ኢትዮጵያ ብድር እንድታገኝ የተካሄደ ውይይት
ሰኞ፣ ሚያዝያ 9 2015ኢትዮጵያ ከዓለም ዓቀፉ የገንዘብ ድርጅት(አይ ኤም ኤፍ) ድጋፍ ለማግኘት በምታካሂደው የፖሊሲ ማሻሻያ ውይይት ስምምነት ላይ ለመድረስ መቃረቧ ተገለጸ። ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ በተካሄደ፣የአይ ኤፍ ኤም እና የዓለም ባንክ "የስፕሪንግ" ጉባኤ ላይ የተሳተፈው የኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ልዑክ፣የኢትዮጵያን የውጭ ዕዳ መልሶ በማዋቀር ዕፎይታና ብድር ማግኘት የሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክሯል።
በገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ የተመራ የኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ልዑካን ቡድን፣ ሰሞኑን ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ በተካኼደው፣የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅትና ዓለም ባንክ ጉባዔ ላይ ተሳትፏል።
አይኤምኤፍ ለኢትዮጵያ ሊሰጥ በሚችለው ድጋፍ ዙሪያ ቴክኒካዊ የተባለ ሥራ ለማከናወን፣የድርጅቱ ባለሥልጣናት ከዚህ ቀደም አዲስ አበባ ውስጥ ቆይታ አድርገው መመለሳቸው ታውቋል። ኢትዮጵያ በከፍተኛ ዋጋ ግሽበት፣ የውጭ ምንዛሪ ንረት፣ግጭትና ድርቅ የተጎዳውን ምጣኔ ሀብት እንዲያገግም ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ብድር ለማግኘት ትሻለች።
ዘገባዎችን የሚያመለክቱት፣ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት የሁለት ቢሊዮን ዶላር ብድር ለማግኘት ከተቋሙ ጋር እየተነጋገሩ ናቸው። ለዚህ እንዲረዳም በፖሊሲው ማሻሻዎች ውስጥ ውይይት ማካሄድ አስፈልጓል።
ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ የአይኤምኤፍ እና የዓለም ባንክ የጋራ ጉባዔ በተደረገበት ወቅት የተካኼደው ውይይት ለስምምነት መቃረቡን ዶይቸ ቨለ ያነጋገርናቸው እና ጉዳዩን በቅርበት የተከታተሉት፣በአትላንቲክ ካውንስል የአፍሪቃ ማዕከል ከፍተኛ ተመራማሪ አቶ ገብርኤልን ንጋቱ፣ ገልጸዋል። "አይ ኤፍ ኤም የሪፎርም ማስተካካያ ፕሮግራሞች አሉ።እነሱ ላይ ሙሉ በሙሉ ሥምምነት ላይ ለመድረስ የተቃረቡ ይመስለኛል።
ስምምነት ላይ እንደተደረሰ፣ ይሄን ወደ ቦርድ አቅርቦ ማስፈቀድ ነው። ስለዚህ ፕሮግራሙ ላይ ችግር የለም የሚል አንድምታ ነውያለው። እርግጠኛ ነኝ ደግሞ ኢትዮጵያ ማሻሻያውን ለራሷ ብላ የምታደርገው እንጂ አይ ኤም ኤፍ ስላለውም አይደለም። ቀድሞ ብዙውን ሪፎርም በግሏ በሃገር በቀል የኤኮኖሚ ፕሮግራሙ በኩል እየተካሄዱ ነው።አንዳንድ ጉዳዮች እንደውጭ ምንዛሬ የማስተካከል የመሳሰሉትን እነሱ እነሱን በይበልጥ ጠለቅ ባለ ደረጃ ውይይት ይደረግባቸዋል። ግን አንዴ እዛ ላይ ሙሉ በሙሉ ስምምነት ሲደረስ ፕሮግራሙ ለቦርድ ማኔጅመንት ይቀርብና ገንዘቡን ያስፈቅዳል።"
የዓለም ባንክ ፕሬዝደንት ዴቪድ ማልፕስ፣ ኢትዮጵያ ጨምሮ ሌሎች ታዳጊ አገሮች ያለባችሁን ከፍተኛ የውጭ ዕዳ ማቅለያ ለማራዘም ያቀረቡትን ጥያቄ መዘግየቱን። አሳሳቢ ብለውታል። በአፍሪቃ ልማት ባንክና ዓለም ባንክ የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት የሰሩት፣አቶ ገብርኤል ጥያቄው በርግጥም ጊዜ መፍጀቱ፣ የሀገራቱን ምጣኔ ሀብት የሚጎዳ መሆኑን ገልፀው፣ በአጭር ግዜ ውስጥ መፍትሄ ያገኛል የሚል እምነት እንዳላቸው ጠቁመዋል።
"ትንሽ ጊዜ መፍጀቱ፣ ኢትዮጵያንም ሌሎችን ሃገሮች እንደ ጋና እዛ ውስጥ የገቡት አሉና ትንሽ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ይታይባቸዋል። ምክንያቱም ጊዜ ፈጀ ይሄ ነገር።ኢኮኖሚያችን እየተጎዳ ነውና ይኼን ነገር ቶሎ እንጨርስና ይዘጋ ይኼ ድርድር ቶሎ ይዘጋ ይኼ ድርድር የሚል ጥሪ ይሰማል። እንግዲህ እስኪ ከዚህ በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ድርድሩ መፍትሔ ላይ ደርሶ ይዘጋል የሚል እምነት አለኝ።"
ባለፉት ሁለት ዓመታት፣ በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደው ጦርነት ሰበብ፣ኢትዮጵያ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ጋር የነበራትን ግንኙነት በመሻከሩ፣ አስፈላጊውን ደጋፍ እንዳታገኝ አድርጓት ቆይቷል። ከቻይና ይገኛል የተባለው ብድርም፣ በምዕራባዊያኑ ዘንድ በምክንያትነት ሲጠቀስ ይሰማል።
የውጭ ዕዳ ማቅለያ ዕፎይታ ጊዜውን በተመለከተ እና በሌሎች ድጋፎች ዙሪያ፣ ከአሜሪካ መንግስት ጋር ሰፋ ያለ ውይይት የተደረገበት አጀንዳ እንደነበር፣በአትላንቲክ ካውንስል የአፍሪቃ ማዕከል ከፍተኛ ባልደረባ አቶ ገብርኤል አስረድተዋል።
" ከአሜሪካ መንግስት ጋር ሰፋ ያለ ድርድር ተደርጓል።ከተለያዩ ባለስልጣንኖችም ጋር ተገናኝተው ንግግር አድርገዋል።እና በሰፊው ለማስረዳት ተችሏል።ምን እየተደረገ እንደሆነ፣ምን እንደቀረ፣ ምን ዓይነት ተግዳሮቶች እንዳሉ በሰፊው ማስረዳት ተችሏል እና አሁን ትንሽ ረገብ ያለ ይመስላል።እንግዲህ ፖለቲካው ረገብ ካለ በኢኮኖሚው ያለው ሥምምነት ይደረሳል የሚል እምነት አለኝ።"ብለዋል።
ታሪኩ ኃይሉ
አዜብ ታደሰ
እሸቴ በቀለ