ውይይት፤ የአማራ ክልል ምስቅልቅል እና የክልሉ ነዋሪ ሰቆቃ እንዴት ያብቃ?
እሑድ፣ ኅዳር 22 2017በአማራ ክልል በመካለከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በሚካሄደው እና ከዓንድ አመት በላይ በዘለቀው ግጭት የክልሉን ነዋሪ ለዘርፈ ብዙ ችግር ዳርጎታል። ከሁለት ዓመቱ የሰሜኑ ጦርነት በቅጡ ሳያገግም ወደ ሌላ ጦርነት የገባው ይህ ክልል፤በግጭቱ ሳቢያበአብዛኛው የክልሉ አካባቢዎች የንግድ፣ የትራንስፖርት፣ የጤና፣ የትምህርት እና ሌሎችም እንቅስቃሴዎች መስተጓጎላቸው እና የአገልግሎት መስጫ ተቋማት እየወደሙ መሆናቸው ይነገራል። ወደ ትምህርት ገበታ መሄድ የነበረባቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ የክልሉ ህፃናት በግጭቱ ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው ለመፈናቀል ተገደዋል። የክልሉ ትምህርት ተቋማት ፎረም ሰሞኑን ባወጣው መረጃ ወደ አምስት ሚሊዮን የሚጠጉ ተማሪዎች በክልሉ ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸው ተገልጿል።
በክልሉ እገታ አስገድዶ መድፈር ተደጋግመው የሚሰሙ ዜናዎች ናቸው።ወጥቶ መግባት ሰርቶ መብላት በክልሉ ከባድ ፈተና መሆኑን በተለያዬ ጊዜያት አስተያየት የሰጡ የክልሉ ነዋሪዎች ይገልፃሉ።
ከዚህ ባሻገር ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ሰላማዊ ሰዎች ጦርነቱን ተከትሎ የጥቃት ሰለባመሆናቸውን የመብት ተሟጋቾች በተለያዩ ጊዜዎች የሚያወጧቸው መረጃዎች ያሳያሉ።
ለአብነትም በቅርቡ በሰሜን ጎጃም በድሮን ጥቃት ተገደሉ የተባሉ ሰዎችን ጨምሮ በመራዓዊ፣ በፍኖተ ሰላም፣ በአዲስ ቅዳም ከተማ እና በሌሎች አካባቢዎች በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል ውጊያ መደረጉን ተከትሎ በጦርነቱ ተሳትፎ የሌላቸው ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎችን እና የተጎጂ ቤተሰቦችን ዋቢ አድርገው የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እና የመገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ያም ሆኖ ይህንን ሰቆቃ ለማስቆም በሁለቱ ተፋላሚ ሀይሎች መካከል የሰላም እና የንግግር ፍንጭም አልታየም። ሁለቱን ወገኖች የሚያሸማግል የሰላም ምክር ቤት ቢቋቋምም አስካሁን በተጨባጭ የተጀመረ ወይም የተካሄደ ጥረት ስለመኖሩ በይፋ የተባለ ነገር የለም።በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚደረገው ግፊትም ያን ያህል ጎልቶ አይታይም።
ለመሆኑ ይህንን ምስቅልቅል እና የክልሉ ነዋሪ ሰቆቃ እንዴት ያብቃ? ሰላማዊ ሰዎችንስ ማን ይታደጋቸው? ከሊህቃን ፣ከመንግስት፣ ከተፋላሚ ሀይሎች፣ እንዲሁም ከዓለም አቀፍ ማኅበረሰብስ ምን ይጠበቃል?iየዚህ ሳምንት ውይይታችን ማጠንጠኛ ነው።
በውይይቱ አራት እንግዶች ጋብዘናል።እንግዶቹ፤
ዶክተር ሲሳይ መንግስቴ ---በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የፌደራሊዝም መምህር እና የሰብዓዊ መብት ረዳት ፕሮፌሰር
አቶ ያሬድ ሀይለማርያም---የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል ዋና ዳይሬክተር
አቶ ገለታው ዘለቀ--- ፖለቲከኛ እና የፖለቲካ ተንታኝ- አሜሪካ ከቦስተን
አቶ ያየህ ይራድ- በለጠ---- የአማራ ክልል የሰላም ካውንስል ሀላፊ ናቸው።
ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።
ፀሐይ ጫኔ