የሐምሌ 24 ቀን 2015 ዓ/ም የስፖርት ዝግጅት
ሰኞ፣ ሐምሌ 24 2015ሰላም ጤና ይስጥልን አድማጮች እንደምን ቆያችሁን ሳምንታዊ ስፖርታዊ መሰናዷችን እነሆ አሁን ጀመረ። በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት የተከናወኑ አበይት ስፖርታዊ ክንውኖች ይዳሰሱበታል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ወደ አሜሪካ ተጉዟል። በሴካፋ የእግር ኳስ ውድድር እየተሳተፈ የሚገኘው ከ18 ዓመት በታች የሴቶች ብሄራዊ ቡድን ከሁለት ተከታታይ ሽንፈት በኋላ የቡሩንዲ አቻውን ማሸነፍ ችሏል። ኒውዚላንድ እና አውስትራሊያ እያስተናገዱ የሚገኘው 2023 የሴቶች ዓለም ዋንጫ ወደ ጥሎ ማለፍ የተሸጋገሩ ሃገራት እየተለዩ ናቸው። አፍሪቃን ከወከሉት ዛምቢያ ከወዲሁ ከውድድሩ መሰናበቷን አረጋግጣለች። በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት የአውሮጳ ኃያላን ክለቦች የወዳጅነት ጫወታዎች አከናውነዋል፤ ጃፓን ቶኪዮ ላይ የጀርመኑን ቦሩሽያ ዶርት ሙንድን የገጠመው የቴን ሃጉ ማንችስተር ዩናይትድ ሽንፈት ገጥሞታል። በዝውውር ዜናዎች የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን እና ፒኤስ ጂ ኮከብ ኬሊያን ምባፔ ማረፊያ ሳይታወቅ የቀን ገደቡ ዛሬ ሊጠናቀቅ ነው ።
ታንዛኒያ ዳሬሰላም እያስተናገደች በምትገኘው የሴካፋ ዞን ከ18 ዓመት በታች ሻምፒዮና እየተሳተፈ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሴት ብሔራዊ ቡድን ትናንት እሁድ ሶስተኛውን ጫወታውን አድርጎ ቡሩንዲን 2 ለ 0 አሸንፏል። ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሁለቱንም የማሸነፊያ ጎሎች ከመረብ ያገናኘችው ደግሞ እሙሽ ዳንኤል ናት። ቡድኑ አስቀድሞ ያደረጋቸውን ሁለት ጫወታዎች መሸነፉ አይዘነጋም። በመጀመሪያ ጫወታ የዩጋንዳ አቻውን የገጠመው ብሄራዊ ቡድኑ 1 ለ 0 በሆነ ጠባብ ውጤት የተሸነፈ ሲሆን ቡድኑ በሁለተኛው ጫወታውም ከአስተናጋጇ ሀገር ታንዛንያ ጋር በውጥረት በተሞላ ጫወታ አድርጎ 2 ለ 0 ተሸንፏል። ቡድኑ አራተኛ ጫወታውን ነገ ከዛንዚባር አቻው ጋር የሚያደርግ ሲሆን ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ የማሸነፍ ግዴታ ተጥሎበታል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግርኳስ ቡድን የወዳጅነት ጫወታዎችን ለማከናወን ትናንት ምሽት ወደ አሜሪካ መጓዙ ተሰምቷል። ከብሔራዊ ቡድኑ አባላት በጉዞ ሰነድ አለመሟላት የቀሩ እንዳሉ ሰምተናል። ቡድኑ በአሜሪካ ቆይታው የተለያዩ የወዳጅነት ጫወታዎችን እንደሚያደርግ ይጠበቃል። የቡድኑ ወደ አሜሪካ መጓዝ እና አጠቃላይ አንድምታ ላይ ከአዲስ አበባው ተባባሪ ዘጋቢያችን ኦምና ታደለ ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርጌአለሁ።
የ2023 የዓለም የሴቶች እግር ኳስ ዋንጫን ወደሚመለከተው ዘገባችን ስንሸጋገር ፤ ኒውዚላንድ እና አውስትራሊያ በጋራ እያስተናገዱ በሚገኘው ሻምፒዮና የጥሎ ማለፉን ዙር የሚቀላቀሉ ሃገራት እየተለዩ ነው። አፍሪቃን ወክለው በውድድሩ እየተሳተፉ ከሚገኙ አራቱ ሃገራት ናይጄሪያ 16ቱን መቀላቀል የቻለች ሀገር መሆን ችላለች ። ዛምቢያ ደግሞ በመጀመሪያው ዙር ተሰናባች ሆናለች። በምድብ ሁለት ውስጥ ከአውስትራሊያ ፣ ካናዳ እና አየርላንድ ሪፐብሊክ ጋር የተደለደለችው ናይጄሪያ በአምስት ነጥቦች አዘጋጇን ሀገር አውስትራሊያን ተከትላ ቀጣዩን ዙር መቀላቀሏን አረጋግጣለች። በምድብ 3 ከጃፓን፣ ስፔይን እና ኮስታሪካ ጋር ተደልድላ የነበረችው ዛምቢያ አንድ ጫወታ አሸንፋ በሁለቱ ተሸንፋ ነው ከምድቡቧ ማለፍ ሳትችል የቀረችው ። በምድብ ስምንት የተመደበችው ሞሮኮ በሶስት ነጥቦች ሶስተኛ ላይ የተቀመጠች ሲሆን ከምድቧ ለማለፍ ሶስተኛውን ጫወታ ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን በርካታ ጎሎች የማስቆጠር ግዴታ ወድቆባታል። ሞሮኮ በመጀመሪያ ጫወታ በጀርመን 5 ለ 0 ከተሸነፈች በኃላ ደቡብ ኮሪያን 1 ለ 0 በማሸነፍ ነው በሶስት ነጥቦች ሶስተኛ ላይ የተቀመጠችው ። ምድቡን ኮሎምቢያ በስድስት ነጥቦች ስትመራ ጀርመን በሶስት ነጥብ እና በአምስት የጎል ክፍያ ሁለተኛ ላይ ተቀምጣለች። በምድብ ሰባት የተደለደለችው ደቡብ አፍሪቃ ከምድቧ ባደረገቻቸው ሁለት ጫወታዎች በአንድ ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች ሲሆን ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ ያላት ተስፋ ለራሷ ከማሸነፍ ባሻገር በምታስቆጥረው የጎል ብዛት እና በጣልያን መሸነፍ ላይ የተመሰረተ ይሆናል። በውድድሩ እንስካሁን የጥምረት አዘጋጇን ሀገር አውስትራሊያን ጨምሮ 9 ሃገራት ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፋቸውን ሲያረጋግጡ ፤ ተጣማሪ አዘጋጇን ኒውዚላንድን ጨምሮ 10 ሃገራት ከመጀመሪያው የዙር ማጣሪያ ተሰናባቾች ሆነዋል። በውድድሩ በርካታ ጎሎችን በማስቆጠር ደግሞ ፤ ጃፓናዊቷ አጥቂ ሂናታ ሚያዛዋ በ4 ጎሎች የከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነቱን እየመራች ትገኛለች። ጃፓን በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ድንቅ የውድድር ጊዜ እያሳለፈች ሲሆን ሶስቱንም የምድብ ቻወታዎች በማሸነፍ አስራስድስቱን መቀላቀል ችላለች።
በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት አንዳንድ የአውሮጳ ኃያላን ክለቦች ለሽርሽር በተጓዙባቸው ሃገራት የወዳጅነት ጫወታቸውን አድርገዋል። ወደ ጃፓን የተጓዘው ማንችስተር ዩናይትድ ትናንት እሁድ ከጀርመኑ ቦሩሽያ ዶርትሙንድ ጋር ያደረገው ጫወታ በዶርትሙንድ 3 ለ 2 አሸናፊነት ተጠናቋል። በጫወታው የተሻለ የኳስ ቁጥጥር የነበራቸው ማንችስተሮች ጎል በማስቆጠር ቀዳሚ የነበሩ ቢሆኑም በአንድ ደቂቃ ልዩነት ውስጥ ተከታትሎ በተቆጠረባቸው ጎሎች ከእረፍት በፊት 2 ለ 1 እንዲሁም ከእረፍት በኋላ ሁለቱም ቡድኖች አንድ አንድ ጎሎች አስቆጥረው ጫወታው 3 ለ 2 ተጠናቋል። ትናንት ደቡብ ኮሪያ ሴዑል ላይ የተገናኙት የእንግሊዙ ማንችስተር ሲቲ እና የስፔይኑ አትሌቲኮ ማድሪድ ጫወታ በአትሌቲኮ የበላይነት ተጠናቋል። የኳስ ቁጥጥሩ የበላይነት የነበራቸው ማንችስተር ሲቲዎች ቢሆኑም አትሌቲኮ ማድሪድ ከእረፍት በኋላ አንድ ጎል አስተናግደው ባስቆጠሯቸው 2 ጎሎች አሸናፊ መሆን ችለዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ወደ ደቡብ ኤዥያዊቷ ሀገር ሲንጋፖር ያቀኑት የእንግሊዞቹ ሊቨርፑል እና ሌስተርሲቲ የወዳጅነት ጫወታ በሊቨርፑል የበላይነት 4 ለ 0 ተጠናቋል። ሊቨርፑል በቅድመ የውድድር ዘመን የወዳጅነት ጫወታዎች ግሩም ጊዜ እያሳለፈ ይገኛል።
በዝውውር ዜና መዳረሻው በውል ያልለየለት የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን እና የፒ ኤስ ጂው አጥቂ ኬይላን ምባፔ ጉዳይ አሁንም መነጋገሪያ ሆኖ እንደቀጠለ ነው። ምባፔ ለክለቡ የዓለም ክብረወሰን የዝውውር ዋጋ እንዲሁም ለእርሱ ለራሱ ቆጥሮ የማይጨርሰው ረብጣ ዶላር በነዳጅ ከበለጸገችው የሳዑዲ አረቢያ ምድር ከበቀለው አልሂላል ክለብ ቢቀርብለትም ፤ አይ ይቅርብኝ ብሏል። ተጫዋቹ ከክለቡ ፒኤስ ጂ በቀረበለት የውል ማደስ አልያም አሁኑኑ ከክለቡ በሽያጭ የመሰናበት የውሳኔ ማሳወቂያ የመጨረሻ ቀን ዛሬ ነው። ይህ ዘገባ እስከ ተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ምባፔ የአልሂላልን ጥያቄ ውድቅ ካደረገ በኋላ ሊቨርፑል ተጫዋቹን በውሰት የመውሰድ ፍላጎት እንዳለው ተሰምቷል። ሊቨርፑል ከፒኤስ ጂ ጋር ተጫዋቹን ለአንድ ዓመት በውሰት በመውሰድ የተቻዋቹንም ሆነ የክለቡን ፍላጎት በአንድ ጠጠር ሁለት ወፍ ላሳካ እችላለሁ ቢልም እስካሁን የተደረሰበት ግልጽ የሆነ ስምምነት ግን የለም። ኬሊያን ምባፔ ከፒኤስ ጂ ጋር የቀረውን የአንድ ዓመት ውል አጠናቆ በነጻ ወደ ማድሪድ የመጓዝ ፍላጎት ነበረው። ፒኤስ ጂ ግን በነጻ አላሰናብትህም ወይ ከኔ ጋር ተጨማሪ ውል ያዝ አልያም አሁኑኑ ልቀቅ እያለው ነው። ምባፔ የዓለማችን ክብረወሰን በነበረው የሳዑዲ አረቢያው ክለብ የቀረበለትን ግብዣ ተቀብሎ ቢሆን ኖሮ ፒኤስ ጂ የ259 ሚሊዮን ፓውንድ ወደ ካዝናው ማስገባት ሲችል ተጫዋቹ በበኩሉ ክለቡ ከሚያገኘው የሽያጭ ገንዘብ ሁለት እጥፍ በላይ በአንድ ዓመት ውስጥ ማጋበስ ያስችለው ነበር ፤ ነበር።
በዓለም የሴቶች ዋንጫ ታሪክ መጀመሪያዋ ሂጃብ ለባሽ ተጫዋች ተከስታለች። ኒውዚላንድ እና አውስትራሊያ በጥምረት እያስተናገዱ በሚገኙት የሴቶች የዓለም ዋንጫ ላይ እየተሰሳተፈች የምትገኘው ሞሮኳዊቷ ኖሃዪላ ቤንዚና በዓለም ዋንጫ የተሳተፈች የመጀመሪያዋ ሂጃብ ለባሽ ተጫዋች ሆናለች ። 3 ቁጥር ለባሿ የ25 ዓመቷ የሞሮኮ ብሄራዊ ብድን ተከላካይ ቤንዚና ለመጀመሪያ ጊዜ በተሰለፈችበት ጫወታ ሞሮኮ ደቡብ ኮሪያን 1 ለ 0 ማሸነፍ ችላለች። ቤኒዚና ለብሳ የተሰለፈችውን አይነት ሰውነትን የሚሸፍን አለባበስ በዓለምአቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ ፈቃድ የተሰጠው በጎርጎርሳውያኑ 2014 ነበር።
ታምራት ዲንሳ
ሸዋዬ ለገሠ