1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢጋድ የሞቅዲሹ ጉባኤ አንድምታ

Tesfalem Waldyesረቡዕ፣ መስከረም 4 2009

የምስራቅ አፍሪካ በይነ-መንግስታት (ኢጋድ) አገራት ጉባኤ ዋና አጀንዳ ከነበሩት ውስጥ አንዱ የደቡብ ሱዳን ጉዳይ ቢሆንም የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር በሞቃዲሾ አልተገኙም፡፡ የጅቡቲው ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦመር ጌሌም ጉዞ ከጀመሩ በኋላ መመለሳቸው ተሰምቷል፡፡ ይህንን ተከትሎ ታዛቢዎች ስብሰባው እንደታሰበው ውጤታማ አልነበረም ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

https://p.dw.com/p/1K2hx
Somalia Selbstmordanschlag auf Nasahablood Hotel in Mogadischu
ምስል Reuters/F. Omar

[No title]

የሶማሊያን ጉዳይ ለዓመታት በቅርብ ሲከታተሉ የቆዩት የፖለቲካ ተንታኙ አቶ አብደታ ድርብሳ ሁለቱ መሪዎች ባይገኙም ስብሰባው እንዲካሄድ የተደረገው ከዚህ ቀደም የኢጋድ አገራት በሚኒስትሮች ደረጃ ተሰብስበው ሶማሊያ ያሳየችውን መሻሻል ለማሳወቅ ቃል ስለገቡ ነው ይላሉ፡፡ በጉባኤው የተላለፈው ውሳኔም “ለሁሉም አባል ሀገራት ገዢ ነው” ሲሉ ያስረዳሉ፡፡
“እነዚህ የጎረቤት ሀገሮች መሪዎች ባይኖሩም ውሳኔው ሁሉንም የኢጋድ አባል ሀገራት የሚመለከት ስለሆነ ገዢ ነው” የሚሉት አቶ አብደታ “ሁሉም ለውሳኔው ተገዢ የሚሆኑበት ልምድ እና አሰራር ነው ያለው” ሲሉ የኢጋድን አካሄድ ይገልጻሉ፡፡
የትናንቱ የሞቅዲሾ ስብሰባ ሲጠናቀቅ ኢጋድ ባወጣው ባለ 22 ነጥብ የአቋም መግለጫ በቀውስ ላይ የምትገኘው የደቡብ ሱዳን ጉዳይ ገሸሽ ተደርጓል፡፡ አብዛኛውን ትኩረት ለሶማሊያ የሰጠው መግለጫው በቀጣዩ ወር በአገሪቱ ለሚካሄደው ምርጫ ያለውን ድጋፍ አሳይቷል፡፡ አቶ አብደታ የደቡብ ሱዳን ጉዳይ እምብዛም ትኩረት አለማግኘቱ ሊያስገርም አይገባም ባይ ናቸው፡፡
“የስብሰባው አላማ በይበልጥ ከሶማሊያ ጋር ተያያዘ ስለሆነ ነው፡፡ የደቡብ ሱዳን ጉዳይ የኢጋድ ፕላስ ስብሰባ አዲስ አበባ ውስጥ በተካሄደበት ጊዜ ሰፊ ውይይት የተደረገበት እና የተወሰነበት ነው። ስለዚህ የሶማሊያው በአብዛኛው ሶማሊያ ተኮር የሆነ ውይይት ነው። ከደቡብ ሱዳን መሪ አለመገኘት ጋር ተያይዞ አይደለም እንደዚያ የሆነው” ሲሉ የጉባኤው የትኩረት አቅጣጫ ምን እንደነበር ያብራራሉ።
እንደ አቶ አብደታ አባባል መሪዎቹ የሞቅዲሾውን ጉባኤ በጥቅምት ወር በሶማሊያ ሊካሄድ ለታሰበው ምርጫ ያላቸውን ቁርጠኝነት አሳይተውበታል ይላሉ።
03.07.2014 online karte somalia eng
“መሪዎቹ የሶማሊያ ፌደራላዊ መንግስት ለቀጣዩ ምርጫ ግልጽ እና ተቀባይነት ያለው የምርጫ ስርአት ለማበጀት ያለውን ቁርጠኝነት አድንቀው ነው ስብሰባቸውን ያጠናቀቁት። ያ ማለት ደግሞ የሶማሊያ ፌደራላዊ መንግስት የተለያዩ ተቋማት ምርጫዉን የተሳካ ለማድረግ የሚያደርጉትን ጥረት ለመደገፍና ዉጤቱንም ተቀብለዉ ለመንቀሳቀስ ያላቸዉን ቁርጠኝነት ያሳዩበት ነዉ ብዬ ነዉ የማስበዉ።” ሲሉ አቶ አብደታ ይገልፃሉ።
የሞቅዲሾው ስብሰባ በሊቀ-መንበርነት የተመራው በኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ነበር፡፡ የኢጋድ የሊቀ-መንበርነት ቦታ በኢትዮጵያ ተይዞ ለበርካታ ዓመታት መቆየቱ እና በአገራቱ ጥምረት ላይ ያላት ከፍተኛ ተጽዕኖ አይሎ መታየቱ በይነ መንግስታቱ “የብቻ ትዕይንት ማስተናገጃ ሆነ” የሚል ትችት አስከትሏል፡፡ አቶ አብደታ ግን ለዚህ የኢጋድን አሰራር እና ደንብ መመልከት ይገባል ይላሉ፡፡
“የኢጋድን አሰራር፣ከአጋሮቹ ጋር ያለዉን ግንኙነት፣ ድርጅቱ በሌሎችም ተዓማኒ ሆኖ እንዲቀጥል የተደረገ አካሄድ ነዉ። ኢትዮጵያ ብቻዋን የያዘችዉ አይደለም። መሪዎቹ ከተስማሙበትና ከፈለጉ ለሌላዉ ለማስተላለፍ ችግር ያለ አይመስለኝም። አንድ ሃገር ከዚህ በላይ ሊቀመንበርነቱን ከዚህ በላይ ሊይዝ አይገባም የሚል የተፃፈ ነገር የለም ” ሲሉ ያጠቃልላሉ።
ተስፋለም ወልደየስ
አርያም ተክሌ