በአማራ ክልል የቀጠለው የመከላከያ ሰራዊትና የፋኖ ታጣቂዎች ግጭት
ሐሙስ፣ የካቲት 21 2016
በአማራ ክልል በምዕራብ ጎጃም ዞን ፈረስ ቤት ተብሎ በሚጠራዉ ቦታ ልዩ ስሙ ዝቋላ ወገብ ቀበሌ አንድ ስማቸውን መግለፅ ያልፈለጉ ነዋሪ ለዶቼቬለ እንደገለፁት በአካባቢው ከሰኞ ጀምሮ በመከላከያ ሰራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ከፍተኛ ዉጊያ ነበር። በአሁኑ ጊዜ ግን ውጊያው ጋብ ብሎ አካባቢው በመከላከያ ስር መሆኑን አስረድተዋል።ነዋሪው አያይዘውም በአካባቢው በሁለቱ ተፋላሚ ሀይሎች የተካሄደውን ግጭት ተከትሎ ንፁሃን መገደላቸውንም አብራርተዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በአካባቢው በተፈጠረው ችግር መደበኛ እንቅስቃሴ ለማድረግ ነዋሪዎች መቸገራቸውን አስረድተዋል።በመሆኑም የደረሰውን ጉዳት ለሚመለከተው አካል እንዲደርስ ጠይቀዋል።
በክልሉ የአዊ ብሄረሰብ ዞን እንጅባራ ከተማ ነዋሪ የሆኑ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የከተማው ነዋሪ በበኩላቸው በከተማው ዙሪያ ውጊያ እና ተኩስ መኖሩን ትናንት ምሽት ለዶቼ ቬለ ልጸዋል።በዚህ ሳቢያ ከቤት መውጣት እና መደበኛ እንቅስቃሴ መከወን እንዳልቻሉ ገልፀዋል።
እንደ ነዋሪው ገለፃ ግጭቱ በወንድማማች መካከል የሚካሄድ በመሆኑ፤ ለውይይት ቅድሚያ ተሰጥቶ ችግሩ እንዲፈታ ጠይቀዋል።
የክልሉን ልዩ ኃይል ለመበተን እና ታጣቂዎችን ትጥቅ ለማስፈታት የተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱት የፋኖ ታጣቂዎች ከመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ጋር ግጭት ውስጥ ከገቡ ወራቶች ተቆጥረዋል። ይህንን ተከትሎ የክልሉ ነዋሪዎች ለሞት እና ለተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች እየተጋለጡ መሆናቸውን እየገለፁ ነው።
የሰብዓዊ ተሟጋች ድርጅቶችም በክልሉ የሚፈፀም የንፁሃን ግድያ እንዳሳሰባቸው ሲገልፁ መቆየታቸው ይታወሳል። በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የክልሉን የሰላም እና የፀጥታ ሀላፊ እንዲሁም የኮማንድ ፖስት አባል ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።
ፀሀይ ጫኔ
ማንተጋፍቶት ስለሺ