በሳኡዲ እስር ቤቶች የኢትዮጵያውያን ስቃይ
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 28 2014ሳዑዲ አረቢያ እስር ቤቶች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለረሃብ፣ እብደትና ሞት እየተዳረጉ እንደሆን የዓይን እማኞች ለዶቸ ቬለ ተናግረዋል። አቶ ኡመር ዳውድ በሳዑዲ አረቢያ ከአስር አመታት በላይ ኖረዋል። ከእስር ቤት ውጪ ያዩትንና እስር ቤት ላይ በኢትዮጵያውያን ላይ ደረሰ ያሉትን ሲያስርዱ በህክምና ውስጥ የነበረች እርጉዝ የምግብ መርፌ ነቅለው ጭምር እንዳሰርዋትና በርካታ ኢትዮጵያውያን በአንድ ክፍል እስክ 200 ድረስ ታጭቀው እንደሚገኙ ገልዋል። ወይዘሮ ሣባ ገብረ ሥላሴ በሳዑዲ አረቢያ የኢትዮጵያውያን መብት ተከራካሪ ናቸው። እስር ቤቶች ዉስጥ በኢትዮጵያውያን ላይ እየደረሰ ነው ያሉት በደል «ለሰሚ ግራ የሚያጋባ ነው» ይላሉ። በአንድ ክፍል ከ200 በላይ በቀን አንዴ ብቻ ምግብ እየተስጣችው የቆሻሻ መጣያ ፕላስቲክ ደርበው እንደሚተኙ በምሬት ተናግረዋል። ወይዘሮ ሣባ በኢትዮጵያውያኑ ላይ ደረሰ ያሉትን ስቃይ ጂዳ ላለው የኢትዮጵያ ቆንስላም ሆነ የዲያስፖራ ጽሕፈት ቤት «አቤት» ለማለት ሲሄዱም በራቸው ዝግ መሆኑን ያስረዳሉ።
ሕጋዊውም ሕገወጡም ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሙሉ እንደሚታፈስ የገለጹልን አንድ ሌላ ስማችው እንዲጠቅስ ያልፈሉጉ ነዋሪ ደግሞ አሻራ አሳይተው ሲመለሱም ድጋሚ መንገድ ላይ እንደሚያዙና እንግልት እንደሚደርስባቸው ተናግረዋል። አያይዘውም ከታሳሪዎች ታሞባቸው ሀክምና እንዲያገኝ ሲጠይቁ በእስር ቤት ጠባቂዎች እንደሚደበደቡ ገልጸዋል።
ወይዘሮ ሣባም በእስር ቤት የኢትዮጵያውያኑ አያያዝ አስከፊ እንደሆነ ያስረዳሉ። በጉዳዩ ላይ በጂዳ-ሳዑዲ አረብያ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ቆንስላና የዳያስፖራ ጽሕፈ ቤት እንዲሁም የኢትዮጵያ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለሥልጣናትን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር
ነጋሽ መሐመድ