በደቡብ ኢትዮጵያ ምክር ቤት ጉባኤ ውይይት የተደረገበት የመምህራን ደሞዝ አለመከፈል
ሐሙስ፣ መጋቢት 5 2016የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዙር 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ጉባዔውን እያካሄደ ይገኛል ፡፡ ከትናንት ጀምሮ በአርባምንጭ ከተማ እየተካሄደ የሚገኘው ጉባዔ በበርካታ ክልላዊ ጉዳዮች ላይ መክሯል ፤ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ የቀረበለትን የሥራ አፈጻጸም ሪፖርትም አዳምጧል ፡፡ የርዕሰ መስተዳድሩን ሪፖርት ተከትሎ የምክር ቤቱ አባላት በእርሻ ግበዓት አቅርቦት ፣ በትምህርት ፣ በጤና እና በመሠረተ ልማት ግንባታዎች ዙሪያ አሉን ያሏቸውን ጥያቄዎች አንስተዋል ፡፡የሃድያ ዞን መምህራን እና ሐኪሞች የደሞዝ ጥያቄ ከምን ደረሰ?
የትምህርት ቤቶች መዘጋት
በአርባምንጩ የክልሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጉባዔ ላይ ከአባላቱ ከተነሱት ጥያቄዎች መካከል የመምህራን ደሞዝ አንዱ ነው ፡፡ በተለይም አንድ የምክር ቤቱ አባል በመምህራን ደሞዝ አለመከፈል የተነሳ እየተዘጉ ይገኛሉ ያሏቸው ትምህርት ቤቶች ጉዳይ እንዳሳሰባቸው ለጉባዔተኛው ተናግረዋል፡፡ አሁን ላይ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ትምህር ቤቶች ተዝግተዋል ያሉት የምክር ቤት አባሉ “ የመዘጋታቸው ምክንያትም ከመምህራን የደሞዝ ክፍያ ጋር የተያያዘ ነው ፡፡ በተለይ ዘንድሮ የ12 ክፍል ብሄራዊ መልቀቂያ የሚወስዱ ተማሪዎች እየተማሩ አይደለም ፡፡ መምህራኑ ክፍል መግባት አቁመዋል ፡፡ ክልሉ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ የትምህርት ስብራትን ለመጠገን የተነደፉ ፖሊሲዎችን እንዴት መተግበር ይችላል “ ሲሉ ጠይቀዋል ፡፡
ገቢ ስብሰባ የመፍትሄ አማራጭ
ከመምህራን የደሞዝ አለመከፈል ችግር ጋር በተያያዘ ከጉባኤው አባላት በተነሳው ጥያቄ ላይ የክልሉ አስፈጻሚ አካላት የየበኩላቸውን ምላሽ ሰጥተዋል ፡፡ ጥያቄው መሠረታዊ መሆኑን የጠቀሱት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አባባሁ ታደሰ “ ጉዳዩ ትኩረት የሚሻ ነው “ ብለዋል ፡፡
ደሞዛቸዉን በፈረቃ የሚቀበሎት ዜጎች አቤቱታየክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ በበኩላቸው በክልሉ የመምህራንን ደሞዝን ጨምሮ ሌሎች የፋይናንስ ውጪዎችን ለማሟላት ያልተቻለው በገቢ አሰባሰብ ረገድ በሚፈለገው መጠን ባለመሠራቱ መሆኑን ተናግረዋል ፡፡ በቀጣይ የፋይናንስና የገቢ ሰብሳቢ ተቋማትን አቅም በማጠናከር የደሞዝ ክፍያን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ጥረት እንደሚደረግ ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቅሰዋል ፡፡
ጥቅማ ጥቅሞቹ
በምክር ቤቱ ጉባዔ ላይ በቀረበው የመምህራን ደሞዝ አለመከፈል ዙሪያ አስተያየታቸውን በዶቼ ቬለ ከተጠየቁትና ሥማችን አይጠቀስ ካሉ መምህራን መካከል አንዱ ምክር ቤቱ ጉዳዩን አንስቶ መወያየቱን በበጎ እንደሚመለከቱት ገልጸዋል፡፡ አሁን ላይ ደሞዝ ቢከፈል እንኳን የኑሮ ውድነቱ ሊቋቋሙት እንደማይችሉ የጠቀሱት አስተያየት ሰጪው “ ክልሉ ሠፊ የተፈጥሮ ሀብትና አቅም ያለው ነው ፡፡ ገቢ የመሰብሰብ ንቅናቄን መፍጠር አለበት ፡፡ በዘርፉ የሚታየውን የግብር ስወራንም በጥብቅ መከታተል ይኖርበታል “ ብለዋል ፡፡የሃድያ ዞን መምህራን እና ሐኪሞች የደሞዝ ጥያቄ ከምን ደረሰ?
አሁን ላይ የመምህራንን ደሞዝ በወቅቱ ከመክፈል ባለፈ ሌሎች ተጨማሪ ጥቅሞችን ሊያገኙ የሚችሉባቸው ሁኔታዎች መመቻቸት እንደሚኖርበት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አባባሁ ታደሰ በጉባዔው ላይ ጠቅሰዋል ፡፡ በቀጣይ በመምህራን ጥቅማጥቅሞች ውስጥ ከሚካተቱት መካከል በማህበር ተደራጅተው የመኖሪያ ቤት የሚገነቡበትና ምግባ በሚካሄድባቸው ትምህርት ቤቶች እነሱም የምግብ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚሉት የሚጠቀሱ መሆናቸው የቢሮ ኃላፊ አስረድተዋል ፡፡
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ኂሩት መለሰ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር