ስደተኞችን በማባረረር የምትወቀሰው ግሪክ
ማክሰኞ፣ መጋቢት 21 2013ግሪክ ተገን ጠያቂዎችን በግዳጅ በማባረር እየተወቀሰች ነው። ባለሥልጣናቷ ግን ወቀሳውን ሀሰት ሲሉ በማስተባበል ላይ ናቸው።የአውሮጳ ኅብረት በበኩሉ ዓለም አቀፍ ከለላ የሚያስፈልጋቸው ተገን ጠያቂዎች ሊባረሩ አይገባም ብሏል።የአውሮጳ ኅብረት እና ቱርክ ፤በቱርክ በኩል ወደ አውሮጳ የሚካሄድ ሕገ ወጥ የሚሉትን ስደት ለማስቆም ስምምነት ላይ ከደረሱ አምስት ዓመት አለፈ። በጎርጎሮሳዊው መጋቢት 18፣2016 በተፈረመው በዚህ ስምምነት በቱርክ በኩል ወደ ግሪክ ደሴቶች የተሻገሩና የተገን ማመልከቻቸው ተቀባይነት ያላገኘ ሕገ ወጥ የሚባሉ ስደተኞችና ተገን ጠያቂዎች ወደ ቱርክ እንዲመለሱ ይደረጋል።የአውሮጳ ኅብረትና ቱርክ እዚህ ስምምነት ላይ የደረሱት ከ5 ወራት ድርድር በኋላ ነበር።ይህ ስምምነትም የስደተኞች መጠለያዎቿ ተጨናንቀው ለነበሩት ለግሪክ ትልቅ እፎይታን የሚያስገኝ መፍትሄ ተደርጎ ነበር የታሰበው።ምንም እንኳን ከስምምነቱ በኋላ ወደ ግሪክ የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር ቢቀንስም በተቃራኒው ግሪክ ከለላ የሚያስፈልጋቸውን ስደተኞች ወደ ቱርክ እንደምታባርር መረጃ እንደደረሰው የተመ የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር UNHCR ይፋ አድርጓል።ድርጅቱ እንደሚለው ግሪክ በግዳጅ ስደተኞችን እንደምትመልስ መረጃውን ያገኘው ከራሱ ምንጮች ነው።ይህንንም መረጃ ለግሪክ ባለሥልጣናት አስተላልፏል።ከአንድ ወር በፊት በግሪክዋ ደሴት ሌስቦስ የደረሱ ተገን ጠያቂዎች ተጎትተው እንዲመለሱ መደረጉን ድርጅቱ አስታውቋል።ከዚህኛው መረጃ አስቀድሞ የወጣ ዘገባ ደግሞ የአውሮጳ ኅብረት የባህር በር ተቆጣጣሪ ፍሮንቴክስ ሠራተኞችም በድርጊቱ ተሳትፈዋል ይላል።ከዚህ በተጨማሪም የግሪክ የባህር ጠረፍ ጠባቂዎች ስደተኞች የሚመጡባቸውን አነስተኛ የጎማ ጀልባዎች ሞተሮችን በማበላሸት ስደተኞቹ በቱርክ ባህር እንዲንሳፈፉ በማድረግ የቱርክ የባህር ጠረፍ ጠባቂዎች እንዲታደጓቸው ጥለዋቸው ይሄዳሉ ተብለውም ተወንጅለዋል።ይህ የUNHCR ዘገባ እንዳሳሰበው የአውሮጳ ኅብረት አስታውቋል።ትናንት የግሪኮቹን ደሴቶች ሳሞስና ሌስቦስን የጎበኙት የአውሮጳ ኅብረት የሃገር ውስጥ ጉዳዮች ኮሚሽነር ኢልቫ ጆአንሰን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ስጋታቸውን ገልጸው፣ጉዳዩን ከግሪኩ የኢሚግሬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ኖቲስ ሚታራቺ ጋር እንዳነሱትም አስታውቀዋል።
«የUNHCR ዘገባ በጣም ያሳስበኛል ነው የምለው።እንደሚመስለኝ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ አንዳንድ ልዩ ጉዳዮች አሉ።ይህን ጉዳይ ብዙ ጊዜ ከኖቲስ(የግሪክ የኢሚግሬሽን ሚኒስትር)ና ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር አንስተነዋል።የግሪክ ባለሥልጣናት ስደተኞች በግዳጅ እንዲመለሱ ተደርገዋል የሚለውን ወቀሳን ማጣራትና ግልጽ ማድረግን በተመለከተ ብዙ ሊያከናውኑ ይችላሉ ብዬ አስባለሁ።»
የግሪክ ድንበር ተቆጣጣሪዎችት በአግያን ባህር በኩል በጀልባ የሚመጡ ስደተኞችን እንደሚያዋክቡና እንደሚበድሉ ቱርክም ደጋግማ ስትከስ ነበር።እነዚህን ውንጀላዎች በሙሉ ግን ግሪክ አልተቀበለችም። የግሪክ መንግሥት ባለሥልጣናት ወቀሳውን ሀሰት ሲሉ በተደጋጋሚ ውድቅ አድርገዋል። ትናንት ከኮሚሽነር ጆአንሰን ጋር ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የግሪክ የኢሚግሬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ኖቲስ ሚታራቺ ክሱን በጥብቅ ተቃውመዋል።
«የግሪክ የባህር ጠረፍ ጠባቂዎች ስደተኞችን በኃይል መልሰዋል መባሉን በጥብቅ እንቃወማለን።ግሪክ ለዓለም አቀፍና ለአውሮጳ ሕግ ሙሉ በሙሉ ተገዥ ናት።ሆኖም ከዚሁ ጋር ሃገሮች ድንበሮች እንዳሏቸው የሃገር ድንበርን ለመጠበቅም ባለሥልጣናት ሕገ መንግሥታዊ ግዴታቸውን የሚተገብሩባቸው ደንቦችና መመሪያዎች እንዳሏቸው ግልጽ ሊሆን ይገባል።ፍሮንቴክስ ቀረቡ የተባሉትን ክሶች የሚያጣራ አንድ ቡድን እንዳለው እረዳለሁ። በደረሰኝ ዘገባ መሠረት ምርመራ በተካሄደባቸው ጉዳዮች አንድም የመሠረታዊ መብቶች ጥሰት የለም።»
ሚታራቺ እስካሁን የግሪክ የፍትህ አካላትንና የአውሮጳ ኅብረት የባህር ጠረፍ ጠባቂ ፍሮንቴክስን ጨምሮ በገለልተኛ አካላት በተካሄዱ የማጣራት ሥራዎች ዓለም አቀፍንም ሆነ የአውሮጳን ሕግ የጣሱ ሰዎች አልተገኙም ሲሉም ተናግረዋል። ጆአንሰን በበኩላቸው አባል ሃገራት ለዓለም አቀፍና ለአውሮጳ ሕጎች ተገዥ እንዲሆኑ ጠይቀው በአጋጣሚው ሁሉም ሃገር መሰል ችግሮችን የሚያጣራበት አሠራር እንዲዘረጋ ጥሪ አቅርበዋል።
«የባህር ጠረፍ መጠበቅ ቀላል ሥራ አይደለም።አንዳንዱ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሙያዊ ውሳኔዎች ላይ መድረስ የግድ ይላል።አንዳንዴ ይህን ማድረግ አደገኛ ሊሆንም ይችላል።በሙያው መሠረት መሥራት አስፈላጊ ነው።አባል ሃገራት በሙሉ ለአውሮፓ ኅብረትና ለዓለም አቀፍ ሕግ ተገዥ ሊሆኑ ይገባል።በኔ በኩል ሁሉም አባል ሃገራት መሰል ችግሮችን ሊያጣሩ የሚችሉበት ነጻ አሠራር ሊዘረጉ ይገባል።ስህተት ከተገኘም ተጠያቂነት መኖር አለበት።»
ባለፈው ዓመት በእሳት አደጋ የወደመውን በርካታ ስደተኞች የነበሩበትን የሌስቦሱን የሞሪያ መጠለያ የሚተካ አዲስ የስደተኞች ማቆያ የመገንባት እቅድ ተይዟል።በደሴቶቹ መጠለያዎች መገንባታቸው ለስደተኞቹም ሆነ ለነዋሪዎቹ ጠቃሚ መሆኑን ነው ጆአንሰን በትናንቱ መግለጫቸው ያስረዱት በሌላ በኩል በጎርጎሮሳዊው 2020 በፈቃደኝነትም ይሁን በግዳጅ የተመለሱ ስደተኞችም እንደነበሩ ጆአንሰን ተናግረዋል።
«ምንም እንኳን ባለፈው ዓመት የኮሮና ወረርሽኝ የነበረ ቢሆንም 2500 ስደተኞች በፈቃዳቸው ተመልሰዋል።ግሪክ በግዳe የመለሰቻቸው ደግሞ እንደሚመስለኝ 3500 ይሆናሉ።አስፈላጊ የሆነው የድንበር ጥበቃ እንዲደረግ እናግዛለን።አሁን ደግሞ ተጨባጭ የሆኑ ሥራዎችን እናከናውናለን። ስደተኞች የተሻለ የኑሮ ሁኔታ እንዲመቻችላቸው የአካባቢው ህዝብም የተሻለ የኑሮ ሁኔታ እንዲኖረው በደሴቶቹ አዳዲስ የመቀበያ ማዕከላትን እንገነባለን። እናም ዛሬ በሌስቦስና በኪዮስ ለሚገነቡት የስደተኞች መጠለያ ማዕከላት የተጨማሪ 155 ሚሊዮን ዩሮ ስምምነት ተፈራርመዋናል።»
ይህ ግን በደሴቲቱ ነዋሪዎች ዘንድ ተቀባይነትን አላገኘም።ጆአንሰን የስደተኞች መጠለያውን በጎበኙበት ወቅት የደሴቲቱ ነዋሪዎች የተቃውሞ የተቃውሞ ሰልፍ አካሂደው ነበር። አንድ ደሴቲቱ ነዋሪ ለኮሚሽነር ጆአንሰን ተቃውሞአቸውን በቀጥታ በቁጣ ነግረዋቸዋል።
«አሁን ምን ሊፈርሙ እንደሆነ እናውቃለን። እኛ ደሴት ድረስ መጥተው አሁን የሚያደርጉትን በማድረግዎ በእውነት ሊያፍሩ ይገባል ምን ሊፈርሙ እንደሆነ እናውቃለን።ይህ የኛ ሀገር ነው።የርስዎ አይደለም በሚሰሩት ሥራ በጣም ማፈር አለብዎት።»
ጆአንሰን በወቅቱ የነዋሪዎቹ ትዕግሥት መሟጠጡን እንደተረዱ ተናገረው አንድ የጋራ የአውሮጳ የፍልሰት ፖሊሲ አለመውጣቱ ባለፉት ዓመታት ግሪክን የመሳሰሉ ሃገራት ከፍተኛ ጫና ውስጥ እንዲወድቁ አድርጓል ብለዋል።
«ባለፉት ስድስት ዓመት አውሮጳ ውስጥ የተመለከትነው የጋራ የአውሮጳ የጋራ የፍልሰት ፖሊሲ መጉደሉን ነው።ማለት የኛ የውጭ ድንበራችን የሆኑት አባል ሃገራት ከፍተኛ ጫና ውስጥ ነበሩ።በተለይ አንዳንድ ደሴቶች አውሮጳዊ መፍትሄ ባለመኖሩ ከባድ ጫና ውስጥ ወድቀዋል።እኔ የምለው ይህ ተቀባይነት የለውም።የፍልሰትን ጉዳይ የመላው አውሮጳ ጉዳይ ማድረግ አለብን፤ማናቸውንም አባል ሃገርም ይሁን ደሴት ወደ ጎን መተው የለብንም።»
ግሪክን ጨምሮ ስደተኞች ወደተቀረው አውሮጳ የሚሸጋገሩባቸው ኢጣልያ ስፓኝ ቆጵሮስና ማልታ የአውሮጳ ኅብረት የተቀናጀ የአውሮጳ የጋራ የፍልሰት መርህ እንዲወጣ በተደጋጋሚ ጥሪ ሲያቀርቡ ነበር።ሌሎች አባል ሃገራት ስደተኞችን በመከፋፈል እንዲተባበሩም ሲጠይቁ ቆይተዋል። ስደተኞች በብዛት ወደ አውሮጳ በገቡበት በጎርጎሮሳዊው 2015 ዓም ቁጥራቸው አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ስደተኞች ነበሩ በጀልባ ከቱርክ ወደ ግሪክዋ ሌስቦስ ደሴት የገቡት። በዓመቱ የአውሮጳ ኅብረትና አንካራ ውል ከተፈራረሙ በኋላ በቱርክ በኩል ወደ ግሪክ የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር በጣም ቀነሰ።የስደተኞቹ ቁጥር በየዓመቱ እየቀነሰ አምና ግሪክ የገባው ስደተኛ በተመድ መረጃ መሠረት ከ16 ሺህ ብዙም የሚበልጥ አልነበረም።የግሪኩ ሚኒስትር ሚታራቺ እንዳሉት በአሁኑ ጊዜ ግሪክ በሚገኙ 5 ደሴቶች ውስጥ 14 ሺህ ስደተኞች አሉ።ከሁለት ዓመት በፊት ግን በደሴቶቹ የነበሩት ስደተኞች ብዛት 42 ሺህ ነበር።አሁን ግሪክ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ መጠለያዎች ውስጥ ያሉት ስደተኞች ቁጥር ደግሞ 58 ሺህ ነው።የዛሬ ሁለት ዓመት ግን 92 ሺህ ነበር።ግሪክ ከተጠለሉ ስደተኞች 162ቱ ባለፈው ሳምንት ከሌስቦስ ወደ ጀርመን ተወስደዋል።ከዚያ ቀደም ሲልም 1215 ስደተኞች ከሌስቦስ ጀርመን ገብተዋል።እነዚህ ከለላ እንደሚያሻቸው በባለሥልጣናት ተረጋግጦላቸው ግሪክ እንዲቆዩ የተፈቀደላቸው ስደተኞች ናቸው።ይህን መስፈርት የማያሟሉ ስደተኞች ግን ወደ ሃገራቸው መመለስ እንዳለባቸው ነው ጆአንሰን የተናገሩት።
«ዓለም አቀፍ ጥበቃ ሊደረግላቸው የሚገባውን እንቀበላቸዋለን።ይህ የማይገባቸው ደግሞ ወደ መጡበት ሃገር መመለስ አለባቸው።እናም ይህ ስደተኞችን በአውሮጳ ዓቀፍ ደረጃ መመለስ የምንችልበት ስርዓት፤ማሻሻያ ልናደርግበት የሚገባ አንድ ጉዳይ ነው።እናም አሁን ቱርክ ቃል በገባችው መሠረት ከግሪክ የሚመጡትን ስደተኞች መቀበሏ አስፈላጊ ነው።የአውሮጳ ኅብረትም ስደተኞቹን ከቱርክ መልሶ ማስፈሩን ቀጥሏል።እናም ቱርክ ስደተኞችን ከግሪክ መቀበሏን እንድትቀጥል ጥሪ አቀርባለሁ።»
ቱርክ የምትወስደው ግሪክ ውስጥ የስደት ማመልከቻቸው ተቀባይነት ያላገኘውን ስደተኞች ነው። ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የ27 ቱ የኅብረቱ አባል ሃገራት ትብብር አስፈላጊ መሆኑንም ጆአንሰን ጠቁመዋል። የአውሮጳ ኅብረት ችግሩን ይፈታል የተባለ አዲስ የጋራ የፍልሰት ሕግ ለማውጣት በሂደት ላይ ነው።የስደተኞች መብት ተሟጋቾች ግን ኅብረቱን መውቀሳቸውን ቀጥለዋል።የህክምና እርዳታ የሚሰጠው ድንበር የለሹ የሐኪሞች ቡድን በምህጻሩ MSF ትናንት ለጆአንሰን በጻፈው ደግልጽ ደብዳቤ ተገን ጠያቂዎች የአውሮጳ ኅብረት በገንዘብ ከሚረዳቸው ከግሪኮቹ ደሴቶች የስደተኞች መቀበያ ማዕከላት እንዳይወጡ ተደርገው፣አምስት የክረምት ጊዜያት በማሳለፍ ለስነ ልቦና ቀውስና ለተለያዩ ችግሮች በአንዳንድ ሁኔታዎች ደግሞ ለሞት መዳረጋቸውን ጠቅሷል።በደብዳቤው በደሴቶቹ ኑሮ ለስደተኞች አስከፊ እንደሆነ የገለጸው MSF ይህ ችግር እንዲፈጠር ሆን ተብሎ ያልተደረገ አይደለም።የአቅም እጦት የሃብት ችግርም አይደለም ፤ በማለት ወቅሷል።
ኂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ