1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የበርበራ ወደብ፦ የኢትዮጵያ ወቅታዊ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴና የአፍሪቃው ቀንድ

እሑድ፣ ጥር 5 2016

ወትሮም እዚህም እዚያም በተለያዩ ግጭቶችና ሽኩቻዎች የሚታመሰው የምሥራቅ አፍሪቃ፥ በተለይም የአፍሪቃው ቀንድ ከሰሞኑ በብርቱ ተነቃንቋል ። ራስዋን የሶማሊላንድ ሪፐብሊክ ብላ የምትጠራው ሶማሊላንድን አስቦርቆ በኢትዮጵያ መነጋገሪያ ርእስ መዟል። እጅግ ስልታዊው የቀይ ባሕር እና የኤደን ባሕረሠላጤ የዓለምን ትኩረት ስቧል ። ሙሉ ውይይቱ ከታች አለ።

https://p.dw.com/p/4bBJO
የበርበራ ወደብ፤ ሶማሊላንድ
ራስዋን የሶማሊላንድ ሪፐብሊክ ብላ የምትጠራው ሶማሊላንድ እና ኢትዮጵያ በወደብ አጠቃቀም የመግባቢያ ሰነድ መፈረማቸው ሶማሊያን እጅግ አስቆጥቷል ። የበርበራ ወደብ፤ ሶማሊላንድምስል Jonas Gerding/DW

ጉዳዩ የሶማሊያን ፌዴራል ሪፐብሊክን ከኢትዮጵያ አፋጧል

ወትሮም እዚህም እዚያም በተለያዩ ግጭቶች እና ሽኩቻዎች የሚታመሰው የምሥራቅ አፍሪቃ፥ በተለይም የአፍሪቃው ቀንድ ከሰሞኑ በብርቱ ተነቃንቋል ። ራስዋን የሶማሊላንድ ሪፐብሊክ ብላ የምትጠራው ሶማሊላንድን አስቦርቆ በኢትዮጵያ መነጋገሪያ ርእስ መዟል ። የሶማሊያን ፌዴራል ሪፐብሊክን ከኢትዮጵያ አፋጧል ። ጅቡቲን ለቀናት ጸጥ አድርጎ ቆይቷል ። ኤርትራን ለምክክር ጠረጴዛ አስቧል ። ሱዳንን አስቆጥቶ ከኬንያ አፋጧል ። «በሕዳሴው ግድብ» ግንባታ ቀን ስትጠብቅ የቆየችው ግብጽን ከሩቅ ጠርቷል ። የዩናይትድ ስቴትስ ወዳጆችን የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶችን እና ሣዑዲ ዓረቢያን በተለያየ ጎራ አሰልፎ ወደ አፍሪቃ ቀንድ ይበልጥ አንደርድሯል ። አውሮጳን አሳስቧል ።

ድንገት ይኸን ሁሉ ትርምስ ግን ምን ፈጠረው?  

በእርግጥ በዚህ ሁሉ መሀል አንድ ጎልቶ የወጣ ጉዳይ አለ ። ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ካልተሰጣት ራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋ የ50 ዓመት የወደብ ሊዝ አጠቃቀምን በተመለከተ የፈረመችው የመግባቢያ ሰነድ። የውይይታችን መነሻ ነው ። ዋነኛ መነጋገሪያችን ግን፦ እጅግ ስልታዊው የቀይ ባሕር እና የኤደን ባሕረሠላጤ በሚገኝበት በአፍሪቃው ቀንድ የተከሰተው ትርምስ ሰበቡ እና ዳፋው ነው ። ማን ከማን ጋ ተሰልፏል? ፍጥጫውስ ወዴት እያመራ ነው? ዐቢይ ትኩረታችን ነው ።

በውይይቱ 4 እንግዶች ተሳታፊ ናቸው። እንግዶቻችን ራሳቸውን ያስተዋውቃሉ።

  1. ተሻለ ሠርቦ (/)፦ በሶማሊያ ከፍተኛ ዲፕሎማት ሆነው ያገለገሉ
  2. አቶ ዩሱፍ ያሲን፦የአፍሪቃ ቀንድ ጉዳይ ተንታኝ
  3. አቶ ዳያሞ ዳሌ፦ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሞያ
  4. አቶ አብዱርሃማን ሳይድ፦የአፍሪቃ ቀንድ ጉዳይ ተንታኝ ናቸው ።

በዚህ ውይይት ተሳታፊ እንዲሆኑ ለጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት፤ ለመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሠ ቱሉ (ዶ/ር) እንዲሁም ለምክትላቸው ሠላማዊት ካሳ በዶይቸ ቬለ በኩል የላክነው ይፋዊ የኢሜል ግብዣ ውይይቱን እስካደረግንበት ጊዜ ድረስ ምላሽ አላገኘም ።

የአፍሪቃው ቀንድ ፖለቲካ ተነቃንቋል ። ከሰሞኑ ከተከሰቱ ጉዳዮች መካከል ጥቂቱን ብንጠቅስ እንኳ፦ ኢትዮጵያ የበርበራ ወደብን በተመለከተ የመግባቢያ ሰነድ ላይ መፈረሟ ሶማሊላንድ ግማደ አካሌ ናት የምትለው ጎረቤት ሶማሊያን እጅግ አስቆጥቶ ሰነዱን «ሙሉ ለሙሉ ውድቅ» የሚያደርግ ሕግ እንድታጸድቅ አድርጓታል ያም ብቻ አይደለም ፕሬዚደንቷ በፍጥነት ወደ ኤርትራ አቅንተው ከኤርትራው አቻቸው ጋ ለሁለት ቀናት መክረዋል ። ከግብጽ እና ከሌሎች ሃገራት ጋርም ይበልጥ በቅርበት ለመተባበር መነጋገራቸው ተገልጿል ። ግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚንስትሯን ኤርትራ ልካ መክራለች ።

 ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አሕመድ እና የሶማሊላንድ ፕሬዚደንት ሙሴ ቢሂ
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አሕመድ እና ራሷን የሶማሊላንድ ሪፐብሊክ ብላ የምትጠራው ሶማሊላንድ ፕሬዚደንት ሙሴ ቢሂ የመግባቢያ ሰነድ ፊርማ ባደረጉበት ወቅት ምስል TIKSA NEGERI/REUTERS

በአፍሪቃ ቀንድ ምን እየሆነ ነው?

የሱዳን አማጺ የፈጥኖ ደራሹ ኃይል አዣዥ ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን (ሐምዲቲ) ዳግሎ የሱዳን የሲቢል ዴሞክራሲያዊ ኃይላት ከተባለዉ ስብስብ መሪና ከቀድሞዉ ጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሐምዶክ ጋር ባለፈዉ ሳምንት አዲስ አበባ ዉስጥ መነጋገራቸዉ የጄኔራል አል ቡርሐንን ወገን ክፉኛ አስቆጥቷል። የአማጺ መሪው በተለይ ከኬንያ ፕሬዚደንት ዊሊያም ሩቶ ጋ ያደረጉት ንግግር የሱዳን ጦር ኃይል አዛዥ ጄኔራል አብዱልፈታሕ አል ቡርሐን አምባሳደራቸውን ከኬንያ ወደ ሱዳን በአስቸኳይ እንዲጠሩ አድርጓል። የሱዳን የርስበርስ ጦርነትን ለማስቆም የተፋላሚ ኃይላት መሪዎች ፊት ለፊት ተገናኝተዉ ይነጋገራሉ የሚለዉ ተስፋንም ያጠወለገ ይመስላል ።  

ለመሆኑ በአፍሪቃ ቀንድ ኢትዮጵያን ጨምሮ የኃይል አሰላለፉ ምን ይመስላል? ከአፍሪቃ ውጪ ያሉ ሃገራት ቀጣናው ላይ ፍላጎታቸውን በማንጸባረቅ እና ተጽእኖዋቸውን በማሳረፉ ረገድ እነማንስ ናቸው በዋናነት የሚጠቀሱት?

ሙሉ ውይይቱን ከድምፅ ማእቀፉ ማድመጥ ይቻላል ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ ሥዩም Mantegaftot Sileshi ዜና አዘጋጅ፤ መርኃ ግብር መሪ፤ የሳምንታዊ ስፖርት አዘጋጅ ነው፥ በአጭር ፊልም የበርካታ ዓለም አቀፍ ተሸላሚው ማንተጋፍቶት የቪዲዮ ዘገባዎችንም ያዘጋጃል።@manti