1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«የህወሓት ከሽብርተኝነት መሰረዝ መልካም ጅምር ነው» የህወሃት ባለሥልጣን

ረቡዕ፣ መጋቢት 13 2015

የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ አባል እና የክልሉ አስተዳደር የሕግ ጉዳዮች አማካሪ አቶ አማኑኤል አሰፋ፥ «መጀመርያውኑም ህወሓትን በአሸባሪነት መፈረጅ አስፈላጊ አልነበረም» ያሉ ሲሆን፣ አሁን የኢትዮጵያ ፓርላማ እዚህ ውሳኔ ላይ መድረሱ ግን መልካም እርምጃ ነው ብለውታል።

https://p.dw.com/p/4P4yb
Emblem der Tigray People's Libration Font (TPLF)

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔ ላይ ከህወሃት ባለስልጣን የተሰጠ አስተያየት

የኢትዮጵያ ህዝብ ተወካዮች ምክርቤት በዛሬው ልዩ ጉባኤው፥ ከሁለት ዓመት በፊት ህወሓት ላይ ጥሎት የነበረው የሽብርተኝነት ውንጀላ ማንሳቱ ተከትሎ ያነጋገርናቸው የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ አባል እና የክልሉ አስተዳደር የሕግ ጉዳዮች አማካሪ አቶ አማኑኤል አሰፋ፥ «መጀመርያውኑም ህወሓትን በአሸባሪነት መፈረጅ አስፈላጊ አልነበረም» ያሉ ሲሆን፣ አሁን ላይ የኢትዮጵያ ፓርላማ ይህ ውሳኔ ላይ መድረሱ ግን መልካም እርምጃ ነው ብለውታል። እንደ የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ አባሉ አቶ አማኑኤል ገለፃ የህወሓት ከአሸባሪነት ዝርዝር መነሳት በፓርቲው እና ፌደራል መንግስቱ፣ በፓርቲው እና የክልል አስተዳደሮች እንዲሁም ዓለምአቀፍ ተቋማት መካከል ያለው ግንኙነት ሕጋዊ ያደርገዋል ሲሉ ተናግረዋል። 

የዛሬው የኢትዮጵያ ህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ውሳኔ ከሰላም ስምምነቱ አንፃር ሲታይ በሁለቱ ስምምነቱ የፈረሙ ሃይሎች መካከል ያለው መተማመን የሚያሳድግ መሆኑ ያነሱት የህወሓቱ ከፍተኛ አመራር አቶ አማኑኤል አሰፋ፣ ህወሓት ከአሸባሪነት መነሳቱ ተከትሎ በፍረጃው ምክንያት የታሰሩ የትግራይ ተወላጆች እንዲፈቱ፣ ለሶስት ዓመታት ተከልክሎ ያለ የፌደራሉ መንግስት ለትግራይ የሚያደርገው የበጀት ድጎማ እንዲቀጥል መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር ነው ሲሉ አክለዋል። 

የዛሬው የፓርላማ ውሳኔ ከሀገሪቱ የፖለቲካ እንቅስቃሴ አንፃር ሲታይ፣ ህወሓት ከሌሎች የፖለቲካ ሐይሎች ጋር በቀጥታ እና በሕጋዊ መንገድ አብሮ እንዲሰራ፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲጠናከር እንዲያደርግ እንደሚረዳ የህወሓቱ ማእከላይ ኮሚቴ አባል አቶ አማኑኤል ተናግረዋል።

ከተመሰረተ 48 ዓመታት ያለፈው እና በኢትዮጵያ ፖለቲካ ትልቅ ስም ያለው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ከትግራዩ ጦርነት ጋር በተያያዘ ምክንያት በኢትዮጵያ ፓርላማ በአሸባሪነት የተፈረጀው በ2013 ዓመተምህረት ሚያዝያ ወር ነበር።

ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ

ታምራት ዲንሳ

እሸቴ በቀለ