1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃ ቀንድና ሶማሊያ በባለሙያ ዓይን

ዓርብ፣ ጥር 25 1999

በአፍሪቃ ቀንድ በሚገኙ አገራት አካባቢ ተቋማቸዉን ዘርግተዉ ከሚንቀሳቀሱ የባህር ማዶ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መካከል Life and Peace Institute የተሰኘዉ ይገኝበታል። ዋና መስሪያ ቤቱ ስዊድን ዑፕሳላ የሆነዉ ይህ ተቋም በኬንያ ናይሮቢ ፅህፈት ቤት አለዉ፣ ለአፍሪቃ ቀንድ አገራት አገልግሎቱን የሚያሳርስበት።

https://p.dw.com/p/E0hM
የሸንጎዉ መሪ ሸህ ሸሪፍ
የሸንጎዉ መሪ ሸህ ሸሪፍምስል AP

ወይዘሮ ኪርሲ ሳሪሲቶ እንደሚሉት ተቋማቸዉ በሶማሊያ ስራ ከጀመረ 10ዓመታት አልፈዋል። ከ1990ዎቹ መነሻ አንስተቶም በሶማሌ ላንድ የሰላም ሂደቱን ይህ ተቋም ሲረዳ እንደቆየ ጊዜያዊ አስተባባሪዋ ይገልጻሊ። ከዚያም
«ከዚያም ከጥቂት ዓመታት በፊት በናይሮቢ በተካሄደዉ የሰላም ድርድር Life and Peace Institute ሂደቱን ደግፏል። በመቀጠልም መንግስት ተመሰረተ። ከዚያም በሶማሊያ ሌላ ጥያቄ መጣ። በሶማሊያ ብሄራዊ እርቅ ኮሚሽንን እንድንደግፍ።»

ከዚያም አሉ ሳሪሲቶ በደቡብ ሶማሊያ የተመሰረተዉ የሽግግር መንግስት ወደተረጋጋችዉ ባይደዋ በመዝለቅ መንግስትና ምክር ቤቱን መሰረተ። የእነሱ ተቋምም ወደባይደዋ ዞሮ መንግስቱን በሰላም ሂደት ሊረዳ የሚችልበትን መንገድ ይቃኝ ገባ።

እንደሚታወቀዉ ላለፉት 15ዓመታት መንግስት አልባ በቆየችዉ ሶማሊያ የተለያዩ የጦር አበጋዞች የህዝቡን ሰላም የሚያምሱባት፤ ተፈናቃዩም በየዕለቱ እየበረከ ወደተለያዩ አገራት የሚሰደደዉ እየተበራከ ነዉ የሰነበተዉ። ይህ ተቋም ደግሞ 10ዓመታት እዚያዉ ሶማሊያ የሰላም ሂደቱን ሲያግዝ ሰንብቷል ነዉ ያሉት ጊዜያዊ አስተባባሪዋ። በሂደቱ ግን ሶማሊያ ተረጋግታ አልታየችምና የተቋማቸዉ አስተዋፅዖ ምን ነበር ማለት ይቻላል? ምላሽ አላቸዉ

«Life and Peace Institute ብቻዉን በሶማሊያ ሰላምን ሊያመጣ አይችልም። እኛ የምናደርገዉ ምንድነዉ በሶማሊያ ለሚገኙ የተለያዩ አካላት መስጠት የሚገባዉን ድጋፋችንን መስጠት ነዉ። እናም እነሱ በአገሪቱ ሰላም ሊያመጡ ይችላሉ። የሶማሊያ ሁኔታ ደግሞ በእርግጥ ዉስብስብ በመሆኑ ቅር ካላለሽ ሶማሊያዊዉ የስራ ባልደረባችን በዚህ ቃለ ምልልስ እዲሳተፍ ልጋብዘዉ እችላለሁ።»

ሶማሊያ ዉስጥ ለሚገኘዉ ፅህፈት ቤታቸዉ በኃላፊነት የሚሰሩት አቶ አብዲ አደን አሊ ደግሞ እኛ ለሶማሊያ ሰላም ማምጣት ሳይሆን ስራችን ሰላም እንዲፈጠር ሁኔታዉን ማመቻቸት ነዉ ይላሉ።

በሶማሊያ የሚገኙ የተለያዩ ተቋማት መንግስታዊም ሆኑ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሚያቀርቡትን ሃሳብና እቅድ በአቅም መደገፍና በስልጠና ማገዝ ዋነኛ ተግባራቸዉ መሆኑንም አስረዱ።

የአካባቢዉ ተወላጅ እንደመሆናቸዉና በተቋሙም ባላቸዉ ሃላፊነት በአፍሪቃ ቀንድ ያለዉን ችግር ማለትም የዳርፉር፤ አሁን የተባባሰዉና ለዓመታት በተመሳሳይ የዘለቀዉ የሶማሊያ የሰላም እጦት፣ እንዲሁም የአፍሪቃ ቀንድ የፖለቲካ ተንታኞች እየሰጉለት የሚገኘዉ የአካባቢዉ ሁኔታ ምን ይመስላል ይላሉ አልኳቸዉ

«በእርግጥ የአፍሪቃ ቀንድ ምናልባት ስህተት ልባል እችላለሁ ግን እዉነት ነዉ በአህጉሩ ካለዉ ሁሉ በቋፍ ያለ አካባቢ ነዉ ማለት እችላለሁ። ለአካባቢዉ ደግሞ ነገሩ እንደ እንግዳ ደራሽ አይደለም ያለና ሲወራረስ የመጣ ሁኔታ ነዉ። ምክንያቱ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ሊሆን ይችላል፤ የተፈጥሮ ሃብትም ሊሆን ይችላል፤ ምናልባትም ከፒለቲካዊ ያለመረጋጋት ሁኔታ ጋር የተዛመደ ሊሆን ይችላል። ሌላዉ ይህን ችግር ያመጣዉ ደግሞ እንደ ሶማሊያ መንግስት ያሉት የመፍረሳቸዉ ነገር ነዉ። የዳርፉር ጉዳይ ሲታይ መንግሳት መሰረታዊ አገልግሎቶችን አላዳረሰም በሚል በአካባቢዉ የተነሳ ነዉ፥ ያ ደግሞ በህዝቦች መካከል አለመመቸትን ፈጠረ። ይህን መሰሉ ችግር ደግሞ በሱዳን ወይም በሶማሊያ ብቻ የተወሰነ አይደለም። በአካባቢዉ በአጠቃላይ የኖረ ችግር ነዉ ማለት ይቻላል።»

በተለያዩ ተቋማት፤ መንግስታትና ድርጅቶች የሚደረገዉ የሰላም ጥረት በአካባቢዉ ዉጤት ሊያመጣ ይችላል ብሎ መገመት ይቻልን ይሆን? አብዲ አደን አሊ ይህን ይላሉ

«ሶማሊያ የአካባቢዉ አካል የሆነች አገር ናት። ሶማሊያ ዉስጥ መረጋጋት ከሌለ የአካባቢዉን ሀገራትም መጉዳቱ አይቀርም። የዓለም ዓቀፉ ህብረተሰብ ሰላምን ማምጣትና መጫን አይችልም። ሊያደርጉ የሚችሉት በአገሪቱ የሚገኙት ህዝቦች ግጭትን ለመፍታት የሚያሳዩትን ተነሳሽነት መደገፍ ነዉ። ለምሳሌ ሶማሊያን ብናይ ሰላምን በሶማሊያ የማምጣት ፍላጎት ከህዝቡ መምጣት አለበት። ራሳቸዉ በአገራቸዉ ሰላምን ለማምጣት ዝግጁ መሆናቸዉን ማሳየት አለባቸዉ።»

ለምሳሌ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ከተሸናፊዉ የሸሪዓ ፍርድ ቤቶች ህብረት መሪ ከሆኑት ሼኽ ሸሪፍ ሼህ አህመድ ጋ መነጋገር መጀመራቸዉ ተገልጿል። ይህ ዉጤት ያመጣ ይሆን?

«በጣም! አየሽ የእስላማዊዉ ሸንጎ አባላት በወታደራዊ ረገድ ተሸነፉ ልንል እንችላለን በፖለቲካዊ ረገድ ግን አልተሸነፉም። አሁንም የማይካደዉ በጣም በጣም ከፍተኛ የሆነ የህዝብ ድጋፍ አላቸዉ። ይህም ድጋፍ ነበር ላለፉት 15ዓመታት ችግር ሲፈጥሩ የነበሩትን የጦር አበጋዞች አሸንፈዉ አካባቢዉን እንዲቆጣጠሩ የረዳቸዉ። ምንም እንኳን በጦር ኃይል ቢሸነፉም እንደሶማሌ ዜጋ እነሱም በሶማሊያ የሰላም ሂደት ሊጫዉት የሚችሉት ታላቅ ሚና አለ ብዬ አምናለሁ። እነሱን ማግለሉ ሁኔታዉን ያባብሳል። ዋናዉ ነገር የብሄራዊ እርቅ ሂደቱን መጀመር ነዉ። ያም ይሆናል ብዬም አስባለሁ።»