የላሊበላ ከተማ ኗሪዎች በጦርነት ምክንያት ለረሀብ ተዳርገናል አሉ
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 3 2017በላሊበላ ከተማ ህዝብ በኢትዮጵያ መንግስትና የፋኖ ታጣቂ ሀይሎች መካከል እየተካሄደ ያለዉ ጦርነት ለከፋ የኑሮ ዉድነት አጋልጦናል ሲሉ ሰላማዊ ሰልፍ አካሄዱ። ከ2012 ዓመተ ምህረት ጀምሮ የኮረና ወረርሽኝ የሰሜኑ ጦርነትና አሁን ደግሞ በመንግስትና በፋኖ ሀይሎች መካከል የሚካሄደዉ ጦርነት ፣የኑሯቸዉ መሰረት የሆነውን ቱሪዝምን ጎድቶብናል የሚሉት ሰልፈኞቹ ችግሩ ለርሀብ አጋልጦናል ብለዋል። በላሊበላ ከተማ ከ80 ሺህ በላይ ህዝብ ቢኖርም ከደረሰዉ ጉዳት አንፃር የረድኤት ድርጅቶችም ሆኑ መንግስት ተገቢዉን ድጋፍ አላደረገልንም የሚሉት የከተማዉ ነዋሪዎች በገበያ ዉስጥ የተፈጠረ የኑሮ ዉድነት በቱሪዝም ላይ ለተመሰረተ ኑሯችን ፈተና ሆኗል ይላሉ። በከተማዉ የሚገኙ 45 ሆቴሎች ከግጭት ጋር በተያያዘ ከዚህ በፊት ተዘግተዉ ነበር ።በላሊበላ ከተማ የሀገር ዉስጥም ይሁን የዉጭ ጎብኝዎች በግጭቱ ምክንያት እየመጡ ባለመሆኑ ከሆቴል እስከታችኛዉ የስራ ዘርፍ ጉዳት አስተናግዷል የሚሉት አስተያየት ሰጭዎቹ በግጭቱ ምክንያት ዉሎ ለመግባትም ተቸግረናል ይላሉ።
የላሊበላ ከተማ በዮኔስኮ የተመዘገቡ ቅርሶች ያሉበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የመንግስትም ሆነ የፋኖ ኃይሎች ጥንቃቄ ማድረጉተገቢ ነዉ ሲሉ የከተማዉ ኗሪዎች አስተያየታቸዉን ይሰጣሉ ። በመንግስትና በፋኖ ኃይሎች መካከል ንግግር መደረግ አለበት ይላሉ ኗሪዎቹ መንግስትም ይሁን የፋኖ ኃይሎች ለመነጋገር ቅድሚያ ሰጥተዉ ችግሮቻቸዉን ለመፍታትም መዘጋጀት እንዳለባቸዉ ነዉ የሚናገሩት አስተያየት ሰጭዎች በላሊበላ ብል ባላ ይምርሀነ እና ሌሎች የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች ያሉ ቅርሶች አስፈላጊዉ ጥንቃቄ ሊደረግላቸዉ ይገባል በማለት ይናገራሉ። የላሊበላ ከተማ ከንቲባ አቶ ወንድምነዉ ወዳይ እንደሚገልፁትም ባለፋት 5 አመታት የከተማዉ ማህበረሰብ ለከፍተኛ የኑሮ ጫናና ችግር ተጋልጧል በማለት በአካባቢዉ ያለዉ ግጭት ኤምባሲዎች ዜጎቻቸዉ ላሊበላንና አካባቢዉን እንዳይጎበኙ እንዳደረገ ይገልፃሉ.በአካባቢዉ ከሚንቀሳቀሱ የፋኖ ኃይሎች ጋር ለመነጋገርና አካባቢዉን ወደ ሰላም ለመመለስ በመንግስት በኩል ፍላጎቱ አለ የሚሉት አቶ ወንድምነዉ አካባቢዉን ወደ ቀደመ እንቅስቃሴዉ ለመመለስ ይሰራል ብለዋል።
ኢሳያስ ገላው
ኂሩት መለሰ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር