1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጦርነት የተጎዱት የትግራይ ክልል የጤና ተቋማት

ሐሙስ፣ መጋቢት 19 2016

በትግራይ ክልል በጦርነቱ የወደሙ የጤና ተቋማትን መልሶ ወደ ሥራ ለማስገባት እና አዳዲስ የጤና ፕሮጀክቶች ለመጀመር እየሠራ መሆኑ ጤና ሚኒስቴር ገልጿል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በክልሉ በተለይም በከተሞች ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች፣ በወጣቶች ደግሞ ሱስ አሳሳቢ እንደሆነ የትግራይ ጤና ቢሮ ይገልፃል።

https://p.dw.com/p/4eEHb
ፎቶ ከማኅደር፤ ዓይደር ሆስፒታል
በትግራይ ክልል ትልቁ ሀኪም ቤት መሆኑ ከሚገለጸው ዓይደር ሆስፒታል ብቻ ከአንድ መቶ በላይ ሐኪሞች መልቀቃቸው ሲገለፅ ቆይቷል። ፎቶ ከማኅደር፤ ዓይደር ሆስፒታልምስል Million Hailessilasie/DW

በጦርነት የተጎዱት የትግራይ ክልል የጤና ተቋማት

 

ጦርነቱ በትግራይ ክልል በሚገኝ የጤና መሠረተ ልማት እና አጠቃላይ የጤና ስርዓት ላይ ከፍተኛ ውድመት ማስከተሉን የዓለም አቀፉ ተቋማት እና የትግራይ ጤና ቢሮ መረጃዎች ያመለክታሉ። በጦርነቱ ወቅት በተለያየ ደረጃ የሚገለፅ ውድመት የደረሰባቸው 80 በመቶ የሚሆን የትግራይ ክልል የጤና ተቋማት መልሶ ወደ ሥራ ለማስገባት ባለፉት ጊዜያት ጥረት ሲደረግ ነበር። አሁን አብዛኞቹ በክልሉ የሚገኙ ሆስፒታሎች እና ጤና ጣብያዎች የግብአት እጥረት ቢኖርም ወደ ሥራ ተመልሰዋል። በመቐለ ከሚገኙ የጤና ተቋማት መካከል የሆነው መንግሥታዊው የካሰች ጤና ጣብያ ሥራ አስከያጅ የሆኑ ሲስተር አልማዝ ለዶቼ ቬለ እንደገለፁት፥ በመድሃኒት፣ ክትባት እና ሌሎች የሕክምና ግብአቶች እጦት አብዛኛውን አገልግሎቱን አቋርጦ የነበረው ተቋማቸው አሁን ወደ መደበኛ ሥራው ተመልስዋል።  ሲስተር አልማዝ «ከነበረበት የተሻለ ነው። በአቅርቦት ረገድ ክትባቶች ጨምሮ መድሃኒቶች በተወሰነ መጠንም ቢሆን ይቀርባል። የላብራቶሪ ግብአቶች ግን አሁንም የሉም። ካሳለፍነው መጥፎ ጊዜ አንፃር ስታየው ግን አሁን የተሻለ ነው» ይላሉ።

ሌላበትግራይአሳሳቢ የሆነው የጤና ችግር በተለይም በከተሞች የወጣቶች በሱስ መጠመድ እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መሆናቸውን ነው የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ የሚገልጸው። የክልሉ ጤና ቢሮ ሐላፊ ዶክተር አማኑኤል ሃይለ «በተለይም በከተሞች በወጣቶች አካባቢ የሚታይ ሰፊ የሱሶች መንሰራፋት አለ። ይህ ተጨማሪ ፈተና ነው። ከዚህ በተጨማሪ ተላላፊ በሽታዎች አሉ፣ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችም ይታያሉ፣ ከአደጋዎች ጋር የተያያዙ ችግሮች አሉ። ስለዚህ ከተሞቻችን ከገጠር በተለየ በእነዚህ ጫናዎች እየተጠቁ ነው» ብለዋል።

ይህን በመላው ሀገሪቱ የሚታይ አደጋ ለመከላከል ያለመ ከተማ ተኮር የጤና ፕሮጀክት የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር በትግራይ ክልል አስጀምሯል። በዚህ የጤና ስርዓት ማጠናከርያ ሥራ በተለይም በትግራይ ክልል በግጭቱ ምክንያት ከቀያቸው ተፈናቅለው በመጠለያዎች ያሉ እና ሌሎች በከተሞች ለጤና አስጊ በሆነ ሁኔታ ለሚኖሩ መፍትሔ ለመስጠት ያለመ ነው ተብሏል።

 በትግራይ ክልል በአብዛኛው አካባቢዎች ጤና ተቋማት ወደ መደበኛ ሥራቸው ቢመለሱም የባለሙያዎች ፍልሰት ግን አሳሳቢ መሆኑ ይገለፃል። በክልሉ ትልቁ ሀኪም ቤት መሆኑ ከሚገለጸው  ዓይደር ሆስፒታል ብቻ ከአንድ መቶ በላይ ሐኪሞች መልቀቃቸው ሲገለፅ ቆይቷል።

ሚሊየን ኃይለ ሥላሴ

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ