በኦሮሚያ ክልል በታጣቂዎች መመለስ ነዋሪዎች ምን አሉ?
ሐሙስ፣ ኅዳር 26 2017በኦሮሚያ ክልል በታጣቂዎች መመለስ ነዋሪዎች ምን አሉ?
በኦሮሚያ ክልል ማዕከላዊ ዞኖች መንግስትን ሲገዳደሩ የቆዩት የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነግ-ኦነሰ) ታጣቂዎች በስፋት እየገቡ መሆኑን መንግስት አስታወቋል፡፡ የምዕራብ ሸዋ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች ነዋሪዎችና የአገር ሽማግሌዎችም ይህንኑን ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል፡፤ በሌሎች አካባቢዎች የቀሩ ታጣቂዎች ጉዳይ ግን ግን አሁንም ያሳስበናል ይላሉ ።
መንግስት እንዳስታወቀው ታጣቂዎቹ በስፋት መግባታቸውን የቀጠሉት ባለፈው እሁድ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት እና የኦነግ-ኦነሰ ማዕከላቂ ዞን አዛዥ የሰላም ስምምነት ማኖራቸውን ተከትሎ ነው፡፡
የኦነግ-ኦነሰ ከፍተኛ አዛዥ ስምምነቱን ማጣጣላቸውን ተከትሎ ግን ነዋሪዎች አሁንም የስምምነቱን ሰላም የማምጣት ዘላቂነት በስጋት ነው ሚመለከቱት፡፡
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ጮቢ ወረዳ ላለፉት አምስት ዓመታት ግድም እራሳቸውን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊ ያሉና መንግስት ሸነ ሲል ስጠራ የቆየው የታጠቁ አካላት በስፋት ከሚንቀሳቀስባቸው አከባቢዎች ተጠቃሽ ነው፡፡ በዚህ ስፍራ በተፈጠረው ጥልቅ የጸጥታ ችግር የተለያዩ የልማትና ማህበራዊ አገልግሎቶችም እስከመስተጓጎል ደርሷል፡፡
የኦሮሚያ ክልል መስተዳድር እና የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አመራር ጋር የተደረሰ ስምምነት
ግንደበረት እና ጀልዱን የመሳሰሉ የምዕራብ ሸዋ ዞን ወረዳዎችን በሚያዋስነውና ከአምቦ ከተማ 80 ኪ.ሜ. ግድም ርቀት ላይ በሚገኝ በዚህ ወረዳ ከአባይ በረሃ እስከ የሆሮ ጉዱሩ ወለጋው ፍንጫን የሚያዋስነው የኛማር በረሃም መገኛው በዚህ ነውና ባለፉት ጢቂት ዓመታት ለታጣቂዎች አንዱ ምሽግ ሆኖ ቆይቷል፡፡
የታጣቂዎቹ አመላለስ
ባለፈው እሁድ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት የቀድሞ የማዕከላዊ ዞን ዋና አዛዥ ጦሩን ወክለው ከመንግስት ጋር የሰላም ስምምነት ስለማድረጋቸው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በይፋ ማሳወቁን ተከትሎ ባለፉት ሶስት ቀናት ታጣቂዎች በረሃን ለቀው በብዛት የተዘገጃጀላቸው ወደ ተባለ ካምፕ ስተሙ ታይተዋል፡፡
ለደህንነታቸው ስባል ለጊዜው ስማቸው ያልተጠቀሰ ነገር ግን ታጣቂዎቹ ስመለሱ ከሚቀበሉዋቸው አንዱ የሆኑት የጮቢ ወረዳ የሀገር ሽማግሌም ይህንኑን በማረጋገጥ ባለፉት ሁለት ቀናት ከዚሁ እሳቸው ከሚገኙበት ከጮቢ ወረዳ ብቻ ወደ አንድ ሺህ ግድም ታጣቂዎች ስመለሱ መታዘባቸውን ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል፡፡ “እኛ አከባቢ መጀመሪያ በጣም የተጎዳና በረሃማ አከባቢ ነው፡፡ እኔ በአከባቢው የአገር ሽማግሌ ነኝ፡፡ ባሁን ወቅት በታጠቀው አካልና መንግስት መካከል በተፈጠረው መግባባት ነገሮች እየተሸሻሉ ስንመለከት ደስታ ተሰምቶናል፡፡ ማክሰኞና እረቡዕ ብቻ 520 ታጣቂች እና 470 የታጣቂዎቹ ካድረ አንድ ላይ 990 ስገቡ ተመልክተናል” ብለዋል፡፡
ስለመንግስት እና የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት የሰላም ስምምነት የህዝብ አስተያየት
ህብረተሰቡን ዋጋ ያስከፈሉት የባለፈው ግጭት
እንደ የአከባቢ ነዋሪው የአገር ሽማግሌ አስተያየት በታጠቂ ቡድኑና በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች መካከል በተፈጠረው የለየለት ቀውስ ያለፉት ጢቂት የመከራ ኣመታት ለማስታወስም የሚመች አይደለም ሲሉ የሳለፉት ሰቆቃ ከባድ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ “ይቅርታ እድርግልኝና የወረዳው ህዝብ በስነልቦናም በጣም የተጎዳ ነው፡፡ ባለፉት ኣመታ በመንግስትም ሆነ በአማጺያን ታጣቂዎች በሁለቱም በኩል የተመታ ህዝብ ሲሆን ወረዳውም እንደ ዞን በረሃማ ስለሆነ በጣም የተጎዳ ወረዳ ነው” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ሌላው በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ያከሉት የጀልዱ ወረዳ ነዋሪ ታጣቂቹ በስፋት ስመለሱ መመልከታቸውን አስረድተዋል፡፡ “ሰው ወደ ከተማ ወጥተው ስመለከቷቸው ነበር፡፡ ታጣቂዎቹ በየቀበሌያት ተሰብስበው ይጠብቃሉ ከዚያን መንግስት በመኪና እየሄደ ይቀበላቸዋል፡፡ አሁን እንደ ጀልዱ ወረዳ ከብዙ ቀበሌዎች እየገቡ ነው” ሲሉ የተመለከቱትን አጋርተውናል፡፡
የመንግስት የሰላም ስምምነትና የገጠመው ቅሬታ
መንግስት “የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በሁሉም አቅጣጫ መግባታቸውን ቀጥለዋል” እያለ ነው፡፡ የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ በየቀኑ በማህበራዊ ገጹ በኩል እያጋራ ባለው መግለጫ በርካታ የታጣቂ ቡድኑ አባላት እየገቡ መሆኑን አጋርቷል፡፡ እስካሁን ምን ያህል ታጣቂዎች ገብተው ይሆን የሚለውና ተያያዝ ጉዳዮች ላይ ለክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ጥያቄውን የማቅረብ ጥረት ብናደርግም እስካሁን አልሰመረልንም፡፡
የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት ግን መንግስት ባለፈው እሁድ ከታጣቂ ቡድኑ አመራሮች ጋር የሰላም ስምምነት ማኖሩን በይፋ ከገለጸ በኋላ ከምዕራብ ሸዋ እና ደቡብ ምዕራብ ሸዋ የተለያዩ ወረዳዎች ታጣቂዎቹ በስፋት እየተመለሱ ነው፡፡
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝደንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ የሰሞኑ ንግግርና አስተያየት
የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነግ-ኦነሰ) የባለፈውን እሁድ ስምምነት ተከትሎ ባወጣው ይፋዊ መግለጫ “ኦነግ-ኦነሰ ከመንግስት ጋር ያደረገው ስምምነት የለም” በማለት ጉዳዩን ወዲያው ነበር ያስተባበለው፡፡ በእለቱ አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡ የታጣቂ ቡድኑ ዋና አዘዥ አማካሪ ጅሬኛ ጉደታ “ስምምነቱ መንግስት የሚሰራው ድራማ ነው” በማለት መንግስት አደረኩ ያለውን የሰላም ስምምነት አጣጥለው ነቅፈውት ነበር፡፡ በዚህ መንገድ ሰላም መምጣት እንደማይችልና ስምምነቱን ከመንግስት ጋር የፈረሙ የታጣቂ ቡድኑ የቀድሞ ማዕከላዊ ኦሮሚያ ዋና አዛዥ ከጦሩ ከተሰናበቱ መቆየቱን ተነግረዋልም፡፡
እሁድ የአገሪቱ መከላከያ ሰራዊት ኢታማዦር በተገኙበት ስምምነቱን ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ጋር ያኖሩት የቀድሞ የኦነግ-ኦነሰ ማዕከላዊ ዞን አዛዥ ሰኚ ነጋሳ ግን “በህዝቡ ላይ የሚደርስ ሰቆቃ እንዲያበቃ እንጂ ወደ ስምምነቱ የመጣነው እጅ በመስጠት አይደለም” ሲሉ በእሁድ ህዳር 22 ቀን 2017 ዓ.ም. ስምምነት ወቅት ተናግረዋል፡፡
ታጣቂዎች በስፋት እየተመለሱ ነው በተባለበት ምዕራብ ሸዋ ዞን ነዋሪዎቹ ያሰለቻቸው ግጭት ይቆም ይሆን ብለው በተስፋና ደስታ ቢመለከቱትም አሁንም ግን ስጋት እንዳላቸው አልሸሸጉም፡፡ “ስጋት አለ፡፡ አሁን ገቡ የሚባለው ታጣቂዎች ከምዕራብ ሸዋ እና ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ነው፡፡ ሌላ ከወለጋ እና ሰሜን ሸዋ አከባቢ የሚመጣ ተንቀሳቃሽ ቡድን አለና ያው እነሱ ተደራጅተው ከህብረተሰቡ ጋር ተወያይተው የሆነ መፍትሄ ካልመጣ የነበረው ሰቆቃ ሊቀጥል የሚችልበት እድል እንዳለ ስጋት አለን” ነው ያሉት፡፡
ሥዩም ጌቱ
ታምራት ዲንሳ
አዜብ ታደሰ