1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኢትዮጵያ የተከሰተው ኃይለኛ ቅዝቃዜ መንስኤና ማብቂያው

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 7 2017

በአማራ ክልል ደባርቅ፣ባቲ፣ሾላ ገቢያና ደብረ ብርሃን የቀኑ ዝቅተኛ የሙቀት መጠን ከ5 ድግሪሴንቲግሬድ በታች እንደነበር፤በደብረብርሃን ደግሞ ከዜሮ በታች የሙቀት መጠን መመዝገቡን ባለሙያው አስታውሰዋል። ዘንድሮ ደአዲስ አበባን ጨምሮ በበርካታ አከባቢዎች ከአምናው ጋር ሲነጻጸር ጠንከር ያለ የማለዳ ቅዝቃዜ እንደነበርም አስረድተዋል።

https://p.dw.com/p/4oCqK
 አዲስ አበባ ፤ ቅዝቃዜው ከበረታባቸው ከተሞች አንዷ
አዲስ አበባ ፤ ቅዝቃዜው ከበረታባቸው ከተሞች አንዷምስል Seyoum Getu/DW

በኢትዮጵያ የተከሰተው ኃይለኛ ቅዝቃዜ መንስኤና ማብቂያው

አዲስ አበባን ጨምሮ በኢትዮጵያ አብዛኛው ስፍራዎች ሰሞኑን የተከሰተው ጠንከር ያለ ብርድ ከዚህ ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ እየተዳከመ እንደሚሄድ የኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡ በዚህ ወቅት ከሳይቤሪያ በመነሳት ወደ ኢትዮጵያ በሚገባው ደረቅና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ ምክንያት ጠንከር ያለው ቅዝቃዜ መከሰቱን የሚያስረዱት ባለሙያዎች የዘንድሮው ቅዝቃዜ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ጠንከር ያለ መሆኑን አረገጋግጠዋል። 

“ዘንድሮ ህዳር መጨረሻ አከባቢ ከፍተኛ ቅዝቃዜ ነው ያለው፡፡ አሁን ደግሞ ያለንበት ታህሳስ ወር በጣም የባሰበት ቅዝቃዜ እያስተዋልን ነው” በጠዋት ወጥተው ስፖርትን የሚያዘወትሩ አንድ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሰጡን አስተያየት ነው፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ በተለይ ካለፈው ህዳር ወር መጨረሻ ጀምሮ አሁን እስካለንበት ታህሳስ ወር ከተለመደውም ጠንከር ያለ ከፍተኛ ብርድ ተስተውሏል፡፡

ቅዝቃዜው ለምን በረታ?

 

የሜትዮሮጂ ባለሞያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ዓመታዊ የአየር ጠባይ ወቅቶችን ክረምት፣ በጋ እና በልግ በማለት በሶስት ይከፍሉታል፡፡ የወቅቶቹን ባህሪያት የሚወስኑትም በካባቢ አየር ውስጥ፣ በየብስ እና በውሃ አካላት ላይ የሚፈጠሩ የአየር ሁኔታ ክስተቶች እንደሆኑ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡ በኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት የትንበያና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ምርምር ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አሳምነው ተሾመ ከጥቅምት እስከ ጥር ወራት ያሉትን የሚሸፍነው አሁን የምንገኝበት በጋ ተብሎ የሚጠቀሰው ወቅት ለአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍሎች ደረቅና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ የሚስተዋልበት ነው፡፡የሰሞኑ ቅዝቃዜ እና የበረታው የክረምት ዝናብ

ጥቁር ደመና የተጫነው ወንጪ
ጥቁር ደመና የተጫነው ወንጪ ምስል Seyoum Getu/DW

“ይህ ወቅት ለአብዛኛው የአገራችን አከባቢዎች፤ ለአብነትም ለትግራይ፣ አፋር፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ አብኛው የኦሮሚያ እና ማዕከላዊና ምስራቃዊ የኢትዮጵያ አከባቢዎች በዚህ በበጋ ወቅት የበጋ ደረቃማ እና ነፋሻማ የአየር ሁኔታዎች የሚያመዝንበት ወቅት ነው” ይላሉ፡፡ በተለይም ከሳይበሪያ የሚነሳው ደረቅና ነፋሻማ የአየር ጠባይ በነዚህ አከባቢዎች ለሚስተዋለው የአየር ጠባይ ወሳኙን ሚና እንደሚጫወቱም የሚያነሱት ባለሙያው በተጠቀሱት አንዳንድ አከባቢዎች በሚከሰት ከፍተኛ ቅዝቃዜ የሙቀት መጠኑ ከአንድ ድግሪ ሴልሽየስ በታች እንደሚወርድ ገልጸዋል፡፡

የዘንድሮው ቅዝቃዜ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት መጠንከሩ

ባለፉት ጥቂት ቀናት በኢትዮጵያ ደጋማ ስፍራዎች በተለይም በአማራ ክልል ደባርቅ፣ በባቲ፣ በሾላ ገቢያ እና በደብረ ብርሃን የቀኑ ዝቅተኛ የሙቀት መጠን ከ5 ድግሪሴንቲግሬድ በታች ሆኖ መመዝገቡን እንዲሁም በደብረብርሃን ከዜሮ በታች የሙቀት መጠን የተመዘገበበት እለት መኖሩንም ያነሱት ባለሙያው ዘንድሮ አዲስ አበባን ጨምሮ በበርካታ አከባቢዎች ከባለፈው ዓመት እንኳ ሲነጻጸር ጠንከር ያለ የማለዳ ቅዝቃዜ አሁን መስተዋሉን አንስተዋል፡፡ “በተለይም አዲስ አበባን ከባለፈው በጋ 2016 ዓም ተመሳሳይ ወቅት ጋር አነጻጽረን ስንመለከተው የቀኑ ዝቅተኛ የሙቀት መጠን ከ10 ወደ 6.6 ድግሪ ሴንትግሬድ ዝቅ ብሎ ተመልክተናል” ያለጁት ዶ/ር አሳምነው፤ “በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች አከባቢዎች ላይ የማለዳው ቅዝቃዜ ማለዳ ላይ መጠናከሩን ተመልክተናል” ነው ያሉት፡፡ ይህም ከሳይበሪያ ላይ በመነሳት ወደ አገሪቱ ስገባ የነበረው ደረቅና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ በመጠናከሩ ነው ብለዋል፡፡ ይህም ቅዝቃዜ እስከ ታህሳስ ወር አጋማሽ ድረስ እንደሚቀጥልና ከታህሳስ 13 በኋላ ግን የቅዝቃዜ መጠኑ እየተዳከመ እንደሚሄድ አስረድተዋል፡፡ቀዝቃዛው የአየር ጠባይ ያበረታው ኢንፍሉዌንዛ

 

ከዚህ ቀደም ብርዱ በጥቅምት ላይ እንደሚጠነክር፤ ዘንድሮ ግን ከህዳር መጨረሻ ጀምሮ አሁን እስከ ምንገኝበበት ታህሳስ ወር የተጠናከረበትን ምክንያት የተጠየቁት ባለሙያው፤ ባለፈው ግንቦት ወር የተሰጠውን የአየር ሁኔታ ትንቢያ ማስታወስ እንደሚያስፈልግ አንስተዋል፡፡ “የክረምቱ ዝናብ አወጣጥ ሊዘገይ እንደሚችል ባለፈው ግንቦት 2016 ኣ.ም. አንስተን ነበር” ያሉት ዶ/ር አሳምነው፤ እስከ ህዳር አጋማሽ ከበርካታ አገሪቱ አከባቢዎች ያልጠፋው ዝናብና ደመና ወበቅ በመፍጠሩ የቅዝቃዜውን ወቅት ወዲህ መግፋቱን አስረድተዋል፡፡

ስዩም ጌቱ

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ