለው ወረዳ የቀንድ ከብቶች እየሞቱ ነው። ፊሊፕ ኤዎቶን ቬልት ሁንገር ሂልፈ የተባለው የእርዳታ ድርጅት ባልደረባ ናቸው።በማርሳቢት ድርቅ ያስከተለውን ጉዳት ለዶቼቬለ ገልጸዋል።
«በየመንደሮቹ የሞቱ እንሰሳት ይታያሉ። በህይወት የሚገኙት ላሞችና ግመሎችን ጨምሮ አንዳንድ እንሰሳት መራመድ አይችሉም። ኅይለኛው ሙቀት ይገድላቸዋል። የሚሞቱትም በቂ ውኃ ስለሌለን ነው። ህብረተሰቡ እነዚህን እንሰሳት ውኃ ለማምጣት ይጠቀምባቸዋል። ውኃ ለማምጣት ረዥም ርቀት መጓዝ አለባቸው። አቅም ስለሌላቸው ግን አብዛኛዎቹ ይህን ማድረግ አይችሉም።»
በድሃይቱ ማርሳቢት ስጋት የሆነው የአሁኑ ጉዳት ብቻ አይደለም፤ የወደፊቱም እንጂ። በአሁኑ ጊዜ በወረዳዋ የሚገኙ 183 ሺህ ሰዎች የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። ይሁንና ዝናብ ካልዘነበ የእርዳታ ፈላጊዎቹ ቁጥር ከፍ ማለቱ እንደማይቀር ኤዎተን ይሰጋሉ።በአካባቢው በሶስት የዝናብ ወቅቶች ዝናብ አልጣለም። እስካሁን በሚታወቀው የአካባቢው የድርቅ ታሪክ ይህን ያህል ጊዜ ዝናብ ሳይጥል የቀረበት ጊዜ እንደሌለ ፊሊፕ ኤዎቶን ገልጸዋል።በኬንያ አንዳንድ ግዛቶ ከ80 እስከ 90 በመቶ የሚሆኑ ግድቦችና የውኃ ማቆሪያዎች ካለፈው ታኅሳስ አንስቶ ደርቀዋል።በውኃ እጦት ማሳ ላይ የነበሩ አትክልቶች አረዋል፤አፈሩም ደርቋል። በኬንያ ዋነኛ ምግብ የሆነው የበቆሎ ምርት በ70 በመቶ ቀንሷል። ከድርቁ ጋራ የአንበጣ መንጋና የኮሮና ወረርሽኝ መዘዞች ተደምረው ሁኔታውን አባብሰውታል ። የማርሳቢት ሀገረ ገዥ ሞሀመድ አሊ ህዝቡን ከተጨማሪ ረሀብ መታደግ ይገባል ይላሉ ።
« ወረዳችን ደረቅ ከሆኑ አካባቢዎች አንዱ ነው። ከብቶቻችን እየሞቱ ነው።በሀገራችን ረሀብ ህዝቡን እያሰቃየው ነው።ዝናብ ካጣን አንስቶ ከባድ ችግር ውስጥ እንገኛለን። እናም እንደ መንግሥት ህዝባችን ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስበት ማረጋገጥ አለብን። »
በማርሳቢት የአሁኑ ብቻ ሳይሆን የወደፊቱም አሳሳቢ ነው። ከመጪው መጋቢት እስከ ግንቦት ዝናብ መዝነቡ አጠራጥሯል። በብዙ አካባቢዎች እንደ ከዚህ ቀደም ጥቂት ዝናብ ብቻ ይጥላል ተብሎ ተፈርቷል። በተለይ ረሀብ ባሰጋቸው የማርሳቢት ወረዳን በመሳሰሉት አካባቢዎች ፍርሀቱ ከፍተኛ ነው፤እንደ ኤውቶን ።
«አርብቶ አደሮች ፈርተዋል።ምክንያቱም ቀስ በቀስ ከብቶቻቸው ሲሞቱ ኑሮአቸውም ሲዳከም እያዩ ነው።አሁን በጣም የሚያስፈራቸው ድርቁ የቤተሰቦቻቸውን አባላት ጠራርጎ እንዳይወስድባቸው ነው። የልጆቻቸው የሴቶች እና አዛውንቶች ሕይወት እንዳያልፍ ነው አሁን ትልቁ ስጋታቸው።»
በኬንያ ምክር ቤት የአካባቢው ተወካይ ቱራ ኤልማ ሰዎች በምግብ እጦት መሞት መጀመራቸውን ይናገራሉ።
«በርካታ ፈተናዎች አሉብን ኖርዝ ሆር ዋርድ በጣም የተጎዳ አካባቢ ነው አንድ ሰው ሞቶብናል።69 ዓመቱ ነበር።የሞተውም በረሀብ ነው።በደረሱኝ ሪፖርቶች መሰረት በምግብ እጦት ራሳቸውን የሚስቱ ሰዎች አሉ።ይህ የህይወት ጉዳይ ስለሆነ ነው አስቸኳይ እርዳታ እንዲሰጥ ጥሪ የምናቀርበው።ሰውየው የሞተው ከአንድ ሳምንት በፊት ነው። እስካሁን ምንም ምላሽ የለም።መንግሥት የኖርዝ ሆር ዋርድ ህዝብ እንዲረዳ ጥሪ አቀርባለሁ፤ምክንያቱም አካባቢው ክፉኛ ተጎድቷል።»
350 አፍሪቃ ዶት ኦርግ የተባለው የአካባቢ ጥበቃ ድርጅት የአፍሪቃ ጉዳዮች ሃላፊ ላንድሪ ኒተረስተ የአየር ንብረት ለውጥ የችግሩ መንስኤ ነው ይላሉ።
« ባለፉት ጥቂት ዓመታት ወረዳው በተደጋጋሚ በድርቅ ተመቷል። የአየር ንብረ ለውጥ ድርቅ እንዲደጋገም እያደረገ ነው።በመስኩ ባለሞያዎች እምነት በአፍሪቃ ቀንድ ሀገራት የተከሰተው ድርቅ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ይገኛል።»
ሰዎች አሁን በአፍሪቃ ቀንድ በድርቅ በተጎዱት አካባቢዎች የቀድሞውን ዓይነት ህይወት መምራት እንደማይችሉ ነው የሚያስቡት።የመስኩ ባለሞያዎች እና የመብት ተሟጋቾች ግን እንደ አሁኑ ዓይነት ሰብዓዊ ጥፋትን የሚያስከትል አስቸጋሪ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም መሰረታዊ ማስተካከያዎችን ማድረግ አስፈላጊ ብለው ያምናሉ። ኒተረስተ ዘላቂ ድጋፍ እንዲሰጥ ነው የሚጠይቁት። በተለይም የዝናብ ውኃን ማጠራቀም። ዘመናዊ የመስኖ ቴክኒኮችን ማስፋፋት እንዲሁም ድርቅን መቋቋም የሚችሉ ተክሎችን ማብቀልና የመሳሰሉት ትኩረት እንዲሰጣቸው የሚያደርግ ድጋፍ ያሻል ይላሉ። ኤውተን ደግሞ የየአካባቢውን ኤኮኖሚ ማሳደግ፣ ገበያን ማስፋፋትን ይመክራሉ። ማርሳቢትን ምሳሌ ያደረጉት ኤውተን በዚያ በግመሎች ብዙ የእርሻ ስራ ላይ ጥቅም ላይ እንደሚውሉ አስታውሰው የግመሎችን የወተት ምርት መጠንን ማሳደግ ትኩረት እንዲሰጠው መክረዋል። በድርቅ የሚጎዱ አካባቢዎች ለአካባቢያቸው ብቻ ሳይሆን ለመለ ሃገሪቱ ምርታቸውን በማቅረብ የተሻለ ገቢ ማግኘት እንደሚችሉም ተናግረዋል። ይህ የአካባቢውን ህዝብ ብቻ ሳይሆን ከኬንያ መንግሥት አቅምም በላይ ነው ይላሉ። የአካባቢ ጥበቃ ባለሞያው ኒተረስተ ግን ወጪውን የበለጸጉት አገራት መሸፈን አለባቸው ነው የሚሉት።
«ኬንያ ለአየር ንብረት ለውጥ በጋዝ ልቀት ረገድ እጅግ በጣም አናሳ አስተዋጽኦ ከሚያደርጉ የአፍሪቃ ሀገራት አንዷ ናት። ነገር ግን ተጽእኖው ደርሶባታል። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከዚያም በላይ ያደገው ዓለም እነዚህ ሀገራት ከተለወጠው የአየር ንብረት ጋር ተላምደው መኖር የሚችሉበትን የአየር ንብረት ድጎማ ለመስጠት ቃል መግባት አለባቸው»
ኂሩት መለሰ
እሸቴ በቀለ