የአረቦች ጠብ መዘዝ
ሰኞ፣ ሰኔ 12 2009ከሰዎስት ዓመት በፊት ሳዑዲ አረቢያ የምትመራቸዉ የዓረብ መንግሥታት ጦር የየመን ሁቲ አማፂያንን ይዞታ በጄት መደብደብ ሲጀምር የፖለቲካ ተንታኝ ዩሱፍ ያሲንን «የመንን ማጥፋት የጀመረዉ ጦርነት ቀይ ባሕርን ተሻግሮ አፍሪቃ ቀንድን ያሰጋ ይሆን?» ብዬ ጠይቄያቸዉ ነበር።«መላ ካልተበጀለት» መለሱ የቀድሞዉ ዲፕሎማት «የት ይቀራል።»ያኔ የአረብ-ፋርሶች ሽሚያ መስሎ ነበር።ዛሬ የአረብ-አረቦች ጠብ ነዉ-ምክንያቱ።የሪያድ-ማናማ፤ አቡዳቢ-ካይሮ እና የዶሐ ቁርቁስ።ዳፋዉ የኤርትራ-ጅቡቲን፤ የኤርትራ-ኢትዮጵያን፤ የኢትዮጵያ ግብፅን የተዳፈነ ቁርሾ ይቀሰቅስ ይሆን?
በኤርትራ ጉዳይ ላይ በተከታታይ የሚዘግበዉ ፈረንሳዊ ጋዜጠኛ ሊዮናርድ ቪንሴንት በ2013 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) «ዘ-አትላንቲክ ለተሰኘዉ አምደ-መረብ በሰጠዉ መግለጫ «ኤትርትራን ለማሳመን ፈቃዱ እና ስልቱ ያላት ብቸኛ ሐገር አለ «ቀጠር ነች።»
ጋዜጠኛዉ ያለዉን ለማለቱ ምክንያቱ እዉነት ብዙም ነዉ።ጥቂቱን እንጥቀስ።የጅቡቲ እና የኤርትራን የድንበር ዉዝግብ ለማብረድ የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ)፤ የአፍሪቃ ሕብረት፤የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፤ ምናልባት ሌሎችም ማሕበራት፤ ድርጅቶችና መንግሥታት እንደ ዲፕሎማሲዉ ወግ ካስመራ-ጅቡቲ መለስ ቀለስ ማለታቸዉ አልቀረም ነበር።ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂንና ፕሬዝደንት ኢስማኤል ዑመር ጌሌን የሠላም ዉል ያፈራረሙት ግን ቀጠሮች ነበሩ።
ጥቅምት 2012 የፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ልዩ ጄት አብራሪ አዉሮፕላኒቱን ጂዛን ሳዑዲ አረቢያ አሳርፎ ጥገኝነት ጠየቀ።በስድስተኛ ወሩ ሚያዚያ ፕሬዝደንት ኢሳያስ ወደ ዶሐ ለመጓዝ ሲነሱ አዉሮፕላን አልነበራቸዉም።በምን ይብረሩ? አሚር ሐማድ ቢን ኸሊፋ አል ሳኒ የግል ጄት ላኩላቸዉ።ፕሬዝደንት ኢሳያስ ዶሐ ደርሰዉ በተመለሱ በሁለተኛ ወሩ ሰኔ ቀጠር፤ ደሕላክ ከቢር በተባለዉ የኤርትራ ደሴት ላይ የሐገር ጎብኚዎች ማዕከላትን ለመገንባት 115 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር መመደቧን አስታወቀች።
ቀጠር በዚያዉ ሰሞን ኤርትራ ዉስጥ ማዕድን የሚያወጣዉ የካንዳ ኩባንያን የአንድ ቢሊዮን ዶላር ይዞታን ለመግዛት ከኩባንያዉ ጋር ድርድር ጀምራም ነበር።ከሽምግልና እስከ ግል ወዳጅነት፤ ከመዋዕለ ነዋይ ፍሰት እስከ ዲፕሎማሲ ድጋፍ የነበረዉ የዶኽ-አስመሮች ጥብቅ ወዳጅነት ካለፈዉ ሳምንት ጀምሮ ትዝታ ነዉ።ምክንያት የአረቦች ጠብ።ጠቡ የፖለቲካ ተንታኝ የሱፍ ያሲን እንደሚሉት አዲስ የኃይል አሰላለፍ አስከትሏል።
ሳዑዲ አረቢያ፤ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች፤ ባሕሬን፤ ግብፅና የመን በቀጠር ላይ የጣሉት የዲፕሎማሲ፤ ያየር፤የየብስና የባሕር መስመር እገዳን ኤርትራ ደግፋለች።ጅቡቲም ልክ እንደ ኤርትራ የሳዑዲ አረቢያዉን ጎራ ተቀይጣለች።
ከኤርትራ ጋር የገጠመችዉን ደም አፋሳሽ ዉዝግብ በጦርነት የለም፤ ሠላምም የለም ዓይነት መርሕ ያዳፈነችዉ ኢትዮጵያ፤ በቅጡ ያልጠናችዉ ሶማሊያ እና ከቀጠርም፤ ከሳዑዲ አረቢያም ጋር ጠንካራ ግንኙነት ያላት ሱዳን «የኩዌቱ አሚር የጀመሩትን የሽምግልና ጥረት እንደግፋለን በማለት» በገለልተኝነት ለመቆም ሞክረዋል።
የብራስልሱ ወኪላችን ገበያዉ ንጉሴ እንደሚለዉ ግን የአረቦቹ ጠብ ወትሮም በየዉሳጣቸዉ ወይም አንዳቸዉ ከሌላቸዉ ግጭትና ቁርቁስ ያልተለያቸዉን የአፍሪቃ ቀንድ ሐገራትን የተወነካከረ ሠላም ማበጡ አይቀርም።
ጠመንጃ ያማዘዘዉን ጠባቸዉ በቀጠሮች ሽምግልና የበረደዉ፤ አዋሳኝ ድንበራቸዉ በቀጠር ጦር የሚጠበቀዉ፤ ከቀጠር ጠቀም ያለ ገንዘብ የሚያገኙት ኤርትራና ጅቡቲ በጣም ለተሻለ ጥቅም ከቀጠር ባላጋራዎች ጎን መሠለፋቸዉ የዶሐ መሪዎችን ለአፀፋ እርምጃ መገፋፈቱ በርግጥ አያስደንቅም።የቀጠር የመጀመሪያ እርምጃ ጅቡቲና ኤርትራ አወዛጋቢ ድንበር ዱሜራ ኮረብታና ደሴት ላይ የሰፈረዉን ሠላም አስከባሪ ሠራዊቷን ወደ ሐገሯ መመለስ ነበር።450 የሚገመተዉ የትንሺቱ ሐገር ሠራዊት ባለፈዉ ማክሰኞና ሮብ አካባቢዉን ለቅቆ ወጣ።የቀጠር ጦር የለቀቀዉን አካባቢ የኤርትራ ሠራዊት ተቆጣጥሮታል መባሉ ጅቡቲን ማመልከቻዋን ይዛ የአፍሪቃ ሕብረትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ደጅ እድትጠና አስገድዷታል።
የአፍሪቃ ሕብረት ሁለቱ ሐገራት እንዲታገሱ ተማፅኗል።የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ዛሬ በጉዳዩ ላይ እየተነጋገረበት ነዉ።ግብፅ እና ሳዑዲ አረቢያ በበኩላቸዉ የቀጠር ጦር በለቀቀዉ ሥልታዊ ግዛት የየራሳቸዉን ጦር ለማስፈር መፈቅዳቸዉ እየተነገረ ነዉ።ከመነገር አልፎ ግን ሁለቱ መንግሥታት በይፋ አላረጋገጡም።ተረጋገጠም አልተረጋገጠ የፖለቲካ ተንታኝ ዩሱፍ ያሲን እንደሚሉት መዘዙ አዲስ አበባንም መነካካቱ አይቀርም።
የአፍሪቃ ሕብረት ኮሚሽን ፕሬዝደንት ሙሳ ፋኪ መሐመት ጅቡቲ እና ኤርትራ ጠቡን ከሚያባብስ እርምጃ እንዲታቀቡ አደራ ብለዋል።መሐሜት ዛሬ ባሰራጩት መልዕክት ድርጅታቸዉ አዋዛጋቢዉን ድንበር የሚጎበኝ ቡድን ሰሞኑን እንደሚልክ አስታዉቋልም።የብራስልሱ ወኪላችን ገበያዉ ንጉሴ እንደሚለዉ ግን ጉዳዩ ከዲፕሎማሲ ሽንገላ ባለፍ ጥብቅ ጥንቃቄ ካልተደረገበት መዘዙ ኢትዮጵያንም መንካቱ አይቀርም።
የአረቦቹ ጠብ እንደ ጅቡቲ-ኤርትራዉ ሁሉ የሶማሌዎችን ልዩነት ያቀጣጠለ መስሏል።ሶማሊያ ሞቃዲሾ ላይ የሶማሊያ ፌደራላዊ ሪፐብሊክ የሚባል አንድ መንግሥት አላት።ሐርጌሳ ላይ የሶማሊላንድ ሪፐብሊክ የሚባል ሌላ መንግሥት አላት።ጋርዌ ላይ የፑንት ላንድ ራስገዝ የሚባል መስተዳድር አላት።
ዓለም አቀፍ ዕዉቅና ያለዉ የሞቃዲሾዉ መንግሥት በሳዑዲ አረቢያ የሚመራዉን ጎራ እንዲደግፍ ሪያዶች 80 ሚሊዮን ዶላር ጉርሻ ሊሰጡት ቃል ገብተዉለት ነበር ይባላል።ፕሬዝደንት መሐመድ አብዱላሒ መሐመድ (ፎርማጆ) ግን እንደ ኢትዮጵያና ሱዳን ሁሉ ገለልተንኘትን ነዉ-የመረጡት።
የሞቃዲሾዉ የሶማሊያ ፌደራል ሪፐብሊክ ከሚያስተናብራቸዉ ግዛቶች አንዷ ፑንት ላንድ ግን የሞቃዲሾ አቋምን ተቃርና ከነሳዑዲ አረቢያ ጎን ቆማለች።ሶማሊላንድን ከአዲስ አበባ እስከ ካይሮ፤ ከለንደን እስከ ዋሽግተን የሚገኙ መንግሥታት በይፋ እንደመንግሥት እዉቅና አንሰጥም ይሏታል።ሥልታዊ መሬት፤ አየር፤ ወደቧን ሲፈልጉ ግን እንደመንግሥት እየተደራደሩ እንደመንግሥት ይዋዋሏታል።
ባለፈዉ ዓመት የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች በርበራ ወደብ ላይ ጦር ሠፈር ለማቋቋም መስማማትዋ ተዘግቦ ነበር።አረቦች ሰሞኑን እንደገና እንደመንግስት አስታወሷት።ሐርጌሳዎች ከትንሺቱ ሐብታም አረብ፤ ትላልቆቹን፤ ብዙዎቹን በጣም ሐብታሞቹንም መረጡ።የአረቦቹ ጠብ የምዕራቡም የመስራቁንም ሐያል ዓለም እያነጋገረ፤ እያከራከረ፤ እያወዛገበም ነዉ።መዘዙ ከሰሜን እስከ ደቡባዊ አፍሪቃ የሚገኙ መንግሥታትንም መነካካቱ አልቀረም።የፖለቲካ ተንታኝ ዩሱፍ ያሲን እንደሚሉት ግን ጠቡ ከተካረረ ከመካከለኛዉ ምሥራቅ ቀጥሎ የሚጎዳዉ የአፍሪቃ ቀንድ ነዉ።
የአዉሮጳ ሕብረትና አባላቱ ጠቡ በድርድር እንዲረገብ እየጠየቁ ነዉ።ዩናይትድ ስቴትስ ለሳዑዲ አረቢያም፤ለቀጠርም የቢሊዮነ-ቢሊዮናት ዶላር ጦር መሳሪያ ትሸጣለች።ፕሬዝደንቷ የፋርስ ባሕረ-ሠላጤ አካባቢ ሐገራት «ቀጠር አሸባሪዎችን ትደግፈናለች ብለዉ ነግረዉኝ ነበር ይላሉ።ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሯ ሽምግልና ይላሉ።እስካሁን ጠቡን ለማርገብ ግልፅ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት የጀመረችዉ ኩዌት ናት።የቱርክ ፕሬዝደንት ሬሴፕ ጠይብ ኤርዶኻን እስከተገባደደዉ የረመዳን ማብቂያ ድረስ አረቦቹ ልዩነታቸዉን በዉይይት እንዲፈቱ አደራ ብለዋል።እስካሁን ግን የጠብ እንጂ የሠላም ጭላንጭል የለም።
ነጋሽ መሐመድ
አርያም ተክሌ