በሃዲያ ዞን የቀጠለው የሥራ ማቆም አድማ
ሰኞ፣ ጥቅምት 12 2016
አገልግሎት የተቋረጠባቸው የምሥራቅ ባድዋቾ ወረዳ ነዋሪዎች
የህክምናና የትምህርት አገልግሎት በመቋረጡ መቸገራቸውን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሃድያ ዞን የምሥራቅ ባድዋቾወረዳ ነዋሪዎች ገለፁ። ነዋሪዎቹ እንዳሉት የወረዳው ሀኪሞችና መምህራን ደሞዝ አልተከፈለንም በሚል ሥራ ካቆሙ ሁለት ሳምንት አስቆጥረዋል፤ በዚህ ምክንያትም ልጆቻቸው ቤት ለመዋል ተገደዋል፤ የታመሙ ሰዎችም ህክምና ለማግኘት ተቸግረዋል።
በሃድያ ዞን ምሥራቅ ባድዋቾ ወረዳ የሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች የጀመሩት የሥራ ማቆም አድማ ዛሬ ሰኞ ሁለተኛ ሳምንቱን አስቆጥሯል። ሠራተኞቹ የሥራ ማቆም አድማውን ማካሄድ የጀመሩት ካለፈው ሐምሌ ጀምሮ ያለው ደሞዛቸው እንዲከፈላቸው በመጠይቅ ነው።
በሠራተኞቹ አድማ የተነሳ በወረዳው የሚገኙ መንግሥታዊ ተቋማት አሁን ድረስ አገልግሎታቸው እንደተስተጓጎለ የወረዳው ነዋሪዎች ተናግረዋል። በተለይም የሾኔ ሆስፒታልን ጨምሮ የህክምና ተቋማትና ትምሀርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ በመዘጋታቸው ለከፍተኛ ችግር መዳረጋቸውን ነው ነዋሪዎቹ ለዶቼ ቬለ የገለጹት። በወረዳው በሠራተኞች ደሞዝ አለመከፍል ምክንያት የተቋረጡ የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን ለማስቀጠል በአካባቢው ባለሥልጣናት በኩል የሚደረግ ጥረት አለመኖሩን የጠቀሱት ነዋሪዎቹ «ችግሩ ከወረዳ፣ ከዞኑና ከክልሉ አቅም በላይ የሆነ ይመስላል። የፌዴራሉ መንግሥት ያለንበትን ሁኔታ አይቶ መፍትሄ እንዲሰጠን እንፈልጋለን። ጥያቄያችንን ለማቅረብም በወከልናቸው ሰዎች አማካኝነት ወደ አዲስ አበባ ለመሄድ ዝግጅት እያደረግን እንገኛለን» ብለዋል።
ዶቼ ቬለ በነዋሪዎቹ ቅሬታ ዙሪያ የምሥራቅ ባድዋቾ ወረዳ አስተዳደር፣ የሃድያ ዞን የሰው ሀብት ልማትና የመንግሥት አገልግሎት መምሪያ እና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የፋይናንስ ቢሮ ሃላፊዎችን ለማነጋገር ጥረት አድርጓል። ይሁንእንጂ ባለሥልጣናቱ «ስብሰባ ላይ ስለሆንን ቆይታችሁ ደውሉ» ባሉት መሠረት ቢደወልላቸውም አንዳንዶች ጥሪ አይመልሱም፤ የተቀሩት ደግሞ ሥልካቸው በመዘጋቱ ምላሻቸውን በዚህ ዘገባ ማካተት አልተቻለም።
ያም ሆኖ የአካባቢው ባለሥልጣናት ትናንት እሑድ የሾኔ ሆስፒታል ሠራተኞችን ያነጋገሩ ቢሆንም ከስምምነት ሳይደርሱ መቅረታቸውን አንድ የሆስፒታሉ ሠራተኛ ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል። ሠራተኛው ስብሰባውን ለጠሩት የወረዳው አመራሮች «ሳንበላ ማከም አንችልም» የሚል ምላሽ መሰጠቱን የጠቀሱት እኝሁ አስተያየት ሰጪ «መጀመሪያ ደሞዛችንን አስገቡልንና ወደ ሥራ እንመለሳለን የሚል ምላሽ ከሠራተኛው በኩል ተነስቷል፤ መፍትሄው መክፈል ብቻ ነው ከዚህ ውጭ አማራጭ የለም በሚል ከአመራሮቹ ጋር ከስምምነት ሳንደርስ ቀርተናል» ብለዋል።
ቁጥራቸው ከሁለት ሺህ በላይ የሚሆኑት በሃድያ ዞን የምሥራቅ ባድዋቾ ወረዳ መንግሥት ሠራተኞች «የሠራንበት የሦስት ወር ደሞዝ ይከፈልን» በሚል ከሁለት ሳምንት በፊት ጀምሮ በሥራ ማቆም አድማ ላይ ናቸው። ለሠራተኞቹ ደሞዝ መክፈል ያልተቻለው የቀድሞው የደቡብ ክልል ለወሰደው የአፈር ማዳበሪያ ብድር የወረዳውን ባጀት በዋስትና በማስያዙ እንደሆነ ከዚህ በፊት የወረዳው ባለሥልጣናት መግለጻቸው ይታወቃል።
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ሸዋዬ ለገሠ
ነጋሽ መሐመድ