የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በአል ገና በቅዱስ ላሊበላ ተከበረ
ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 29 2017የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በአል ገና በላሊበላ ተከበረ
የገና በአልን በቅዱስ ላሊበላ ለማክበር ከአዲስ አበባ :ደሴ :ደብረብርሀን ከተሞች ወደ ስፍራዉ ያቀኑ ምዕመናን በአሉ በደመቀና ሰላማዊ በሆነ መልኩ ተከብሯል ብለዋል። ላለፋት 17 አመታት ገናን በላሊበላ በማክበር ላይ እገኛለሁ ሲሉ ለዶቼቬለ አስተያየታቸዉን የሰጡት የደሴ ከተማ ኗሪ አቶ ዳዊት መኮንን የዘንድሮዉ በአል በታዳሚዎች ቁጥር ከዚህ ቀደም ከነበረዉ የቀነሰ ነዉ ብለዋል።
የላሊበላና አካባቢዉ አስጎብኝማህበር ፕሬዝደንት የሆኑት አቶ እስታሉ ቀለሙ ለዶቼቬለ በሰጡት አስተያየት የቤዛ ኩሉ ሀይማኖታዊ ስርአት ላይ ስጋት የነበረን ቢሆንም በአሉ ግን በደመቀ መልኩ ተከብሯል ይሁን እንጂ የዉጭ ሀገርቱሪስቶች ቁጥር ከሰሞኑ ጭማሬ ያሳየ መሆኑን ተናግረዋል። በበአሉ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋየ በክልሉ ባለፈዉ አንድ አመት የነበረዉ የሰላም መደፍረስና እርስበርስ ግጭት ለክልሉ ኗሪ መፍትሄ ይዞ ስላልመጣ ሁሉም ጥያቄ ያላቸዉ አካላት ሊነጋገሩ ይገባል ብለዋል። ቱሪዝምን ዋንኛ አጋዥ የኢኮኖሚ አዉታር ለማድረግ መንግስት እየሰራ ነዉ ያሉት የቱሪዝም ሚኒስቴሯ ሰላማዊት ካሳ የኢትዮጵያ መንግስት የላሊበላንና አካባቢዉን የተሻለ የቱሪዝም መዳረሻ እንዲሆን እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
ኢሳያስ ገላዉ
አዜብ ታደሰ
እሸቴ በቀለ