በምስራቅ ሸዋ ዞን አደዓ ወረዳ የተፈጸመ እገታ እና ግድያ
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 18 2017
በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን አደአ ወረዳ ጊጬ ገረባቦ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ስድስት ሰላማዊ ዜጎች በታጣቂዎች መገደላቸውን ቤተሰቦች ለዶይቼ ቬለ ገለጹ፡፡
ከወረዳው ዋና ከተማ ቢሾፍቱ ቅርብ ርቀት ላይ በምትገኝ ቀበሌዋ ከሁለት ወራት በፊት ሶስት ሰዎች ላይ የተፈጸመውን የታጣቂዎች እገታ ተከትሎ የታገቱትን ቤተሰቦቻቸውን ለማስለቀቅ የወጡ ተጨማሪ ሶስት ቤተሰቦቻቸው ተጨምረው ከታገቱ በኋላ ስድስቱም መገደላቸውን ታውቋል፡፡
የእገታው አፈጻጸም
ጥቅምት 16 ቀን 2017 ዓ.ም ከምሽቱ ሶስት ሰዓት ግድም ማንነታቸው የማይታወቁ ታጣቂዎች በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን አደአ ወረዳ ጊጬ ገረባቦ ቀበሌ ገበሬማህበር ውስጥ ነዋሪ የሆኑ ታደለ መከተ፣ አስታጥቀው ተበጀ እና ጌቱ ፋንታሁን የተባሉ ሶስት አርሶ አደሮችንአፍነው ይወስዳሉ፡፡ ለእንደነዚህ ላለው ነገር አዲስ ያልሆነው የአከባቢው ማህበረሰብ እና ቤተሰብ ከዚህን ቀደም እንደሚደረገው ሁሉ የታፈኑ ሰዎች ሲያዙ ለማስለቀቅ በማግስቱ እና በሁለተኛው ቀን ስልክ ይደወልና በእያንዳንዱ ታጋች ላይ የገንዘብ መጠን ተጥሎ ወደ ቤተሰብ ይደወላል፡፡ “ይህን ያህል አምጡ ካለበለዚያ እንገድላቸዋለን” የሚል የአጋቾች ማስጠንቀቂያና ቀነ ገደብም በዚሁ ይነገራቸዋል፡፡ በዛ መሃል ነው እንግዲህ ቤተሰብ የሚጠየቀው ገንዘብ እንዲቀንስለት ተደራድሮ ከየትም ብሎ በሚሰጣቸው የመክፈያ አድራሻ ገንዘቡን በመክፈል ቤተሰቦቻቸውን የሚያስለቅቁት የተባለው።
አስተያየታቸውን የሰጡን የአከባቢው ተጎጂ ቤተሰብ ለተለመደው የፀጥታ ስጋት ስባል ስማቸውን እንዳንጠቅስና ድምጻቸውንም እንድንቀይር ጠይቀው በሰጡን አስተያየት፤ “ወንድሙ የታፈነበት ካሳሁን መከተ ታደለ መከተን ለማስለቀቅ አባቷ የተያዘባት ካሰች አስታጥቀው አባትዋን አቶ አስታጥቀው አበጀን ለማስለቀቅ እና አቶ ጌቱ ፋንታሁንን ለማስለቀቅ የአቶ ጌቱ ዘመድ የሆነ ወጣት ታደሰ አበባየሁ በአንድ ላይ ሶስት በመሆን የተጠየቁትን ብር ለማድረስ ይሄዳሉ፡፡ ነገር ግን አጋቾች የተባለውን ብር እንደተቀበሉ ሶስቱንም የቤተሰብ አባላት በዚያው ጨምረውአቸው ያግታሉ” ብለዋል፡፡
የመገደላቸውን መርዶ
በዚህ መሃል ሊከፍሉ የሄዱትም የታገቱትም ሳይመለሱ፤ ቤተሰብም ሆኑ የአከባቢው ማህበረሰብ ይመጡ ይሆናል በማለት ለድፍን ሁለት ወር የተስፋ ዜና ቢጠብቁም ያ አልሆነም፡፡ ታህሳስ 17 ቀን 2017 ዓ.ም ትናነት ሓሙስ ሁሉም እንደተገደሉ ለቤተሰብ መርዶ መጣ፡፡ ይህም ከእያንዳንዱ ቤት ሁለት ሁለት ሰዎች ተገድለዋልና ሀዘኑም መሪር ነው ይላሉ፡፡ “ከዚያም ቤተሰብ ቢጠይቅ ምን ቢል ጸጥ ረጭ ሆነ ነገሩ” የሚሉት የሁለቱ ሟቾች ቤተሰብ አሁን ከአሁን ይመጣሉ በሚል በተስፋ ከመጠበቅ ውጪ ምንም ጠብ አለማለቱን ያስረዳሉ፡፡ “እንግዲህ ትናንትሁላቸውም ሞተው ጉድጓድ ውስጥ ተጥለዋልየሚል ዜና መጣ” በማለት ቤተሰብ ይህን ያህል ጊዜ አለማረፉን፤ ነገር ግን ተመልሰው ሌላ ቤተሰብ ወደ ስፍራው ቢልኩ ተጨማሪውን እገታ ፈርተው መቆየታቸውን አክለው አብራሩ፡፡ እገታው ሌሊት ላይ መፈጸሙንም ገልጸው እገታውን በማን እንደተፈጸመ ቤተሰብ አያውቅም ነው ያሉት፡፡
ለተደጋገመው የጸጥታ ችግር የነዋሪዎች ምሬት
አስተያየት ሰጪ ቤተሰብ ምሬታቸውን ሲገልጹም ገዳዩ የሚፈጸመው በማንም ይሁን በማን ንፁኃንን ማጥቃት እንዲቆም ይጠይቃሉ፡፡ በንፁሃን ላይ የሚደርሰውን ሞት፣ መፈናቀል እና ሰቆቃ እንዲቆምም ይጠይቃሉ፡፡
በአሁኑ በአጠቃላይ ከተገደሉት ስድስት ግለሰቦች ውስጥ አንዷ ሴት ስትሆን ነብሰጡር እና ሰርጓ ሊደገስ ከአንድ ወር በኋላ ለጥር የተያዘ ነበር ተብሏል፡፡ ሟች እጮኛ ቤተሰቦቿን ከድህነት ለማውጣት በአረብ ሀገር ተሰዳ ስትሰራም እንደነበር ተነግሯል፡፡
በዚህ ከቢሾፍቱ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኝ በተባለች የገጠር ቀበሌ አከባቢ ከዚህ በፊት መጋቢት 05 ቀን 2016 ዓ.ም. 7 ሰዎች መታገታቸው፣ ነሐሴ 17 ቀን 2015 ዓ.ም. አቶ ሃይሉ በየነ እና መጋቢት 05/2016 ዓ.ም አቶ ግርማ ገብረጊዮርጊስ የተባሉ የአከባቢው ነዋሪዎች እንዲሁ ታግተው መገደላቸውን የአከባቢው ማህበረሰብ ያስታውሳሉ፡፡
ከዚህ ባሻገር ከሃምሳ ያላነሱ አባወራዎች ንብረታቸውንና የእርሻ መሬታቸውን ትተው ከአከባቢው መሰደዳቸውም ይነገራል፡፡ ከነሃሴ 17 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በዚህ አከባቢ በሚፈጸም ተደጋጋሚ እገታና ግድያ ሰላም ርቆት ቆይቷል የሚሉት አስተያየት ሰጪ፤ ከዚን ጊዜ ወዲህ በርካቶች ሲፈናቀሉ ታግተው የተገደሉት ሰዎች ቁጥር ዘጠኝ ደርሰዋል፡፡ “ከዚን ጊዜ ጀምሮ ቤተሰብ ውጪ ነው የሚድረው እስካሁንም ድረስ፡፡ በመሃል መንግስት ሰላሙን ለማረጋጋት ጥረት አድርጎ የነበረ ቢሆንም ከዚያን በኋላ አስቸጋሪ ሁኔታ ተፈጥሯል” ብለዋልም፡፡
ዶይቼ ቬለ የአከባቢውን ማህበረሰብ ያሰለቸውን ተደጋጋሚ እገታ እና አፈናን ለመከላከል የተሄደበትን እርምጃ ጨምሮ መንግስት በጉዳዩ ላይ ስለሚሰጠው ተጨማሪ አስተያየት በዚህ ዘገባ ላይ ለማከል ያደረገው ጥረት ለዛሬ አልሰመረም፡፡ የምስራቅ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ እና የጸጥታ አካላትን ጨምሮ ለአደዓ ወረዳ አስተዳዳሪ ድሪባ ቶሎሳ ደውለን አስተያየታቸውን ለማከል ብርቱ ጥረት አድርገናል፡፡ ለወረዳው ፖሊስ አዛዥ ጉዳዩን ገልጸን አስተያየታቸውን ለመጠየቅ ስንጥርም ያሉበት ስፍራ ኔትዎርክ በማቆራረጡ ለዛሬ ሃሳባቸውን በቅጡ መቀበል አልተቻለም፡፡
ነዋሪዎች ከአንድ ኣመት በላይ ሆኖታል ያሉት የዚህ አከባቢ የጸጥታው ይዞታ መወሳሰብ በመሃል መንግስት በወሰደው ወታደራዊ ዘመቻ ለወራት እፎይታ ቢገኝም ችግሩ አሁንም መልሶ ማገርሸቱን አስረድተዋል፡፡ አከባቢው ላይ የሚንቀሳቀሱ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነግ-ኦነሰ) መኖራቸውን የሚያስረዱት ነዋሪዎች ለአሁኑ ግድያ ኃላፊነቱን ስለሚወስደው አካል ግን ማረጋገጫ አይሰጡም፡፡ የታጣቂ ቡድኑ የበላይ አመራሮችም በተለያዩ ጊዜያት መሰል ግድያዎችን ሰራዊቶቻቸው እንደማይፈትሙ በመግለት ስያስተባብሉ ተደጋግሞ ተሰምቷል፡፡
ሥዩም ጌቱ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ሂሩት መለሰ