1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የብሔራዊ የደህንነት ምክር ቤት ውሳኔዎች ከፍ ያለ ቦታ አግኝተዋል

ዓርብ፣ ኅዳር 1 2010

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ትላንት ጥቅምት 30 በወቅታዊ የፖለቲካ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ሶማሌ እና ኦሮሚያ ክልል ያሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የብሔራዊ የደህንነት ምክር ቤት ያሳለፈውን ውሳኔ በመግለጫቸው ጠቅሰዋል፡፡ በግጭት የተሳተፉ በቁጥጥር ስር ይውላሉ ብለዋል፡፡

https://p.dw.com/p/2nQoA
Äthiopien PK Ministerpräsident Hailemariam Desalegn
ምስል EBC

የብሔራዊ የደህንነት ምክር ቤት ውሳኔዎች ከፍ ያለ ቦታ አግኝተዋል

በኢትዮጵያ ያለውን የፖለቲካ አለመረጋጋት እና በገዢው ፓርቲ ባለስልጣናት መካከል  አለ የሚባለውን ሽኩቻ ተከትሎ በብዙሃኑ ዘንድ ከሚነሱ ጥያቄዎች መካከል “ውሳኔ ሰጪው ማነዉ ነው?” የሚለው ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በትላንትናው ጋዜጣዊ መግለጫቸው ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የመሰለ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ እምብዛም በአደባባይ ስሙ የማይነሳውን እና በሀገሪቱ የጸጥታ ጉዳዮች የመወሰን ከፍተኛ ስልጣን ያለውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤትን ፊት ለፊት አምጥተውታል፡፡

በምክር ቤቱ በማቋቋሚያ አዋጅ እንደተጠቀሰው “ለሀገሪቱ ብሔራዊ የደህንነት የሥጋት ምንጭ የሆኑ ሁኔታዎችን በመገምገም ሊወሰዱ ስለሚገባቸው እርምጃዎች ሃሳብ የማቅረብ” ስልጣን አለው፡፡ የብሔራዊ የደህንነት ምክር ቤቱ በቅርቡ ባደረገው ስብስባ በኢትዮጵያ ሶማሌ እና የኦሮሚያ ክልሎች መካከል ያለውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ውሳኔዎች ማሳለፉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ በአካባቢው በዘላቂነት ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር ምክር ቤቱ ካስተላለፋቸው ውሳኔዎች መካከል “በግጭቱ የተሳተፉ አካላት” ላይ የሚወሰድ እርምጃ አንዱ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

“በሂደቱ የተሳተፉ ህገ ወጥ ተግባር ላይ የተሰማሩ አካላት በተለይም ደግሞ ቀጥተኛ ተሳትፎ ያደረጉ አካላት በህግ ቁጥጥር ስር አብዛኞቹ እንዲገቡ ተደርገዋል፡፡ የተቀሩትም ቢሆኑ በቀጣይ በምንሰራቸው ስራዎች በቁጥጥር ስር የሚውሉ ይሆናሉ፡፡ ወደ ህግም ቀርበው ተጠያቂ ይሆናሉ” ብለዋል አቶ ኃይለማርያም፡፡

Äthiopien Ministerpräsident Hailemariam Desalegn
ምስል Getty Images

በኢትዮ ሶማሌ እና በኦሮሚያ ክልሎች መካከል ያለውን ችግር ስረ-ነገር እንዲያጠና ለመንግስታዊው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኃላፊነት መሰጠቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመልክተዋል፡፡ ኮሚሽኑ በአመራር ደረጃ ላይ ያሉትን ጨምሮ በሰብዓዊ መብትም ሆነ በተለያዩ ጥሰቶች የተሳተፉ አካላት አጣርቶ እንዲያቀርብ መወሰኑን ገልጸዋል፡፡ የማጣራት ስራውን እያከናወነ የሚገኘው የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በሚያመጣው ውጤት ላይ ተመስርቶ መንግስታቸው ቀጣይ እርምጃ እንደሚወስድ ጠቁመዋል፡፡ ከኮሚሽኑ በተጨማሪ ሌሎች በምርመራ ላይ የሚሳተፉ የፌደራል መንግስት አካላት በሚያቀርቡት መረጃ ላይ ተመርኩዞም በህግ የሚጠየቁ አካላት ላይ እርምጃ መውሰድ እንደሚቀጥልም አስረድተዋል፡፡ 

ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት እቅዶች ማውጣቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡ ሰባት ቋሚ አባላት ያሉት ምክር ቤቱ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰብሳቢነት እንደሚመራ ማቋቋሚያ አዋጁ ይደነግጋል፡፡ የሀገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የምክትል ሰብሳቢነት ድርሻ አላቸው፡፡ የመከላከያ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን ጨምሮ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም እና የደህንነት ኃላፊው የምክር ቤቱ አባል ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ስለምክር ቤቱ እቅድ ተከታዩን ብለዋል፡፡ 

“የኢትዮጵያ ብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት በቅርቡ ባደረገው ስብሰባ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል እቅድ አውጥቷል፡፡  በዚህም እቅድ መሰረት ይህ ችግር እንዲፈታ ዋነኛው ተዋናይ የሆነውን ህዝባችንን በሙሉ አቅሙ እንዲሳተፍ የማድረግ ነው፡፡ እስካሁንም ድረስ ችግሩን ለመፍታት ዋነኛውን ሚና የተጫወተው ሰላም ወዳዱ ህዝባችን ነው፡፡ ስለዚህ ሰላም ወዳዱ ህዝባችን እንደተለመደውም ችግሩን ለመፍታት ተጨማሪ ትጋት፤ ተጨማሪ እንቅስቃሴ ማድረግ እንዳለበት አምነናል፡፡ ስለዚህ በተከታታይ በተለያየ አካባቢ የምናደርጋቸው የህዝብ ውይይቶች እና ኮንፈረንሶች ህዝቡ በንቃት እንዲሳተፍ ማድረግ የሚገባን ይሆናል” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው፡፡

የፖለቲካ አመራሩ “ከላይ እስከ ታች በዚህ ግጭት ውስጥ የተሳተፉ አካላትን ለመቆጣጠር ፖለቲካዊ መፍትሄዎችን መስጠት እንዳለበት” አቶ ኃይለማርያም ተናግረዋል፡፡ ከህዝብ ጋር እንደሚደረጉ ውይይቶች ሁሉ ተመሳሳዩም በአመራሮች ደረጃ እየተካሄደ እንዳለ አስረድተዋል፡፡ 

ተስፋለም ወልደየስ 

ነጋሽ መሐመድ