1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መገናኛ ብዙሀን ቢሮዎች ላይ ያነጣጠረው ዘረፋ

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 11 2015

ኢትዮጵያ ኢንሳይደር የተባለው የበይነ መረብ ሚዲያ ቢሮ ላይ የተፈጸመው ዝርፊያ (ስርቆት) የተቋሙን ህልውና በእጅጉ የሚፈታተን መሆኑን ያልሸሸገው በይነ መረብ መስራች እና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ጋዜጠኛ ተስፋለም ምናልባት ስራ እስከማቆም ያደርሳችሁ ይሆን ወይ በሚል ለቀረበለት ጥያቄ ግን መደምደሚ ላይ ለመድረስ ጊዜው ገና ነው የሚል ምላሽ ሰጥቷል፡፡

https://p.dw.com/p/4U5zX
Äthiopien Tesfalem Weldeyes Ethiopian Insider
ምስል Seyoum Getu/DW

የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሀን ቢሮዎች ላይ ያነጣጠረው ዘረፋ

ከትናንት በስቲያ እሁድ ሌሊት ለሰኞ አጥቢያ ኢትዮጵያ ኢንሳይደር የተባለው የበይነ መረብ ሚዲያ ቢሮ መዘረፉን ተቋሙ ትናንት ባወጣው ይፋዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡
“ለእኛ እንደ ደም ስር ያገለግሉናል ብለን የምናምን፤ በበርከታ ዓመታት ቢያንስ ለሶስት ዓመታት ተለፍቶባቸው የተገኙ ንብረቶች ናቸው የተዘረፉብን፡፡”
ኢትዮጵያ ኢንሳይደር የተሰኘ በይነ መረብ መስራች እና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልዴየስ ለዶቼ ቬለ የተናገረው ነው፡፡ የቀድሞው የዶይቼ ቬለ ጋዜጠኛ ተስፋለም ያቋቋመው ኢትዮጵያ ኢንሳይደር የበይነ-መረብ ሚዲያ ቢሮ እሁድ ለሊት ተሰብሮ ሲዘረፍ፤ አራት ላፕቶፕ፣ ሶስት ካሜራ፣ ከሁለት ዘመናዊ ዙም ሌንስ እና አራት መደበኛ ሌንሶች እንዲሁም አንድ የእጅ ስልክ መወሰዱንም ተናግሯል። “እሁድ እስከ 10 ሰዓት እኔን ጨምሮ ሌሎች ባልደረቦቼ ቪዲዮ ፕሮዳክሽን ስንሰራ ውለን ነበር የወጣነው፡፡ ስንወጣ በሮቹ መቆለፋቸውን በሚገባ አረጋግጠናል፡፡ በማግስቱ ሰኞ ጠዋት ባልደረባችን ወደ ቢሮ ስትገባ ነው የካሜራ እና ላፕቶፕ ኮምፒዩተሮች ማስቀመጫ ሎከር እና የጠረጴዛዎች እቃ ማስቀመጫ መሳቢ ተከፋፍተው ተዝረክርከው ያገኘችው፡፡”በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ መድሐኒዓለም አካባቢ ከሚገኘው ባለ አራት ወለል ህንጻ ላይ የተለያዩ ተቋማት ቢሮ እና የንግድ ስፍራ ቢኖርም በእለቱ የዘረፋው ኢላማ የሆነው ይህ የኢትዮጵያ ኢንሳይደር ቢሮ ብቻ ነው። ዶቼ ቬለ በስፍራው ተገኝቶ ባደረገው ቅኝትም በዚህ ቢሮ ከብረት የተሰራ የውድ እቃዎች ማስቀመጫ የተባለው ሳጥን መቆለፊያው ተገንጥሎ ተመልክቷል፡፡ ጠረጴዛዎችም ላይ የተገጠሙ የፋይል ማስቀመጫ መሳቢያዎች ተገነጣጥለው ተከፍቷል፡፡ ጋዜጠኛ ተስፋለም እንደሚለው እሁድ ከሰኣት 10 ሰኣት ከቢሮው ከወጡበት ሰኣት ጀምሮ እስከ ሰኞ ማለዳ 12፡50 ድረስ ዘረፋው የተፈጸመበት ሰዓት በውል ባይታወቅም ዘራፊዎቹ ውድ እቃዎቹን መራርጠው ከወሰዱና ሎከሮቹን ከፋፍተው ከወጡ በኋላ በር ተዘግቷል፡፡ ይህንኑንም ለአከባቢው መርማሪ ፖሊሶች አሳይተዋል፡፡ “በሩን የከፈተችው ባልደረባችን የሆነውን እንዳየችው ስትደውልልኝ ቶሎ ወደ ቢሮ ሄድኩ፡፡ ምንም እዳትነካም ነግሬያት ወደ ቦሌ አዲሱ ስታዲየም አከባቢ ወዳለው ፖሊስ ጣቢ ሄደን አሻራ እንዲያስነሱ አደረግን፡፡ ቃላችንም ሰጥተን ወደ ቢሮያችን ተመልሰን የሆነውን በመግለጫ አወጣን፡፡” 
በሚዲያው ላይ የተፈጸመው ዝርፊያ (ስርቆት) የተቋሙን ህልውና በእጅጉ የሚፈታተን መሆኑን ያልሸሸገው ጋዜጠኛ ተስፋለም፤ ምናልባት ስራ እንከማቆም ያደርሳችሁ ይሆን ወይ በሚል ለቀረበለት ጥያቄ ግን መደምደሚ ላይ ለመድረስ ጊዜው ገና ነው የሚል ምላሽ ሰጥቷል፡፡ “አሁን ጉዳዩ በፖሊስ እንደመያዙ እቃዎቻችን ይመለሱልናል፤ ፍትህም እናገኛለን የሚል ተስፋ አለን፡፡ ካልሆነ ግን ለኛ ኤነት አዲስ አዳጊ መስሪያ ቤት ፈታኝ ሊሆንብን ይችላል፡፡”
መሰል በበይነመረብና ዩቲዩብ ሚዲያዎች ላይ ተመሳሳይ የስርቆት (ዘረፋ)ተግባር ሲፈጸም ይህ የመጀመሪያ አይደለም፡፡ አራት ኪሎ እና ኢትዮ 251 የተሰኙ አራት ኪሎ አከባቢ ቢሮ ተጋርተው ከሚሰሩበት ስፍራ እንዲሁ ሌሊት አስፈላጊ የስራ እቃዎቻቸው መዘረፉን ገልጸው ነበር፡፡ ይህን አስመልክቶም አስተያየቱን ለዶይቼ ቬለ የሰጠው የአራት ኪሎ ሚዲያ መስራች ጋዜጠኛ አልአዛር ተረፈ፤ “መጋቢት 10 ቀን 2015 ዓ.ም. አራት ኪሎ ከኢትዮ251 ጋር ተጋርተን ከምንሰራበት ስቱዲዮ አራት ካሜራዎች እና ዙመር ከተወሰደብን በኋላ ተከታታይ ዛቻ እና ወከባ ደረሰብን፡፡ በመሆኑም ስራችንን ለማቆም ተገደናል” ብሏል።
የኢትዮጵያ ኢንሳይደሩ ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስም ይህ ነገር ተራ ዘረፋ ብቻ አይመስልም ሲል መላምቱን አስቀምጧል፡፡ “የሚገርመው ዘረፋዎቹ ተመሳሳይ ቀን እሁድ ምሽት እየተጠበቀ ነው የተዘረፉት፡፡ ውድ እቃዎች ካሉዋቸው ህንጻዎች ተመርጠው ሚዲያዎች ለምን ተዘረፉ የሚለው ጥያቄ ያጭራል፡፡ አሁን በዚህ ቢሮአችን ባለበት ህንጻ አንድ ደረጃ ስትወርድ ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው የፎቶ ስቱዲዮ እቃዎች አሉ፡፡ ታዲያ ለምን እኛ ላይ አነጣጠረ ብለን ከዚህ በፊት ከነበረው ሂደትት ጋር ስናስተያየው ነው ሴተራ ሳይሆን አይቀርም የሚል ምክknንያታዊw ዊ ጥርጣሬ ያደረብን፡፡”የመገናኛ ብዙሃ ባለሙያዎቹ ላይ ስላተኮረው የስርቆት ወንጀል የተጠየቁት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ ፖሊስ ሁሉንም ተቋማት እኩል የመጠበቅ ኃላፊነቱን ይዞ እንደሚሰራ በመግለጽ፤ በመገናኛ ቡዙሃኑ ላይ አተኩሯል ስለተባለው ዘረፋ ግን መረጃ እንደሌላቸው አስረድተዋል፡፡

Äthiopien Tesfalem Weldeyes Ethiopian Insider
ምስል Seyoum Getu/DW
Äthiopien Tesfalem Weldeyes Ethiopian Insider
ምስል Seyoum Getu/DW

ስዩም ጌቱ 
ኂሩት መለሰ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር