ምዕራብ ወለጋ ውስጥ የተፈናቀሉት መመለሳቸው
ሐሙስ፣ ሐምሌ 7 2014
በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ ሰኔ 11/2014 ዓ.ም በነበረው የጸጥታ ችግር ተፈናቅለው ወደ አርጆ ጉዳቱ ከተማ የሸሹ ዜጎች ወደ ቀድሞ ቀያአቸው መመለሳቸውን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ። የኦሮሚያ «ቡሳ ጎኖፋ» ምዕራብ ወለጋ ቅርንጫፍ ( በቀድሞ ስሙ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ጽ/ቤት) ኃላፊ ወ/ሮ ነጻነት ዓለማየሁ በወቅቱ ተፈናቅለው በአርጆ ጉደቱ ተጠልለው የነበሩ ሁሉም ሰዎች ወደ ቀያአቸው መመለሳቸውን ገልጸዋል፡፡ መኖሪያ ቤታቸው ለተቃጠለባቸው 96 ነዋሪዎችም ለጊዜያዊ መጠለያ የሚሆን ሸራዎች መዳረሱንም ጠቁሟል፡፡ በቶሌ ቀበሌ የሚገኙ ያነጋገርናቸው ነዋሪዎችም ሰብአዊ ድጋፍ እንደ ደረሳቸው ገልጸው በአካባቢው አሁንም የጸጥታ ስጋት መኖሩን ተናግረዋል። በርካታ ሰዎች ደግሞ በጸጥታ ችግሩ ስጋት ወደ ወሎ ሀርቡ የሚባል ስፍራ መሄዳቸውንም ገልጸዋል።
በሰኔ 11/2014 ዓ.ም በምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ በነበረው የጸጥታ ችግር የተፈናቀሉ ዜጎች ባጠቃላይ ወደ 12 ሺህ እንደሚጠጉ የዞኑ አስተዳደር በወቅቱ ገልጾ ነበር። ከቶሌ የተፈናቀሉ የተወሰኑ ሰዎች በቶሌ ከተማ እንዲሁም ሌሎች ወደ አርጆ ጉዳቱ ከተማ ሸሽተው እንደነበርም የቡሳ ጎኖፋ ኦሮሚያ የምዕራብ ወለጋ ዞን ቅርንጫ ኃላፊ ወ/ሮ ነጻነት ዓለማየሁ አስረድተዋል። የዞኑ አስተዳደር ባደረገው ማጣራት ከቶሌ የተፈናቀሉ እና ወደ ሌላ ስፍራ የሸሹ ዜጎች 600 የሚደርሱ ሲሆን በቶሌ ቀበሌ አቅርቢያ በምትገኘዋ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አንዲት ቀበሌ ሴኔ የተባለች ስፍራ የተፈናቀሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችም በአርጆ ጉዳቱ ተጠልለው እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ከጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ ተፈናቅለው በአርጆ ጉዳቱ መጠለያ ጣቢያ የነበሩ በሙሉ ወደቀአያቸው መመለሳቸውን እና በአሁኑ ጊዜም ወደ 6ሺህ ለሚደርሱ ዜጎች ድጋፍ በቶሌ ቀበሌ መዳረሱን ኃላፊዋ አመልክተዋል፡፡
በጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ በወቅቱ በደረሰው ጥቃት መኖሪያ ቤታቸው ሙሉ በሙሉ እንደ ወደመባቸው የነገሩን ነዋሪ በቀይ መስቀል እና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር( ቡሳ ጎኖፍ በኩል) የተወሰነ ድጋፍ ማግኘታቸውን ገልጸዋል። ወደ ቶሌ ሲመለሱ መኖሪያ ቤታቸውን ጨምሮ የነበሯቸውን የቁም እንስሳት እና እህል መውደሙንም አብራርተዋል፡፡
በቶሌ ቀበሌ ስልሳው የሚባል መንደር ነዋሪ እንደሆኑ የተናገሩት ሌላ የአካባቢው ነዋሪም በጥቃቱ ወቅት ሦስት የቤተሰባቸውን አባላት እንዳጡ ጠቁመዋል፡፡ ሰብአዊ ድጋፍ በመንደራቸው እንደተሰጣቸውም ገልጸዋል፡፡
በሰኔ 11/2014 በጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል «ሴኔ» ቀበሌ በደረሰው ጥቃት የበርካታ ሰዎች ሕይወት መጥፋት ሲዘገብ ቆይቷል፡፡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባሎጅጋፎ ወረዳ ሴኔ ቀበሌ የደረሰው የጉዳት መጠን ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም። በወቅቱ በቶሌ እና አካባቢው የ338 ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን መንግሥት ይፋ አድርጓል።
ነጋሳ ደሳለኝ
ሸዋዬ ለገሠ
እሸቴ በቀለ