«መንግሥት እና ሸኔ ሊደራደሩ ነዉ መባሉ»የህዝብ አስተያየት
ሰኞ፣ ሚያዝያ 16 2015ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድ ከ"ሸኔ" ጋር በታንዛኒያ በነገው ዕለት ድርድሩ እንደሚጀመር አስታውቀዋል፡፡ ሠላም የሁሉም ነገሮች መሠረት እንደሆነ በመጥቀስ ይቅርታ በመባባል ጦርነትን በሰላም እና ንግግር መፍታት የስልጣኔ መገለጫ መሆኑንም ጠቁሟል፡፡ ከተለያዩ የወለጋ አካባቢዎች ያነጋገርናቸው ነዋሪዎችም በየቦታው የሚስተዋለውን ግጭት በውይይትና ንግግር ለመፍታት የሚደረገው ጥረት ዘላቂ ሰላም ያሰፍናል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ በሁሉም ዞኖች ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ደስተኛ መሆናቸውንም አክለዋል፡፡
በምዕራብና ደቡብ አሮሚያ ክፍል በስፋት ከሚንቀሳቀሱ መንግስት ሼኔ የሚላቸው ራሳቸውን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብሎ ከሚጠሩ ታጣቂዎች ጋር ንግግር እንደሚጀመር ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር አብይ አህመድ ገልጸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚስትሩ ይህንን የገለጹት በትንትናው ዕለት በሰሜን ኢትየጵያ የነበረውን ጦርነት በሰላም ስምምነት እንዲጠናቀቅ ሚና ለነበራቸው አካላት በተዘጋጀው ምስጋና መርሀ -ግብር ላይ ከ"ኦነግ ሼኔ" ጋር ድርድር በነገው ዕለት በታንዛኒያ እንደሚጀመር መግለጻቸውን የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሐን ዘግበዋል፡፡
ከቄለም ወለጋ፣ሆሮ ጉደሩ፣ ምዕራብና ምስራቅ ወለጋ ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች በበኩላቸው ድርድሩ ተግባራዊ እንዲሆንና በዞኑ ሰላም ይሰፍናል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ የምስራቅ ወለጋ ነቄምቴ ከተማ ነዋሪው አቶ ድርቤ ቱጂ በመንግስትና ታጣቂዎች መካከል ያለው ልዩነት በውይይት እንዲፈታ ጠቅላይ ሚስትሩ ወደ ነቀምቴ ባቀኑበት ባለፈው ሳምንት የሀገር ሽግለዎችም ሀሳብ አቅርበው እንደነበር ጠቁመዋል፡፡
"በባለፈው ውይይት በሰሜኑ የወረደውን ዕርቅ በኦሮሚያ ለምን አልሆንም ብለን ጠይቀን ነበር፡፡ ዛሬ በጣም ደስ ብሎናል፡፡ ሁለቱ ወገኖች ይስማማሉ ብለን እናምናለን፡፡ ህዘቡም በጣም ተደስተዋል፡፡ ድርድሩ በቶሉ ስራ ላይ ሊውል ይገባል ብለን በትልቅ ተስፋ ነው እየጠብቅን ያለነው፡፡ ሰላም ይወርዳል ብለን እናስባለን፡፡"
አቶ ሀሰን ይምር በቄለም ወለጋ መቻራ በተባለች ከተማ ነዋሪ የሆኑና በንግድ ስራ የሚተዳደሩ ሲሆን ባለፉት ሁለት ዓመታት በመንገድ መዘጋጋት እና ጸጥታ ችግር ምክንያት ለከፋ ችግር ተጋልጠው እንደነበር ተናግረዋል፡፡ በመንግስትና ታጣቂዎች መካከል ያለው አለመግባባት በውይይት ቢፈታ በስፍራው ተቋርጦ የቆየው የግብርና፣የመንገድ ግንባታ የማህብረሰቡ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ይቀረፋል ብለው ያምናሉ፡፡
በሆሮ ጉደሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ ነዋሪ የሖኑት አቶ አየለ ቡልቲ በበኩላቸው በወረዳው በተለያዩ ስም ይደርስ በነበረው ጥቃት ምክንያት ከመኖሪያ ቤታቸው ተፈናቅለው በዞኑ ዋና ከተማ ሻምቡ ከተማ መኖር ከጀመሩ ወደ ሁለት ዓመት እንደሆናቸው ተናግረዋል፡፡ መንግስትና ታጣቂዎች ልዩነቶችን በድርድር ለመፍታት ያቀዱት ሀሳብ ህዝቡ ለረጅም ጊዜ ሲመኘው የነበረ ነው ብለዋል፡፡ አሙሩ ወረዳን ከሌላ ስፍራ ጋር የሚያገናኙ መንገዶች ከተዘጉ ረጅም ጊዜ በማስቆጠሩ ሰብአዊ እርዳታ አለመኖሩን እንዲሁም የሂክምና ተቋማት ስራ በማቆማቸው ብዙ ሰዎች ለጉዳት መዳረጋቸውን አቶ አየለ ጠቁሟል፡፡
የምዕራብ ወለጋ ዞን ቆንዳላ ከተማ ነዋሪ መሆናቸውን የነገሩን አቶ ለታ አብዲሳ የሰላም ስምምነቱ ህዝቡ ወደ ልማቱ እንዲመለስ እንደሚያግዝና በአካባቢአቸው የቆየውን የትራንስፖርት ችግርን ያስቀራል ብለዋል፡፡
የታጣቂዎች እንቀስቃሴ በስፋት የሚስተዋልበት ምዕራብ እና ደቡብ ኦሮሚያ በተለያዩ ወቅቶች በተፈጠሩ ግጭች በመቶዎች ሚቆየጠሩ ሰዎች ህይወት ያጡ ሲሆን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ተፈናቅለው ቆይቷል፡፡ ትናንት ማምሻውን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በሚል ስም በማህበራዊ መገናኛ ዜዴ የተሰራጨው መግለጫ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የድርድር ሀሳብ እንደሚቀበል ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ሼኔ የሚል ስያሜ እንደማይቀበልና ትክክለኛው የድርጅቱ ስም የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት መሆኑን በመግለጫው ጠቁሟል፡፡
ነጋሳ ደሳልኝ
አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሐመድ