1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ

ዓርብ፣ ሚያዝያ 27 2009

 የፕሬዝዳንቱ የኢትዮጵያ ጉብኝት ከርሳቸው ከቀደሙት የሶማሊያ ፕሬዝዳንቶች በተለየ መዘግየቱ አንዳንድ ጥያቄዎችን ማጫሩ አልቀረም። ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ የተባሉ አንዳንድ መላ ምቶች ሲሰነዘሩ ቆይተዋል።

https://p.dw.com/p/2cRcH
Äthiopien Mohamed Abdullahi Mohamed, Präsident Somalia
ምስል DW/Y. G/Egziabhare

Äth-Somali-Beziehungen - MP3-Stereo

ሥልጣን ከያዙ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ ሳምንት አጋማሽ ኢትዮጵያን የጎበኙት አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት መሐመድ አብዱላሂ መሐመድ ሀገራቸው ደፈጣ ተዋጊውን ቡድን አሸባብን የማሸነፍ እቅድ እንዳላት ትናንት አዲስ አበባ ውስጥ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል። ፕሬዝዳንቱ እቅዳቸውን ለማሳካትም የኢትዮጵያን እገዛ ጠይቀዋል። አንድ የሶማሊያ ሚኒስትር ትናንት መቅዲሾ ውስጥ ከተገደሉ በኋላ ፕሬዝዳንቱ የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን አቋርጠው ትናንት ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል ። የሶማሊያ ፕሬዝዳንት መሐመድ አብዱላሂ መሐመድ ስልጣን ከያዙ ሦስት ወር ሊሞላቸው ጥቂት ቀናት ናቸው የሚቀሩት። በተመረጡ በጥቂት ቀናት ውስጥ ሳውዲ አረብያን ነበር የጎበኙት። ከዚያም በተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን እና በቱርክ ይፋ ጉብኝት አድርገዋል። ኬንያም ነበሩ።  ከመካከላቸው ኢትዮጵያ የርሳቸውን ፕሬዝዳንት መሆን አለመፈለጓ ሊሆን ይችላል የሚለው ይገኝበታል። ለንደን የሚገኘው ሶማሊያዊ ጋዜጠኛ ሊበን አህመድ ይህን አይቀበልም። ጋዜጠኛው እንደሚለው የዚህ ሳምንቱ የፕሬዝዳንቱ ጉብኝት እነዚህን መላ ምቶች የሚያፈርስ ነው ።
«አዎ እርግጥ ነው ከቀደሚዎቹ ፕሬዝዳንቶች የመጀመሪያ ጉብኝቶች ጋር ሲነጻጸር የርሳቸው ዘግየት ብሏል። እንደሚመስለኝ ፕሬዝዳንቱ ከፀጥታ ፈተናዎች አንስቶ እስከ መንግሥት ምሥረታ ድረስ ብዙ የተጠመዱባቸው ጉዳዮች አሉ። ሳውዲ አረብያ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከዛ በኋላ ደግሞ ቱርክ ነበሩ የኢትዮጵያው ጉብኝት አራተኛ ይፋ ጉብኝታቸው ነው። ይህም ትንሽ እንጂ በጣም አልዘገየም። የኢትዮጵያ መንግሥት በ2017ቱ የሶማሊያ ምርጫ ላይ ፖሊሲው ገለልተኛ እንደሆነ በይፋ አስታውቋል። እንደሚመስለኝ ያ ለሚሰጠው መላ ምት ሁሉ መነሻ ሊሆን ይገባል። ፕሬዝዳንቱ የተደረገላቸው አቀባበል ፣ የፕሬዝዳንቱ እና የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ንግግር የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ግንኙነት ወደ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገሩን ግልፅ ያደርጋል።»
በአሁኑ ጊዜ በሶማሊያ 20 ሺህ የሚደርስ የአፍሪቃ ኅብረት ጦር ይገኛል። ከመካከላቸው 6 ሺህ የሚጠጋው የኢትዮጵያ ሠራዊት ነው። ወታደሮችዋን ሶማሊያ ያዘመተችው ኢትዮጵያ ለሶማሊያ መረጋጋት ትልቅ ሚና የምትጫወት ሀገር ናት ይላል ጋዜጠኛ ሊበን። በርሱ አገላለጽ ኢትዮጵያም ሆነች ሌሎች የአካባቢው ሃገራት ለሶማሊያ መንግሥት በጣም አስፈላጊ ናቸው።
«ወደ ሶማሊያ ቤተመንግሥት «ቪላ ሶማሊያ» የሚመጣ ማናቸውም የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ከኢትዮጵያ ጋር ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ጎረቤት ሃገራት እንዲሁም የሶማሊያ የፖለቲካ ጉዳይ ከሚመለከታቸው ሃገራት ጋር ጠንካራ ግንኙነት መፍጠር ይኖርበታል። ፕሬዝዳንቱ በአሁኑ ጉብኝታቸው የኢትዮጵያ ወታደሮች ለቀዋት ሲወጡ አሸባብ የያዛትን ኤልቡርን ኢትዮጵያ መልሳ እንድትቆጣጠር መጠየቃቸውን ሰምቻለሁ። ስለዚህ የኢትዮጵያ እዚያ መገኘት የኢትዮጵያ እርዳታ በአሁኑም ሆነ በቀድሞው ፕሬዝዳንት ዘመን እጅግ ጠቃሚ ነው።»
ፕሬዝዳንት መሐመድ አብዱላሂ እንደተመረጡ ለአሸባብ ተዋጊዎች የእጃችሁን ስጡ ጥሪ አስተላልፈው ነበር። በምላሹ ጦርነት ያወጀባቸው አሸባብ ሥልጣን ከያዙ ወዲህ በሶማሊያ ጥቃቱን አጠናክሮ ቀጥሏል። በከትናንት በስተያው የአዲስ አበባ ጉብኝታቸው ፕሬዝዳንቱ በሰጡት መግለጫ ሀገራቸው አሸባብን የማሸነፍ ሁሉን አሳታፊ እቅድ ማውጣቷን አስታውቀዋል። «በሽታ» ያሉትን አሸባብን ድል የማድረግ እቅዳቸው የአካባቢውን ሃገራት ድጋፍ እንደሚሻም አሳስበዋል። አሸባብን ድል ለማድረግ ያቀዱት ደግሞ በሁለት ዓመት ውስጥ ነው። ይህ እንዴት ገቢራዊ ሊሆን ይችላል ? ጋዜጠኛ ሊበን፤
«ፕሬዝዳንቱ አሁን አዲሱን የሶማሊያ የፀጥታ አወቃቀር ማለትም ሁሉን አሳታፊ የሶማሊያ ጦር ለመመስረት እየታገሉ ነው። በቅርቡ ዓለም አቀፉ ክራይስ ግሩፕ  የፖሊሲ ምክሮች አቅርቧል። እቅዱ ሁሉን አቀፍ የሶማሊያ ጦር ማቋቋም እና በሶማሊያ የአፍሪቃ ኅብረት ጦር የአሚሶምን ቁጥር መቀነስ ነው። አሚሶም ሲቆጣጠራቸው የቆየውን አካባቢዎች የሶማሊያ ጦር እንዲረከብ ነው እቅዱ። ስለዚህ ፕሬዝዳንቱ ሁሉን ማሳተፍ የሚችል የሶማሊያ ጦር መመስረት ከቻሉ እቅዳቸው ሙሉ በሙሉም ባያሳኩም ወደ ግባቸው ሊቃረቡ ይችላሉ።»
በሶማሊያው ፕሬዝዳንት እቅድ ኢትዮጵያም ተስማምታለች። ፕሬዝዳንት መሐመድ አብዱላሂ መሐመድ ትናንት አንድ የሶማሊያ ሚኒሥትር መቅዲሾ ውስጥ ከተገደሉ በኋላ የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን አቋርጠው ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል።

Äthiopien Mohamed Abdullahi Mohamed, Präsident Somalia
ምስል DW/Y. G/Egziabhare
Äthiopien Mohamed Abdullahi Mohamed, Präsident Somalia
ምስል DW/Y. G/Egziabhare

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሰ