በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ህወሓትን ከሰሱ
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 9 2017
በትግራይ የክልሉ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ አመራሮች የሚሳተፉበት የማዕድን ምዝበራ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ የትግራይ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለፁ። የትግራይ ነፃነት ፓርቲ፣ ባይቶና እና ዓረና በጋራ በሰጡት መግለጫ የህወሓት አመራሮች ማእድናት በመዝረፍ እንዲሁም አዳዲስ ታጣቂዎች በመመልመል እና በማስታጠቅ ላይ ናቸው ብለዋል።
በትግራይ ክልል በተቃዋሚነት ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፖርቲዎች መካከል የሆኑት የትግራይ ነፃነት ፖርቲ፣ የታላቅዋ ትግራይ ብሔራዊ ሸንጎ ባይቶና እና ዓረና ትግራይ ለሉአላዊነት እና ዴሞክራሲ ባለፈው ሳምንት በትግራይ አራት ዞኖች በሚገኙ በርካታ ወረዳዎች ልዑካን በማሰማራት የክልሉ ወቅታዊ ፖለቲካዊ እና አጠቃላይ ሁኔታ መዳሰሳቸው በመግለፅ ስለግኝታቸው ለመገናኛ ብዙሕን መግለጫ ሰጥተዋል።በትግራይ አራት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች «ኪዳን ለስር ነቀል ለውጥ» የተባለ ጥምረት መሰረቱ
ፖርቲዎቹ እንዳስታወቁት፣ በትግራይ በተለይም ሰሜን ምዕራብ እና ማእከላይ ዞኖች ከፍተኛ የወርቅ መአድን ምዝበራ በክልሉ ፖለቲካዊና የሰራዊት አመራሮች እየተፈፀመ ነው ያሉ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ ህወሓት አዳዲስ ታጣቂዎች በመመልመል እና ነባር ያላቸው ተዋጊዎች ለጦርነት እንዲዘጋጁ ቅስቀሳ ላይ ነው ሲሉ ከሰዋል።
«በትግራይ ክልል አዲስ መንግስት ይቋቋም» ተቃዋሚዎች
ከዚህ በተጨማሪ በክልሉ የውጭ ሀገር ዜጎች በቀጥታ የሚሳተፉበት የወርቅ ማዕድን ምዝበራ በስፋት እየቀጠለ ነው፣ ወርቅ የማውጣት ስራው አደገኛ ኬሚካሎች በመጠቀም ጭምር የሚከወን በመሆኑ በተፈጥሮ ሀብት እና ሰው ላይ አደጋ እየፈጠረ ነው ያሉት ሶስቱ ፓርቲዎች፥ በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ እየተከወነ ነው ያሉት የወርቅ ማውጣት ስራ በዘላቂነት ክልሉን አደጋ ላይ የሚጥል ሲሉ ገልፀውታል። የባይቶና ከፍተኛ አመራር አቶ ዮሴፍ በርሃ "የትግራይ ህዝብ ምንም በማይጠቅም፣ የአካባቢው ህዝብ ምንም በማያገኝበት ሁኔታ ይሁንና በኬሚካሎች በሚፈጠር መበከል ዘላቂ የጤና ችግር በሚፈጥር ሁኔታ በፀጥታ ችግር ላይ ያለችው ትግራይ በግልፅ በመሪዎች እየተዘረፈች ነው። መሪዎች ስንል ከክልል ጀምሮ ያሉ የፖለቲካ መሪዎች፣ የሠራዊት መሪዎች አካባቢው እየዘረፉት መሆኑ ያረጋገጥነው ነገር ነው" ብለዋል።
በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ስርዓት ማስከበር አልቻለም አሉ
ከዚህ በተጨማሪ የህወሓት መዋቅር በሕገወጥ ስራዎች ተሰማርትዋል ያሉት የትግራይ ነፃነት ፓርቲ ሊቀመንበር ዶክተር ደጀን መዝገበ፥ ህወሓት በትጥቅ የተደገፈ ማስፈራራት ጭምር በህዝብ በተመረጡ ሹመኞች እያካሄደ ነው ሲሉ ገልፀዋል። ዶክተር ደጀን "ችግሮች እየፈጠረ ያለው አክራሪ፣ ፀረ ሰላም የሆነው ህወሓት ነው። ይህ ሐይል ፀረ ሰላም ሆንዋል። በሄድንበት ዞኖች እና ወረዳዎች በህዝብ የተመረጡ ሹመኞች ጭምር እያስፈራራ ነው። ይህ ሐይል እየሄደበት ያለው ሁኔታ በጣም አደገኛ እና ትግራይ ከተጋሩ እጅ እንድትወጣ እያደረገ ያለ ሽፍታ ሆንዋል" ብለዋል።
ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ በክልሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመፍታት ሁሉ አካታች የሽግግር አስተዳደር እንደአዲስ እንዲቋቋም ጥሪ አቅርበዋል። በዚህ ጉዳይ ዙርያ ከክልሉ አስተዳደር እና የህወሓት ፅሕፈት ቤት ምላሽ ለማግኘት የተደረገ ጥረት አልተሳካም። በሁለት ጎራ ተከፍለው በመወዛገብ ላይ ያሉት የህወሓት አመራሮች እርስበርሳቸው ጭምር በተለያዩ ሕገወጥ ተግባራት ይወነጃጀላሉ።
ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ
ኂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ