የሞቀ ክርክር የተስተዋለበት የሽብር ክስ ችሎት
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 25 2015የኢትዮጵያ የፈደራል አቃቤ ሕግ በአሸባሪነት ወንጀል የከሰሳቸዉን የ51 ተጠርጣሪዎችን ጉዳይ የሚመለከተዉ ፍርድ ቤት የዛሬ ችሎት ተቋረጠ።የመገናኛ ዘዴ ባለሙያዎችን ጨምሮ በአሸባሪነት የተከሰሱት ተጠርጣሪዎች የችሎቱ የመሐል ዳኛ «በአግባቡ አይዳኙንም» በማለት በሌላ እንዲተኩ ጠንካራ ተቃዉሞ አሰምተዋል።ተከሳሾቹ አቤቱታቸዉን በፅሑፍ ለችሎቱ እንዲያቀርቡ ዳኞች ቢጠይቁም ተከሳሾች «የመደመጥ መብታችን ይከበር» በማለት አበክረዉ በመቃወማቸዉ የዛሬዉ ሒደት ተቋርጦ ለጥቅምት 15፣2016 ተቀጥሯል።
በሽብር የተከሰሱትን 51 ሰዎች ጉዳይ የሚመለከተው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ የፀረ ሽብር እና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ችሎት ዛሬ ሲሰየም ፖሊስ የተከሳሽ ቤተሰቦችን እና ሌሎች እድምተኞችን እንዳይታደሙ ከልክሎ ነበር። ታዳሚዎቹ ከዚህ በፊት በነበረው ችሎት ያሳዩት የሥነ ሥርዓት ጥሰት ለዚህ ምክንያት ነው በሚል ችሎቱም ይህንን እርምጃ ተቀብሎት ነበር።
ይሁንና ተከሳሾችና ጠበቆቻቸው ይህ ውሳኔ ችሎቱ "በዝግ ችሎት እንዲሰማ የተወሰነ አድርገን እንወስደዋለን" በሚል ሰፊ ክርክር አድርገዋል። የተከሳሾች ጠበቆችም ችሎቱ "ልዩ ባህሪ ያለው ችሎት ነው" የሚል መከራከሪያ አንስተዋል። ባለፈው ችሎት ላይ ሁከት እንዲፈጠር ሆን ብለው በእድምተኝነት በመግባት ተጽእኖ ለማድረግ የገቡ ሰዎች ስለመኖራቸው ከተከሳሾች መረጃ ደርሶናል በሚልም ጠበቆች ተከራክረዋል።
ይህንን ተከትሎ ዳኞቹ የመጀመርያ ውሳኔያቸውን አሻሽለው እድምተኞቹ ወደ ችሎቱ እንዲገቡ ከመፍቀዳቸው በፊት ችሎቱ እንዲከበር እና ሕግ እኩል እንዲፈፀም ጥብቅ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል። ችሎቱ ዝግ ሊባል የማይችል መሆኑንና ልዩ ባህሪ ያለው ችሎት ነው የሚያስብለው አንዳችም ምክንያት እንደሌለም ዳኞቹ ገልፀዋል።
በዛሬው ችሎት የተከሳሾችን ምስል በመጠቀም እንደ ጥፋተኛ አድርገው ዘግበዋል ከተባሉትና እርምት እንዲያደርጉ ትእዛዝ ከተሰጣቸው መንግሥት ከሚቆጣጠራቸው መገናኛ ብዙኃን መካከል አራት መገናኛ ብዙኃን ለፍርድ ቤቱ ትእዛዝ ተገቢ ምላሽ ሰጥተዋል ተብሏል። ልሌላው የችሎቱ ዋነኛ ክስተት የነበረው ከችሎቱ እንዲነሱ አቤቱታ የቀረበባቸው የመሃል ዳኛው ጉዳይ ሲሆን፣ ይህም ጎላ ያለ ክርክር አስነስቷል።
"ሦስቱ ዳኞች እየዳኙን ነው ብለን አናምንም" ያሉት አቤቱታ አቅራቢዎቹ ተከሳሾች የዳኞች መቀያየር መኖሩን በመጥቀስ በችሎቱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንደፈጠረ እና በተለይ የመሃል ዳኛው "ዳኝተውን ፍትሕ እናገኛለን የሚል እምነት የለንም" በሚል ከፍተኛ ቅሬታ ከተከሳሾች ቀርቦባቸዋል።
በዚህ ሂደት ተከሳሾቹ ዳኛው ላይ ያለንን አቤቱታ በንባብ እናቅርብ በሚል አጥብቀው የተከራከሩ ሲሆን ችሎቱ ዳኛ ይነሳልን ብሎ መጠየቅ ወይም አቤቱታ ማቅረብ ሕገ መንግሥታዊ መብት መሆኑን በመጥቀስ ሆኖም ግን ጥያቃው በጽሁፍ ብቻ እንዲቀርብ በሚል ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ይሁንና ተከሳሾች አቤቱታችንን መገናኛ ብዙኃንን ጨምሮ የችሎቱ እድምተኞች እንዲሰሙን እንፈልጋለን በሚል የመደመጥ ሕገ መንግሥታዊ መብታችን ሊገደብ አይገባም ፣ አቤቱታችንን በንባብ እንዳናቀርብ የተከለከልንበት ምክንያትም ይነገረን በሚል ተደጋግሞ ጎልቶ የተነሳ ጥያቄ ተጠይቋል። ይህንን ሲያደርጉ ሙሉ በሙለ ቆመው የናበሩት ተከሳሾች ከችሎቱ እንዲቀመጡ እና ጉዳያቸውን እንዲያስረዱ ቢጠየቁም ቆመው ሀሳብ ሲያቀርቡ ተስተውሏል። ችሎቱ በበኩሉ ውሳኔውን በማጽናት "ችሎቱን ለማቋረጥ እንገደዳለን" በማለት በዋናነት የክስ መቃወሚያ ለማድመጥ የተሰየመውን ችሎት ትዕዛዝ በመስጠት የችሎቱን ውሎ ቋጭቶታል።
ችሎቱ ክስ ቀርቦባቸው እስካሁን ችሎት ያልቀረቡ ሰዎች በፖሊስ ተይዘው እንዲቀርበ ፣ ሌሎች አቤቱታዎች ካሉ በጽ/ቤት በኩል እንዲቀርቡ፣ የተነሱ የመብት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲሰጣቸው፣ በሰብሳቢ ዳኛው ላይ በቀረበባቸው አቤቱታ እና በሌሎችም ጉዳዩ ላይ ተገቢ ነው የሚለውም ትዕዛዝ ለመስጠት ለጥቅምት 15 ቀን 2016 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል።
51ዱ ተከሳሾቹ የፖለቲካ እና የርዕዮት አላማን ለማራማድ በማሰብ የሽብር ድርጊት ፈጽመዋል በሚል በዐቃቤ ሕግ ክስ የቀረበባቸው ናቸው።
ሰሎሞን ሙጪ
ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዬ ለገሰ