1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሶማሊያ፥አዲስ ጅምር ከምንም

ሰኞ፣ ግንቦት 5 2005

ሶማሊያ ከ20 ዓመታት በላይ ያለ ቋሚ መንግስት ቆይታለች። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በሶማሊያ በርካታ ተቋማት ፈራርሰዋል። እናም በለንደኑ የሶማሊያ ጉባኤ ለጋሽ አገራት የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባታቸው ታውቋል። በምዕራብ አፍሪቃዊቷ ቲምቡክቱስ የፈረንሳይ ጦር ከሰፈረ ወዲህ የነዋሪዎቹ የዕለት ተዕለት የኑሮ ሁናቴ ምን ይመስላል?

https://p.dw.com/p/18VxP
ምስል AFP/Getty Images

ባሳለፍነው ማክሰኞ (29.08.2005 ዓ.ም.)ለንደን ውስጥ ሶማሊያን የሚመለከት ዓለም አቀፍ ጉባኤ ተካሂዶ ነበር። የጉባኤው ጋባዥ የብሪታንያው ጠቅላይ ሚንስትር ዴቪድ ካሜሩንና የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሐሠን ሼክ መሐመድ ነበሩ። በጉባኤው ከ50 አገራት የተውጣጡ ልዑካናትና የተለያዩ የዓለምአቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች ተካፋይ ሆነዋል። ጉባኤተኞቹ ለዓመታት በእርስ በእርስ ግጭት የተዳቀቀችው የአፍሪቃ ቀንዷ ሶማሊያን የፀጥታ፣ የገንዘብና የሕግ ስርዓት ለመገንባት የሚያስችል የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግም ተስማምተዋል። ለ20 ዓመታት ያህል መንግስት አልባ በነበረችው ሶማሊያ የምጣኔ ሀብቱና የባንክ ስርዓቱ ተንኮታኩቶ ነው የቆየው። ሆኖም የመልሶ ግንባታው ተጀምሯል።

የብሪታንያው ጠቅላይ ሚንስትር ዴቪድ ካሜሩንና የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሐሠን ሼክ መሐመድ
የብሪታንያው ጠቅላይ ሚንስትር ዴቪድ ካሜሩንና የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሐሠን ሼክ መሐመድምስል Getty Images
የሶማሊያ ጉባኤ በለንደን
የሶማሊያ ጉባኤ በለንደንምስል Getty Images

ሞቃዲሾ የሚገኘው የባካራ ገበያ ከአፍሪቃ ትልልቅ ገበያዎች መካከል እንደ አንዱ ይቆጠራል። በጠባቦቹ ሰርጣ ሰርጦች ውስጥ ፍራፍሬና ከብቶች፣ ጫማዎች፣ የቤት ቁሳቁሶች፣ ገንዘብ በአጠቃላይ ለኑሮ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ሁሉ ይገበይበታል። ገንዘብ መንዛሪዎች ከፊት ለፊታቸው የሶማሌ ሽልንግ ኖታዎችን ቆልለው ነው የሚውሉት። የአሜሪካ ዶላሩን ግን ሌላ አስተማማኝ ቦታ ነው የሚቆልፉበት። እነዚህ ገንዘብ መንዛሪዎች ጋር ዩሮ ሳይቀር ይመነዘራል። ለእዚያውም ወቅታዊ የዓለም አቀፍ ምንዛሪን መሰረት ባደረገ መልኩ። እውጭ አገራት ለሚኖሩ ዘመዶቹ ገንዘብ ለመላክ የፈለገ ሰው ወይንም ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ እንደሚሆነው እውጭ አገራት ካሉት ዘመዶቹ ገንዘብ የሚላክለት ሰው አገልግሎት ለማግኘት በእስላማዊው መርህ ወደሚተዳደሩት (ወለድ ወደማይከፈልባቸው) ባንኮች ማቅናት ይኖርበታል። ከሃያ ዓመታት በላይ በመላ ሶማሊያ ለቁጥር እንኳ አንድ የሚባል ዓለም አቀፍ ባንክ አይገኝም። ይህ አሁን መቀየር ይኖርበታል።

«ስልታዊ በሆነ መልኩ የባንክ አገልግሎቶችን እየዘረጋን ነው፣ ስዊፍት ኮዶችን በመጠቀም ዓለም አቀፋዊ የባንክ አሰራሮችን በማስተዋወቅ ላይም እንገኛለን። በእዚያ መንገድ ማንኛውም ሶማሌያዊ ገንዘብ ማስገባትም ሆነ ወደ ተቀረው ዓለም መላክ ይችላል።»

አብዱልሠላም ዑመር ከባለፈው ጥር ወር አንስቶ የሶማሌ ማከላዊ ባንክ ሃላፊ ሆነው ተመድበዋል። ከእዚያ በፊት የ58 ዓመቱ ሶማሌ አሜሪካዊው የባንክ ባለሙያ በዋሽንግተን ከተማ ከንቲባ ስር ሆነው ነበር ያገለግሉ የነበረው። የእዚያን ጊዜው ሃላፊነታቸው መዲናይቱን ከፋይናንስ ውድቀት መታደግ ነበር። አሁን ከተሰጣቸው ሃላፊነት ጋር በትንሹም ቢሆን ይዛመዳል። ዑመር በጦርነት የተዳቀቀችውን የትውልድ አገራቸውን ከወደቀችበት አንስተው በሁለት እግሮቿ እንድትቆም መርዳት ይጠበቅባቸዋል።

«ከ22 ዓመታት በላይ አንድም ማዕከላዊ ባንክ አልነበረም። ሁሉንም ዳግም እየገነባን ነው። በእየቀኑ አንድ ርምጃ ወደፊት እያቀናን ለውጥ እያመጣን ነው፤ ሆኖም ገና ረዥም መንገድ ከፊታችን ይጠብቀናል።»

የሶማሊያ ጉባኤ በለንደን
የሶማሊያ ጉባኤ በለንደንምስል AFP/Getty Images

በዓለም አቀፍ መመዘኛ ሲቃኝ የሶማሊያ ማዕከላዊ ባንክ ስያሜው የሚገባው አይነት አይደለም። ባንኩ የሶማሊያ መገበያያ የሆነው ሽልንግ በተቀማጭነት የለውም። ለመጠባበቂያ የሚባል ገንዘብም የለውም። በማዕከላዊ ባንኩ ቁጥጥር ስር መዋል የሚገባው የንግድ ባንክም አይታይም። ይህ ሁሉ መቀየር አለበት ነው የሚሉት የማዕከላዊ ባንኩ ኃላፊ ። ሶማሊያ ዓለም አቀፍ ግንኙነቷን ከሃያ ዓመታት በላይ አቋርጣ በዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም IMF እንኳን ዕውቅና ካገኘች ገና አንድ ወርም አላለፋት። እንዲያም ሆኖ ሶማሊያ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም የ270 ሚሊዮን ዩሮ ዕዳ አለባት፤ ያም በመሆኑ ከተቋሙ በአሁኑ ወቅት አንዳችም አዲስ ብድር አታገኝም። ይሁንና፤ አብዱሣላም ዑመር የማዕከላዊ ባንኩን ከዓለም አቀፍ የባንክ አሰራር ጋር በማቀናጀት ነፍስ እንዲዘራበት ጥረት ማድረግ ይሻሉ።

«ስለእዚህም የቁጥጥርና የፍቃድ ክፍሉን በአንድ ላይ ማዋቀር እንፈልጋለን። ከእዚያም ባሻገር ኢኮኖሚው ላይ አስተማማኝ ውሳኔዎችን ማሳለፍ ያስችለን ዘንድ መረጃዎችን የምንሰበሰብበት የጥናት ቡድን ማቋቋም እንሻለን። እናም አሁን ያለንበት ደረጃ ኢኮኖሚው ቁጥጥር ሳይሆን አስተዳደር የሚያስፈልግበት ነጥብ ላይ ነው። እንደ ማዕከላዊ ባንክ ዓለም አቀፋዊ የገንዘብ ለውጦች ምን ይመስላሉ የሚለውን ማስተዳደር እንሻለን። የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር፣ የአገር ውስጥ መገበያያው አቅሙ ምን ያህል ነው የሚለውን ማየት ያስፈልጋል። እነእዚህ ሁሉ ነገሮች መተግበር አለባቸው። የሚተገበሩም ናቸው ግን ለመተግበር አዳጋች።»

ታዲያ ዋነኛ ችግሬ ብቃት ያላቸው የባለሙያዎች ዕጥረት መኖሩ ነው ይላሉ ባንከኛው። የሶማሌ መንግስት በካዝናው አንዳች ገንዘብ የለውም በሚባልበት በአሁኑ ወቅት ብቃት ያላቸውን ሰዎች አወዳድሮ መቅጠሩ የሚቻል አይመስልም። ያም በመሆኑ ዑመር አንድ ነገር ላይ ተስፋ ጥለዋል። ልክ እንደእሳቸው ሁሉ በውጭ አገራት የሰለጠኑ ብቃት ያላቸው በርካታ ባለሙያዎች ወደ አገራቸው ተመልሰው መሰል አገልግሎት ሊሰጡ ይችሉ ይሆናል የሚል ተስፋ። ምንም እንኳን ሶማሊያ አሁንም ድረስ የጦርነት ዳመና ባይለያትም ለአገሪቱ የተሰነቀ ተስፋ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

መስፍን መኮንን

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ