1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ትምህርትአፍሪቃ

የዩኒቨርሲቲዎች መልሶ መከፈት

ቅዳሜ፣ መስከረም 30 2013

በአማራ ክልል ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል በባሕር ዳር፣ በጎንድረ፣ በደብረታቦርና በደባርቅ ዩኒቨርሲቲዎች ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የተላከ ቡድን ባደረገው ግምገማ ዩኒቨርሲቲዎቹ ተማሪዎቻቸውን ለመቀበል የሚያስችል ዝግጅት አድርገዋል በማለቱ ዩኒቨርሲቲዎቹ ተማሪዎቻቸውን መቀበል እንደሚችሉ አስታወቁ።

https://p.dw.com/p/3jjrk
Äthiopien Bahir Dar University
ምስል A. Mekonnen/DW

በአማራ ክልል በኮሮና ምክንያት ተዘግተው የነበሩ ዩኒቨርሲቲዎች ሊከፈቱ መሆኑን የሳንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ የባሕር ዳርና የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርት ለማስጀመር በሚያስችላቸው ሁኔታ ላይ መገኘታቸውን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ማረጋገጡን አመልክተዋል፡፡ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል አሁን ያለው ዝግጅትና ግንዛቤ እያደገ በመምጣቱ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎቻቸውን እንዲቀበሉ አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ በሚኒስቴሩ የከፍተኛ ትምህርት የትምህርት ብቃትና ምዘና ዳይሬክተር አቶ ከበደ ይግዛው ዛሬ በተዘጋጀ የባለድርሻ አካላት ውይይት ላይ እንዳሉት በአማራ ክልል ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል በባሕር ዳር፣ በጎንድረ፣ በደብረታቦርና በደባርቅ ዩኒቨርሲቲዎች ከሚንስቴሩ የተላከ ቡድን ባደረገው ግምገማ ዩኒቨርሲቲዎቹ ተማሪዎቻቸውን ለመቀበል የሚያስችል ዝግጅት አድርገዋል፡፡ በመሆኑም ዩኒቨርሲቲዎቹ ተማሪዎቻቸውን መቀበል እንደሚችሉ አመልክተዋል፡፡ 
የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር ፍሬው ተገኝ በበኩላቸው የኮሮና ቫይረስ መከላከል በሚያስችል ሁኔታ ላይ የተዘጋጀን በመሆኑ በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ስለተረጋገጠ በቅርቡ ትምህርት ይጀመራል ብለዋል፡፡ 
የመቀበያ ቀኑ በቅርቡ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንደሚገለፅ የጠቆሙት ዶ/ር ፍሬው፣ በመጀመሪያው ዙር ተመራቂ ተማሪዎችን እንደሚቀበሉና በቀጣይ ለሌሎች ተማሪዎችም ጥሪ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡ 
የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዳዊት ብርሐኑ “ገምጋሚ ቡድኑ ትምህርት እንድንጀምር አረጋግጦልናል ሲሉ በስልክ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል“ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንት ከመጋቢት 2012 ዓ ም ጀምሮ በአገሪቱ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች መዘጋታቸው ይታወሳል፡፡
 
ዓለምነው መኮንን 
ልደት አበበ