1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሶማሊያ፣-አዲስ ተስፋ?

ሐሙስ፣ ጥቅምት 11 1997

ካይሮ፣ዋሽንግተንን ሲረግጡ ተፈፀሙ።ያቺ ሐገርም ፈረሰች።የፈረሰችዉን ለማቆም-ከአይዲድ እስከ ዓሊ መሕዲ መሐመድ፣ ከሞርጋን እስከ አብዲ-ቃሲም ሳላድ ሐሰን፣ ያደረጉት ሙከራ ሁሉ የዉሐ ሽታ ሆኗል።ዩሱፍ ይሳካላቸዉ ይሆን።

https://p.dw.com/p/E0kq
ከሞት ለማምለጥ-ስደት--ሶማሊያ
ከሞት ለማምለጥ-ስደት--ሶማሊያምስል AP


ነጋሽ መሐመድ


ሙላሕ መሐመድ ቢን አብዱላሕ ከነፃነት ሌላ የጠየቁት ነገር አልነበረም።በቅኝ ገዢ ጠላታቸዉ-እብድ ተብለዉ ተገደሉባት።የብሪታንያ ቅኝ ገዢዎችና የኢጣሊያ ብጤዎቻቸዉ ነፃነት ጠያቂዉን እሁለት መግመሱ ለዘመናት ሠጥ ለጥ አድርገዉ መግዛቱ አልገደዳቸዉም።ግን እንደአጀመመራቸዉ አልዘለ ቁባትም።ጥለዋት ወጡ።የዓሊ ሸርማርኬ መንግሥት ሪፐብሊክ ብሎ ሲያዋሕዳት ቅኝ ገዢዎች እንጂ ሕዝቧ የሚለያይባት አይደለችም አሰኝቶ ነበር።ሸርማርኬ ተዋርደዉ አለፉባት።ዚያድ ባሬ በሪፐብሊኩ ላይ ዲሞክራሲያዊ የሚል ቅፅል አክለዉባት እንደ ኮሚንስቶቹ ወግ ሲገዟት የምሥራቅ አፍሪቃ ሶሻሊስቶች-መናኸሪያ ተመስላ ነበር።ሶማሊያ።-ከመምሰል አላለፈችም።ባሬ ከሞስኮ-ካይሮ፣ዋሽንግተንን ሲረግጡ ተፈፀሙ።ያቺ ሐገርም ፈረሰች።የፈረሰችዉን ለማቆም-ከአይዲድ እስከ ዓሊ መሕዲ መሐመድ፣ ከሞርጋን እስከ አብዲ-ቃሲም ሳላድ ሐሰን፣ ያደረጉት ሙከራ ሁሉ የዉሐ ሽታ ሆኗል።ዩሱፍ ይሳካላቸዉ ይሆን።

-----------------------

ባለፈዉ ሳምንት ሐሙስ ናይሮቢ-ኬንያ ዉስጥ በተከበረዉ የፕሬዝዳንት አብዱላሒ ዩሱፍ አህመድ ቃላ መሐላ ላይ በክብር እንግድነት ከተገኙት የሐገር መሪዎች አንዱ የዩጋንዳዉ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ካጉታ ሙሳቬኒ እንደ ብዙዉ አለም ሁሉ የሶማሊያ ሁኔታ በቅጡ የገባቸዉ አይመስልም።ሶማሊያ አንድ ሐገር ናት።አንድ ሕዝብ፣ አንድ ሐይማኖት---እና ችግሩ ምንድነዉ---ጠየቁ ሙሳቬኒ።» መለሱም። «የሶማሊያ ችግር የአፍሪቃን ችግር እጅግ በገዘፈ ሁኔታ የሚያንፀባርቅ ነዉ።የሶማሊያ ችግር አለመበልፀግ ነዉ----»እያሉ

እንደ ብዙዎቹ ቅኝ ተገዢ የአፍሪቃ ሐገራት ሕዝብ ሁሉ የዛሬዋ ሶማሊያ ሕዝብ የቅኝ ገዢዎችን ዘግናኝ አጋዛዝ-በመቃወም ማመፅ የጀመረዉ የብሪታያ ቅኝ ገዢዎች እግራቸዉ እዚያች ምድር ገና ከማሳረፋቸዉ ነበር።የብሪታንያ ሶማሊ ላንድ ያሉትን ግማሽ-ሶማሊያን በምክትል ኮሚሽነርነት ይገዙ የነበሩት ጄኔር ሕዳር-1900 (ዘመኑ በሙሉ እንደ አዉሮጳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) በአመፁ ሶማሊያዎች ሲገደሉ ግድያዉ የሶማሌ ሕዝብ የነፃነት ትግል የመጀመሪያዉ ምልክት መሆኑን ቅኝ ገዢዎች አልተቀበሉትም።

እንዲያዉም የብሪታንያዉን ከፍተኛ ባለሥልጣን የገደሉትን ሐይላት የሚመሩት መሐመድ ቢን አብደላ የተባሉ ሙላሕ መሆናቸዉን ቅኝ ገዢዎቹ ሲያዉቁ ሰዬዉን በተከታዮቻቸዉ ዘንድ ለማስጠላት «እብዱ ሙላሕ» እያሉ ከዉጊያ በመለስ ያለዉን ሁሉ ለማድረግ ሞክረዉ ነበር።አልቻሉም።የብሪታንያ ቅኝ ገዢዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱ የመጡት የአብድላሕ ተከታዮች ለአገዛዝቸዉ አስጊ መሆናቸዉን ሲረዱ ከፊል ሶማሊያን ይገዙ የነበሩ የጣሊያን ብጤዎቻቸዉን አስከትለዉ በቢን አብዱላና በተከታዮቻቸዉ ላይ ዘመቱባቸዉ።

በአፍሪቃ የብሪታንያዉ የጦር አዛዥ ጄኔራል ማኒንግና የጣሊያኑ ተወካይ ኮዉንት ሎቫቲ የካቲት 1903 ባደረጉት ሥምምነት መሠረት የዘመተዉ በብዙ ሺሕ የሚቆጠር የሁለቱ ቅኝ ገዢዎች ጦር ቢን አብደላን ያኔ ኦቢያ ይባል ከነበረዉ የሰሜን ሶማሊያ የወደብ ከተማ ድረስ አባሮ ሲገድላቸዉ የሶማሌ የነፃነት ትግል በጅምር ተቀጨ።

ከሶማሊያ ሕዝብ ዘጠና በመቶ የሚሆነዉ ሶማሌ ነዉ።የተቀረዉ አስር ከመቶ-የባንቱ ጎሳ አባል።ሕዝቡ በመቶ በመቶ የሱኒ እስልምና ተከታይ ነዉ።ቋንቋዉ መቶ በመቶ ሶማሊኛ ነዉ።በሁሉም መስክ አንድ የሆነዉን ሕዝብ ለዘመናት እሁለት የከፈሉት ቅኝ ገዢዎች ጥለዉት ሲወጡ አንድነቱን መልሶ የማይገነባበት ምክንያት ለማንም አልታየም ነበር።ብሪታንያና ኢጣሊያ ለሁለት ተቃርጠዋቸዉ የነበሩት ደቡብና ሰሜን ሶማሊያ በየፊናቸዉ ከየቅኝ ገዢዎቻቸዉ ነፃ በወጡ ማግስት ሐምሌ-1960 እንደ አንድ ሐገር አንድ ባንዲራ ሠቅለዉ አንድ መንግሥት ሲያቆሙ በዘር በሐይማኖት፣ በስነ-ልቡና አንድ የሆነዉ ሕዝብ አንድነቱን እንደጠበቀ ይኖራል አሰኝቶም ነበር።

በከነፃነት ማግሥት ሥልጣን የያዙት የሶማሊያ ገዢዎች-ያዙት በነበረዉ ጦር ሐይል ከሥልጣን መወገዳቸዉ፣ በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን ያዩዙት ሁለተኞቹ የሶማሊያ ገዢዎች አለቆቻቸዉን በመፈንቅለ መንግሥት ማስወገዳቸዉም ሆነ ፣ሥልጣን እንደያዙ ሶሻሊዝምን ማወጃቸዉ በድፍን አፍሪቃ የታየ-የዩጋንዳዉ መሪ እንዳሉትም የአፍሪቃን ፖለቲካዊ ሁኔታ በግልፅ የሚያንፀባርቅ እዉነታ ሊሆን ይችላል።ከአምባ ገነኑ የመሐመድ ዚያድ ባሬ መንግሥት በሕዋላ ያቺ ሐገር ከሁለትም በላይ እሰወስት መሰንጠቅዋ-ድፍን አስራ-ሰወስት አመት መንግሥት አልቦ መተራመስዋ ግን ከአፍሪቃ ይሁን ከተቀረዉ አለም በዘመናችን አምሳያ ሊገኝለት አይችልም።

ሶማሊያ አቻ ከማይገኝለት ድቀት ለመድቀቅዋ የዩጋንዳዉ መሪ እንዳሉት ድሕነት አንዱ ምክያት ሊሆን ይችላል።ቅኝ ገዢዎች ቀብረዉት የሔዱት፣ ሐያላን ያራገቡት የግዛት፣ የጎሳ፣ የጎጥ ክፍፍል-ሌላዉ ።የሶማሌ ሕዝብ ከባሕላዊዉ የጎሳ አስተዳደር ወደ ዘመናዊዉ የመንግሥት አገዛዝ የሚያደርገዉን ሽግግር ሙሉ በሙሉ አለመጨረሱ ለብልጣብልጥ ፖለቲከኞች ለዉጪዎቹም ሐይሎች ጥሩ መሳሪያ መሆኑም መዘንጋት የለበትም።

ከነፃነት በሕዋ የመንግሥትነቱን ሥልጣን የያዙት ወገኖች---ቅኝ ገዢዎች የቀበሩት የመከፋፈል፣ የመጠላላት፣ የመናናቅ አደገኛ ቂም-ቁሮሾን ከየሕዝባቸዉ አዕምሮ ለማጥፋት፣-የሐገሪቱን የምጣኔ ሐብት አቅም ለማደርጀት፣ ከየአጎራባቾቹ ጋር መልካም ወዳጅነትን ለመመስረት ከመጣር ይልቅ-የተጋሊቢጦቹን ማድረጋቸዉ ለሆነዉ ሁሉ መሆን ዋናዉ ምክንያት ነዉ።

ሸርማርኬም ሆኑ ባሬ ፣ ባለአምስት ኮኮብ ባንዲራ ሰቅለዉ ጀቡቲን በጠቅላላ፣ የኢትዮጵያዉን ኦጋዴን፣ የኬንያን ሰሜን-ምሥራቅ ግዛት ለመጠቅለል-መባተላቸዉ፣ አለ-ቅማቸዉ ትንሺቱን ሐገር በታላቅነት እብሪት መወጠራቸዉ፣ አልፈዉ ተርፈዉ ከሁለቴ በላይ ጎረቤቶቻቸዉን መውረራቸዉ ሶማሊያን በዘር፣ በሐይማኖት፣ በቋንቋ፣ በመልክ፣ በሥነ-ልቡና በምጣኔ ሐብት አቅም አንድ መሆን ባንድነት ለመኖር ፍቅር እንደማይሆን ለአለም አይነተኛ ምናልባት የመጀመሪያዋ ምሥሌ አድርገዋታል።
-----------------------

የብሪታንያዉ የዜና ማሰራጪያ ጣቢያ ቢቢሲ የጠቀሳቸዉ አንድ የድሮ ጓደኛቸዉ እንደሚሉት በዩስፍ እምነት «አንድም ከኮለኔሉ ጋር ነሕ አለያም ጠላት ነሕ።»ሥልሳ ዘጠነኛ እድሜያቸዉን ያገባደዱት አብዱላሒ ዩሱፍ አሕመድ እንደ ብዙ የእድሜ አቻ ወገኖቻቸዉ አያሸርጡም።በሙሉ ሱፍ ቂቅ ማለቱን ይወዳሉ።አይጠመጥሙም። በካራቫት ማሸብረቁን-ነዉ የሚፈቅዱት።አይጠጡም።አያጨሱም። ሶማሊያ ነፃ ከመዉጣትዋ በፊት ጀምሮ ወታደራዊዉን ሙያ ከነግብሩ ተክነዉበታል።ኮሎኔል ናቸዉ።በ1969 በተደረገዉና መሐመድ ዚያድ ባሬ በመሩት መፈንቅለ መንግሥት አልካፈልም በማለታቸዉ መፈንቅለ መንግስት አድራጊዎች መንግሥት ሲሆኑ ወሕኒ ወርዉረዋቸዉ ነበር።

ያኔ እንደእሳቸዉ ሁሉ ታስረዉ ከነበሩት የጦር መኮንን መሐመድ ፋራህ አይዲድ ጋር ወሕኒ ቤት የጀመሩት ወዳጅነት ከወጣትነታቸዉ ጀምሮ የሰረፃቸዉን ፖለቲካዊ እዉቀት እንዲያዳብሩት ምክንያት ሆኗቸዋል።ኢጣሊያና ሶቬት ህብረት የተማሩትን የኮሎኔልነት ማዕረግ የጫኑበትን ወታደራዊ ክሒል ወሕኒ ካዳበሩት ፖለቲካዊ ፍላጎት ጋር አቀናጅተዉ--ከእስር በተፈቱ በሰወስተኛዉ አመት-በ1978 የዚያድ ባሬን መንግሥት ለመግልበጥ ሞከሩ።አልተሳካላቸዉም።ወደ ኬንያ ኮበለሉ።

ዳሮን የተባለዉ ጎሳቸዉ ከትላልቆቹ የሶማሊያ ጎሳ አንዱ ነዉ።የተወለዱበት ፑንት ላንድ ከሰወስቱ የሶማሊያ ዋና ዋና ግዛቶች-አንዷ ነች።የጦር አዋቂነታቸዉ፣ የፖለቲካ ብስለታቸዉ፣ የተወለዱበት ጎሳና አካባቢ በቀላሉ ብዙ ተከታይ እንዲኖራቸዉ መርዳቱን ጠንቅቆ ያወቀዉ የድሞዉ የኢትዮጵያ መንግሥት የሞቃዲሾ ጠላቶቹን ለማንበርከክ-ኮሎኔሉን ኬንያ ድረስ አስፈልጎ ይረዳቸዉ ገባ።ኮሎኔል አብዱላሒ ዩሱፍ የመሠረቱት ደፈጣ ተዋጊ የዚያድ ባሬን መንግስት ለማስወገድ የሚያደርገዉ ዉጊያ እስከየትነት በቅጡ ሳይታወቅ ኮሌኔሉ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ተጣሉና አዲስ አበባ ወሕኒ ወረዱ።1985።

የቀድሞዉ የኢትዮጵያ መንግሥት በ1991 እንደተወገደ ከእስር ቤት የተፈቱት ዩሱፍ ወደ ትዉልድ ሐገራቸዉ ፑንት ላንድ ሲመለሱ ተቀባያቸዉ እጅግ ነበር።ሞቃዲሾና ሌሎቹን የሶማሊያ ግዛት ያወደመዉ የጦር አበጋዞች ዉጊያ ፑንት ላንድን ብዙ እንዳይነካት ተከላክለዋል።የግዛቲቱን ተቀናቃኞቻቸዉን አስወግደዉ ነፃ መንግሥት አከል እተዳደር ከመሠረቱበት ከ1998 ወዲሕ ደግሞ በአካባቢዉ ዝናቸዉ ገንኖ ተከታያቸዉም በርክቷል። አመራራቸዉ ግን የቀድሞ ጓደኛቸዉ እንዳሉት ከፖለቲካ ብልጠት ይልቅ ወታደራዊዉ ሐይል የሚያልበት ነዉ።

ክሪስቲያኖች ከሚበዙበት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ጠንካራ ወዳጅነት መመሥረታቸዉ ብዙ ወገኖቻቸዉን ቅር ማሰኘቱ፣ ለተቃዋሚዎቻቸዉ የጥላቻ ዘመቻ ምክንያት መሆኑ አልቀረም።በ1992 ዘመቻ ተስፋ መልስ በሚል ሥም የዘመተዉ የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ከጀኔራል ፋራሕ አይዲና ከተከታዮቻቸዉ ጋር ደም ሲቃባ ዩሱፍ የሐይል ሚዛን አስልተዉ ከጠቡ መራቃቸዉ የአሜሪካኖችን ወዳጅነት አትርፎላቸዋል።ነሐሴ-2000 አርታ ጅቡቲ ዉስጥ የተሰየመዉ የሽግግር ብሔራዊ መንግስት የአለም ሐያላንን ድጋፍ፣ የጦር አበጋዞችን ትብብር፣ የሕዝቡን ተቀባይነት ከማግኘቱ በፊት ከአረቦች ጉያ ለመደበቅ መሞኮሩ አገዛዙ ከሞቃዲሾ አንዲት መንደር ሳያልፍ በጅምር አስቀርቶታል።ሸርማርኬ. ባሬ፣ አይዲድ፣ መሕዲ፣ ሐሰን ሌሎችም የሠሩትን ሥሕተት ላለመድገም የሞከሩት ዩሱፍ ባለፈዉ ሐሙስስ ለቃለ መሐላ ለተቀበሉት ሥልጣን እንዲበቁ ረድቷቸዋል።ፈተናቸዉ ግን ገና መጀመሩ ነዉ።

-------------------------

ዩራኒየም፣ ብረት፣ ቆርቆሮ፣ መዳብ፣ የከበረ-ድንጋይ፣ ጨዉ፣ የሚገኝባትን፣ ጋስ፣ የተነጠፈባትን፣ ምናልባት አጥኚዎች እንደሚሉት ነዳጅ ዘይት የማታጣዉን ሐገር-ሐገር ለማድድረግ የመሪዎቿ ብስለት ወሳኝ ነዉ።የቡሳሶ፣ የበርበራ፣ የኪስማዩ፣ የሜርካና የሞቃዲሾ ወደቦች፣ ከጠመንጃ ማመላለሻነት ተላቀዉ ለልማት ሸቀጦች እንዲዉሉ-አብነቱ የሶማሌያ መሪዎች ነዉ።ፕሬዝዳንት ዩሱፍ ቃለ መሐላ ሲፈፅሙ ለጠላቶቻቸዉ ይቅርታ ማድረጋቸዉን አስታዉቀዋል። እነሱም ይቅር እንዲሏቸዉ ጠይቀዋል።የዉጪዉን እርዳታ ተማፅነዋል።እርዳታዉ እንዲመጣ፣ የተበታተነችዉ ሐገር ሐገር እንድትሆን ሶማሌዎችን በርግጥ አለምም ሊያግዛቸዉ ይገባል።