በርካቶችን ግራ ያጋባው የእስረኞቹ መፈታት
እሑድ፣ ጥር 8 2014የኢትዮጵያ መንግሥት በእስር ላይ የቆዩ የተለያዩ የፖለቲካ አመራሮችን ባሳለፍነው ሳምንት ዓርብ መፍታቱ በርካቶችን እጅግ አስደምሟል። በተለይ ደግሞ ከመንግሥት ጋር ጦርነት የገጠመው እና የሀገሪቱ ምክር ቤት በአሸባሪነት የፈረጀው የሕወሓት ከፍተኛ አመራር የነበሩት እና ከጦር ግንባር ተይዘው በእስር የቆዩት ድንገት ክሳቸው ተቋርጦ ነጻ መለቀቅ ብዙዎችን ግራ አጋብቷል፣ በአንድ ወገንም ብርቱ የቁጣ ስሜትም ቀስቅሷል። በሌላ ጎኑ ስለእስረኞቹ መለቀቅ ድጋፋቸውን የገለጡም አሉ። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አሕመድ አዲስ የመከላከያ ዋና መሥሪያ ቤት በሚመረቅበት ዕለት ባሰሙት ንግግር፦ ስለ እስረኞቹ መፈታት ማብራሪያ ሰጥተዋል። ጠቅላይ ሚንሥትሩ «ጉዳዮን» ሲሰሙ ራሳቸውም ጭምር መደንገጣቸውን ገልጠዋል።
መንግሥት እስረኞቹን ስለፈታበት ምክንያቶች ሲያብራራም «ዘላቂና አስተማማኝ ሰላምን» ለማስፈን እንዲሁም «ዴሞክራሲያዊ ስርዓትና፣ ጠንካራ ህብረ-ብሔራዊ አንድነት ለመገንባት» በዋናነት በማለም መሆኑን ጠቅሷል። ከእስር የተለቀቁ ፖለቲከኞች በበኩላቸው ሊደረግ ስለታሰበው «ብሔራዊ ምክክር» አቋማቸውን በእ የፓርቲያቸው በኩል በሰጧቸው መግለጫዎች አንጸባርቀዋል። የመንግሥት እስረኞቹን ለመፍታት የውሳኔ አሰጣጡ እና ሒደቱ እንዲሁም የእስረኞቹ መፈታት ኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ያለው ጠቀሜታ እንዴት ይታያል? «በርካቶችን ግራ ያጋባው የእስረኞቹ መፈታት» የዛሬው የውይይታችን ርእስ ነው።
መንግሥት በውይይቱ በመሳተፍ አቋሙን እንዲያንጸባርቅ ለጠቅላይ ሚንሥትር ሴክሬታሪያት ጽ/ቤት እንዲሁም ለመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሁለት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ዶይቸ ቬለ በኢሜል የላካቸው ግብዣዎች ምላሽ አላገኙም። ኾኖም የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚንሥትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ሐሙስ ዕለት ለዶይቸ ቬለ በተናጠል ከሰጡት ቃለ መጠይቅ ለውይይቱ ግብአት እንዲሆን በመሀል እናስደምጣለን። በዛሬው ውይይት እንዲሳተፉ ሦስት እንግዶችን ጋብዘናል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሰ