የነሐሴ 1 ቀን 2015 ዓ/ም የስፖርት ዝግጅት
ሰኞ፣ ነሐሴ 1 2015
የስፖርት ዝግጅታችን በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት የተከናወኑ ዐበይት ስፖርታዊ ክንዋኔዎች ይዳሰሳሉ ።
ሃንጋሪ ቡዳፔስት የምታስተናግደው የ2023 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሊጀመር ከሁለት ሳምንታት ያነሰ ጊዜ ብቻ ቀርቶታል ። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ምን አይነት ዝግጅት እያደረጉ ይሆን ከአዲስ አበባ እንጠይቃለን ። በታንዛኒያ አዘጋጅነት ለሁለት ሳምንታት ገደማ ሲካሄድ በነበረው የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪቃ ሃገራት ሴካፋ የሴቶች ከ18 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር ላይ ተሳታፊ የነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን 3ኛ ወጥቶ ተመልሷል። ለሽርሽር ወደ አሜሪካ የተጓዘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ያደረጋቸውን ሁለት የወዳጅነት ጫወታዎች ማሸነፍ ችሏል። ብሔራዊ ቡድን ከነ ማን ጋር ተጫውቶ አሸነፈ የእግር ኳስ ደረጃቸውስ በዝግጅታችን ይዳሰሳል። የዓለም የሴቶች እግር ኳስ ዋንጫ የተጠበቀው ቀርቶ ያልተጠበቀውን እያስተናገደ የሩብ ፍጻሜ ተፈላማዊችን እየለየ ነው። የ4 ጊዜ የዓለም ዋንጫ አሸናፊው የአሜሪካ ብሔራዊ ቡድን ከጥሎ ማለፍ ሳይችል ቀርቷል። በእንግሊዝ ሲጠበቅ የነበረው የኮሚኒቲ ሼልድ ዋንጫ በአርሴናል አሸናፊነት ተጠናቋል።
የአውሮጳ ሃያላን ሊጎች ውድድሮቻቸውን ሊጀምሩ እየተዘጋጁ ነው። በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት የቅድመ ውድድር ዘመን ጫወታዎችም ተስተናግደዋል።
በአትሌቲክስ ዜና ስንጀምር ሃንጋሪ ቡዳፔስት የምታስተናግደው 2023 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከሁለት ሳምንታት ያነሰ ጊዜ ብቻ ቀርቶታል። ከነሐሴ 13 እስከ ነሐሴ 21 ቀን 2015 ዓ/ም በሚቆየው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በመላው ዓለም ስመ ጥር አትሌቶች እና ሃገራት ዝግጅት እያደረጉ ነው። ከኦሎምፒክ በመቀጠል ትልቅ ግምት የሚሰጠው እና በየሁለት ዓመቱ በሚደረገው በዚሁ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ተሳታፊ ትሆናለች ። ኢትዮጵያ በውድድሩ እንደ ሀገር ትልቅ ግምት የሚሰጣት ከመሆኑ አንጻር የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑም ሆነ አትሌቶቹ ምን አይነት ዝግጅት እያደረጉ ይሆን ስንል ጠይቀናል። የአዲስ አበባው ተባባሪ ዘጋቢያችን ኦምና ታደለ በዚሁ ጉዳይ ላይ መረጃዎችን አሰባስቧል አጭር የስልክ ቆይታ አድርገናል።
በሌላ የአትሌቲክስ ዜና ትናንት እሁድ በአሜሪካ ኬፕ ኤልዛቤዝ በተካሄደ የ10 ኪ,ሜ የሩጫ ውድድር አዲሱ ይሁኔ አሸነፈ ። አዲሱ ርቀቱን ለመጨረስ 27;56 ሰከንድ ወስዶበታል። በውድድሩ ሌላው የሀገሩ ልጅ ሙክታር ኢድሪስ 3ኛ ሆኗል። አሜሪካዊው ኮነር ማንትስ ሁለተኛ ሆኗል። በሴቶች ምድብ በተካሄደው ተመሳሳይ ርቀት ኢትዮጵያዊቷ ፎቲን ተስፋይ ሁለተኛ ወጥታለች። ውድድሩን ኬንያዊቷ ሄለን ኦብሪ አሸንፋለች ። ሄለን ኦብሪ ርቀቱን ለመጨረስ 31 ደቂቃ ከ37 ሰከንድ ወስዶባታል ።
ወደ እግር ኳስ መረጃዎች ስንሸጋገር ከሀገር ቤት እንጀምራለን። በቅርቡ በታንዛንያ አስተናጋጅነት ሲካሄድ በሰነበተው የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪቃ ሃገራት ሴካፋ የሴቶች ከ18 ዓመት በታች የእግር ኳስ ሻምፒዮና ላይ ተሳታፊ የነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን 3ኛ ወጥቶ ተመልሷል። ብሔራዊ ቡድኑ ያደረጋቸውን ካደረጋቸው አራት ጫወታዎች ሁለቱን ሲያሸንፍ በሁለቱ ሽንፈት ደርሶበታል። ቡድኑ ባደረጋቸው ጨዋታዎች የመጀመሪያውን ሁለት ጫወታዎች በአዘጋጇ ሀገር ታንዛኒያ 2 ለ 0 እንዲሁም ቀጥሎ በዩጋንዳ 1 ለ 0 ሽንፈት ደርሶበታል። ነገር ግን በሶስተኛው ጫወታ የብሩንዲ አቻውን 2ለ 0 እንዲሁም ዛንዚባርን 6ለ1 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት በማሸነፍ ውድድሩን በሶስተኛነት ማጠናቀቅ ችሏል። የቡድኑ አጥቂ እሙሽ ዳንኤል 5 ጎሎችን በማስቆጠር የሻምፒዮናው ከፍተና ጎል አስቆጣሪ ሆና ተመልሳለች። በውድድሩ አዘጋጇ ሀገር ታንዛኒያ አሸናፊ ሆና ዋንቻ ስታነሳ ዩጋንዳ ሁለተኛ ወጥታለች።
የወዳጅነት ጫወታዎችን ለማድረግ ወደ አሜሪካ የተጓዘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በእስካሁን ቆይታው ሁለት ጫወታዎችን አድርጎ ሁለቱንም ማሸነፍ ችሏል። የብሔራዊ ቡድኑ የመጀመሪያው ጫወታውን ከደቡብ አሜሪካዊቷ ሀገር ጉያና ጋር ያደረገ ሲሆን 2 ለ 0 ማሸነፍ ችሏል። ጉያና በዓለም የእግር ኳስ ሰንጠረዥ ከኢትዮጵያ 27 ደረጃዎችን ዝቅ ብላ በ169ኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሀገር ናት ። ቡድኑ በሁለተኛው ጫወታው ገና ከተመሰረተ አምስት ዓመታትን ብቻ ያስቆጠረው እና ተቀማጭነቱን ቨርጂኒያ ሊዝበርግ አድርጎ በአሜሪካ ሻምፒየን ሺፕ የሚወዳደረውን የሉዶን ዩናይትድ ክለብን ነበር የገጠመው ። በጫወታው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን 4 ለ 2 ማሸነፍ ችሏል። ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጎሎቹን ሱራፌል ዳኛቸው፣ ሽመልስ በቀለ፣ አስቻለው ታመነ፣ እና ይሁን እንደሻው) ማስቆጠር ችለዋል። ሉዶን ዩናይትድ በአሜሪካ የቻምፒዮን ሺፕ ምስራቃዊ ምድብ ውስጥ ካሉት 12 ክለቦች 11ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ክለብ ነው ። በተያያዘ ወደ አሜሪካ ከተጓዘው የብሔራዊ ቡድኑ አባላት መካከል ሁለቱ የስነምግባር ጥሰት መፈጸማቸውን ተከትሎ የቆይታ ጊዜአቸውን ሳያጠናቅቁ ወደ ሃገር ቤት እንዲመለሱ መደረጉን ከፌዴሬሽኑ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
አውስትራሊያ እና ኒውዚላንድ በጋራ እያስተናገዱ የሚገኘው የሴቶች የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ የሩብ ፍጻሜ ተፋላሚ ሃገራትን እየለየ ሲሆን የ4 ጊዜ የዋንጫ አሸናፊዋን አሜሪካን አሰናብቷል። በውድድሩ የጥሎ ማለፍ ፍልሚያዎች ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ እየተከናወኑ ሲሆን ሩብ ፍጻሜውን የተቀላቀሉ 6 ሀገራት ተለይተዋል። ቅዳሜ ዕለት በተከናወኙ ጫወታዎች ስፔን ስዊዘርላንድን 5 ለ 1 በሆነ ሰፊ የጎል ልዩነት ስታሸንፍ ጃፓን ኖርዌይን 3 ለ 1 አሸንፋለች። በተመሳሳይ እሁድ ዕለት በተካሄዱ ሁለት ጫወታዎች ኔዘርላንድስ ደቡብ አፍሪቃን 2 ለ 0 እንዲሁም ስዊዲን እና አሜሪካ መደበኛ የጫወታ ጊዜአቸውን 0 ለ 0 አጠናቀው ወደ መለያ ምት ማምራታቸውን ተከትሎ ሰዊዲን አሜሪካን 5 ለ 4 አሸንፋ ሩብ ፍጻሜውን መቀላቀሏን አረጋግጣለች። ዛሬ በተከናወኑ ሁለት ጫወታዎች እንግሊዝ ናይጄሪያን በመለያ ምት 4 ለ 2 እንዲሁም አዘጋጇ ሀገር አውስትራሊያ ዴንማርክን 2 ለ 0 አሸንፋ የሩብ ፍጻሜ ተሳትፏቸውን አረጋግጠዋል። ናይጄሪያ ከአውሮጳ ሻምፒዮናዋ ጋር ብርቱ ፉክክር ማድረግ ብትችልም ጥሎ ማለፉ ላይ ቀርታለች። ቀሪ ሁለት የጥሎ ማለፍ ጫወታዎች በነገው ዕለት ሲከናወኑ ኮሎምቢያ ከጀማይካ እንዲሁም ፈረንሳይ ከአፍሪቃዊቷ ሞሮኮ ጋር የሚያደርጓቸው ጫወታዎች ተጠባቂ ናቸው ።
ሲጠበቅ የነበረው እና የፕሪምየር ሊጉን አሸናፊ ከአርሴናል ያገናኘው የእንግሊዝ ኮሙኒቲ ሼልድ የዋንጫ ፍልሚያ በአርሴናል አሸናፊነት ተደምድሟል። አርሴናል በጫወታው ከመመራት አንስቶ በባከነ ሰዓት አቻ የምታደርገውን በትሮሳርድ አማካኝነት አግኝቷል ። የማንችስተር ሲቲን ጎል በ77ኛው ደቂቃ ኮል ፓልመር አስቆጥሯል። በመጨረሻም አሸናፊውን ለመለየት ወደ መለያ ምት ማምራታቸውን ተከትሎ አርሴናል 4 ለ 2 አሸንፎ የ2023 / 2014 የውድድር ዘመንን በዋንጫ አሟሽቷል ። ከማንችስተር ሲቲ ወገን ኬቪን ዴቡሩኔ እና ሮድሪጎ የመለያ ምቶቹን ሳይጠቀሙበት የቀሩ ናቸው።
በመጨረሻም የዓለም እግር ኳስ አፍቃሪያን በጉጉት የሚጠብቋቸው የአውሮጳ ኃያላን የ2023 / 24 የውድድር ዘመን በቀጣዮቹ ሳምንታት እንደሚጀመሩ ይጠበቃል። የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የፊታችን አርብ የሊጉን አሸናፊ ማንችስተር ሲቲ ከሜዳው ውጭ ተጉዞ በርንሌይን በሚገጥምበት ጫወታ አንድ ተብሎ ይጀመራል። በተከታዩ ቀን ቅዳሜ ስድስት ጫወታዎች ሲደረጉ አርሴናል ከኖቲንግሃም ፎረስት እንዲሁም ኒውካስል ዩናይትድ ከአስቶን ቪላ የሚያደርጓቸው የመጀመሪያ ጫወታዎች ተጠባቂ ናቸው። እሁድ ከሚደረጉት ጫወታዎች ደግሞ ቼልሲ በሜዳው ሊቨርፑልን የሚያስተናግድበት ጫወታም እንዲሁ ይጠበቃል። የስፔን ላሊጋም በተመሳሳይ የፊታችን አርብ ሲጀመር ሴቪያ ከቫሌንሽያ እንዲሁም የፊታችን ቅዳሜ ሪያል ማድሪድ ከሜዳው ውጭ አትሌቲክ ክለብን የሚገጥሙበት ጫወታዎች ከውድድሩ የመክፈቻ ጫወታዎች ተጠቃሾች ናቸው። የፈረንሳይ ሊግ አንድም እንዲሁ በተመሳሳይ የፊታችን አርብ የመጀመሪያ ቻወታዎች ሲደረጉ ኒሴ ከሎስክ እንዲሁም ማርሴ ከሬምስ ይጋጠማሉ ። የጀርመን ቡንደስ ሊጋ ውድድሮች ደግሞ በቀጣዩ ሳምንት የመጨረሻ ቀናት እንደሚጀመር የወጣው መርኃ ግብር ያመለክታል።
ታምራት ዲንሳ
እሸቴ በቀለ