የጠቅላይ ሚኒስትር ለዉጥ ያደረገችዉ ሶማሊያ
ረቡዕ፣ ጥቅምት 20 2000የጌዲ ምክትል ሆነዉ የሰነበቱት ሳሊም አልዩ ኢብሮ ሃላፊነቱን ተረክበዋል። የባለስልጣናት ልዉዉጥ ቢደረግም በሶማሊያ ሰላምን ማስፈን ቅዠት ነዉ ሲሉ አንድ የኬንያ ባለስልጣን ጉዳዩ ገና ሩቅ መሆኑን ያመላከተ መግለጫ ለዘጋቢዎች ሰጥተዋል።
ሳሊም አልዩ ኢብሮ አሊ ሞሃመድ ጌዲ ጠቅላይ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት ምክትላቸዉ ነበሩ። አሁን ደግሞ ጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር። ምንም እንኳን ጌዲ በማንም ጫናና ግፊት አይደለም ስልጣኔን የለቀቁት ብለዉ ባይደዋ ላይ ለተቀመጠዉ የሽግግር መንግስቱ ምክር ቤት ቢናገሩም የፖለቲካ ተንታኞች መረጋጋት በራቃት ምድር የፕሬዝደንቱና የጠቅላይ ሚኒስትሩ አለመግባባት ችግሩን ያባብሰዋል ከሚል ግፊት የመጣ መሆኑን ያምናሉ።
ፕሬዝደንቱ ማንን መጌዲ ቦታ መተካት እንደሚቻል የየጎሳዉን መሪዎች እንዲሁም የምክር ቤት አባላትን ምክር ጠይቀዋል። ዉስጥ አዋቂ የሆኑ የፖለቲካ ተንታኞችና ዲፕሎማቶች በበኩላቸዉ ዩሱፍ የአንድነት መንፈስ በሶማሊያ ለማምጣት ከፈለጉና እያመረቀዘ የሄደዉን የሽምቅ ጥቃት ለማብረድ ከሃዉዬ ጎሳ መምረጥ እንደሚኖርባቸዉ ይጠቁማሉ።
በጌዲና ዩሱፍ መካከል የሚታየዉ የፖለቲካና የሰብዕና ልዮነት ጥቃት የሚሰነዘርበት የሽግግር መንግስታቸዉን አስተዳደር በመሰንጠቁ ምዕራባዉያን ደጋፊዎችን ግራ እንዳጋባ ነዉ የሚነገረዉ። ዉጤቱም ጌዲ ስልጣን በፈቃዴ ለቅቄያለሁ እንዲሉ አብቅቷል። የአሊ ሞሃመድ ጌዲ ከስልጣን መልቀቅ በሶማሊያ ሽግግር መንግስት ላይ የተደቀነዉን ፈተናም ሆነ በአገሪቱ መረን የለቀቀዉን ዉጥንቅጥ የሚያስተካክለዉ እንደማይሆን ጀርመናዊቷ የምስራቅ አፍሪቀፖለቲካ ተንታኝ አኔተ ቬበር ይናገራሉ፤
«ምንም ዓይነት መሻሻል ይመጣል ብዬ አላስብም። ምክንያቱም ፕሬዝደንቱ ራሳቸዉ የጋራ እንቅስቃሴ እንዲኖር ሁሉንም ያካተተ ዉይይት ይካሄድ የሚለዉን ሃሳብ ለመቀበል የሚበገሩ ሰዉ አልሆኑም። በዉይይቱ እስላማዊዉ ሸንጎ ይካተት የሚለዉን የተቃወሙት ጌዲ አልነበሩም። አብዱላሂ ዩሱፍ ናቸዉ። ስለዚህ መሻሻል ሊያመጣ ይችላል የሚባለዉ ከሁሉም ወገኖች ጋ እዉነተኛ የሆነ ዉይይት በማካሄድ መንግስት ለመገንባት ቢሞከር ነበር። ይህን መንግስት ብቻ ማጠናከር ሁኔታዉን የሚያረጋጋ ብቸኛ አማራጭ ነዉ ብዬ አላስብም።»
ፕሬዝደንት ዩሱፍ ተቀናቃኛቸዉ ጌዲ ስልጣን በለቀቁ ማግስት ወደጎሳ መሪዎች በመቅረብ ቀዉስ አስወጋጅ ዉይይት መፈለጋቸዉ ተሰምቷል። በሶማላኢ ያለዉን ከ16 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ የፖለቲካና የፍላጎት ትርምስ ለመፍታት ደግሞ ሁሉን ያካተተ ዉይይትና የእርቀ ሰላም ጉባኤ ማስፈልጉ ተደጋግሞ ተጠይቋል። አገር ዉስጥ ከሚገኙት የሽግግር መንግስቱ ተቃዋሚዎች ጋ ብቻ ሳይሆን በኃይል ተሸንፎ ከተበታተነዉ ራሱን እስላማዊ ሸንጎ ብሎ ከሚጠራዉ ቡድንም ጭምር መወያየቱ ለምድሪቱና ሰላም ለጠማዉ ህዝቧ መፍትሄ ያመጣልና ይህን ቡድን ለማነጋገር ሞክራችኋል? አስመራ ላይ ግንባር ፈጥረናል ካሉትስ ጋ ግንኙነት ፈጥራችኋል? ለሚለዉ ከዶቼ የእንግሊዘኛዉ ክፍል ለቀረበላቸዉ ጥያቄ በተጠባባቂነት የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ስልጣን የያዙት ሳሊም አልዩ ኢብሮ ሲመልሱ፤
«ከእኛ ጋ ለመነጋገር እንዲመጡ ሁሉንም መንገድ በመጠቀም ማበረታታችንን እንቀጥላለን። ምክንያቱም ፍላጎታችን ሁሉ የጋራ ፍላጎታችን ማለት ነዉ በሶማሊያ ሰላምን ማስፈን ነዉ። ይህ የመንግስታችን ፍላጎት ነዉ። የእነሱም ፍላጎት ይኸዉ መሆን አለበት። ስለዚህ በሶማሊያ ሰላምን ማስፈን የሚሻ ሁሉ ከሽግግር መንግስቱ የቀረበዉን ጥሪ ሊያጣጥልም ሆነ ወደጎን ሊያደርግ አይችልም። የሽግግር መንግስቱ ነገሩን እንዳዲስ ከዜሮ ነዉ የጀመረዉ። አንዳንድ ነገሮችን ጀምረናል። ያንን ለማጠናቀቅ ደግሞ በበርካታ ጉዳዮች ላይ አስቸጋሪ ነገሮች ይገጥሙናል።»
አያይዘዉም ከዓለም ዓቀፉ ህብረተሰብ የተፈለገዉን ያህል ድጋፍ አላገኘነም ያሉት የሽግግር መንግስቱ ሞግዚት በየደረጃዉ ከተቧደኑ ኃይላት ጋ ፍልሚያ ላይ የሚገኘዉ ያልተረጋጋዉ መንግስታቸዉ ከተባሉት ጋ ግንኙነት ለመፍጠርና ለመወያየት ፋታ እንዳላገኘ ተናግረዋል። የተሰጣቸዉን ጊዜያዊ ኃላፊነት በተመለከተ ሳሊም አልዩ ኢብሮ ሲናገሩ፤
«ሃዉዮዎችም ሆኑ ሁሉም ጎላ ይህ የሞግዚትነት ተግባር መሆኑን ያዉቃሉ ብዬ አስባለሁ።»
በሌላ በኩል ታዛቢዎች በሶማሊያ ወደመጋጋት የሚያመጣዉ መንገድ እጅግ ዉስብስብ እንደመሆኑ ያች አገር ሰላም ትሆናለች ማለት ቅዠት ነዉ ይላሉ። የኬንያ የዉጪ ጉዳይ ሚኒስትር ራፋኤል ቱጂ ይህን ለዘጋቢዎች የተናገሩት የጌዲን ስንብት ተከትሎ ዩሱፍ ከጎሳ መሪዎችና የምክር ቤት አባላት ጋ ቀዉስ ማስወገጃ ያሉትን ዉይይት እንዳካሄዱ ነዉ። ቱጂ እንደሚሉት በሶማሊያ መረጋጋትን በማስፈን ማዕከላዊ መንግስትን መመስረት እጅግ ሩቅ ነዉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በዛሬዉ ዕለት ፕሬዝደንት አብዱላሂ ዩሱፍ የዉጪ ጉዳይ ሚኒስትር ስዩም መስፍንን ባይደዋ ላይ በወቅቱ የሶማሊያ ሁኔታና የኢትዮጵያ ሰራዊት በመቃዲሾ የሚታየዉን የአደጋ ጣዮች ጥቃት ለመከላከል እያደረገ ያለዉን ጥረት በተመለከተ ተነጋግረዋል። ለአዣንስ ፍራንስ ፕረስ ስማቸዉ እንዳይጠቀስ በማሳሰብ አንድ የፕሬዝደንት ዩሱፍ ፅህፈት ቤት ባለስልጣን እንደነገሩት ከሆነ ችግሮች በሰላማዊ ዉይይት እንዲፈቱ አቶ ስዩም ለፕሬዝደንት ዩሱፍ አሳስበዋል።