1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

"ሂር ሂሴ" በዩኔስኮ የማይዳሰስ ቅርስነት እንዲመዘገብ የሚደረገው ጥረት

ሐሙስ፣ መጋቢት 7 2015

የሶማሌ ሂሳ ብሄረሰብ ህጉን መሰረት በማድረግ የብሄረሰቡ ባህላዊ ፣ መንፈሳዊ እና ፖለቲካዊ መሪ አድርጎ የመረጣቸው ዑጋዝ ሙስጠፋ መሀመድን ጨምሮ ከጅቡቲ እና ከሶማሌላንድ የመጡ ተወካዮች እና ባለስልጣናት በውይይቱ ተገኝተዋል። የብሄረሰቡ መገኛ የሆኑት ኢትዮጵያ ፣ ጅቡቲ እና ሶማሌላንድ በጋራ ጥያቄውን ያቀርባሉ ተብሏል።

https://p.dw.com/p/4Omhi
Äthiopien Addis Abeba | Diskussion zu Kulturgesetz "Xeer Ise"
ምስል Mesay Tekelu/DW

"ሂር ሂሴ" በዩኔስኮ የማይዳሰስ ቅርስነት እንዲመዘገብ የሚደረገው ጥረት

በሶማሌ ህዝብ ለሂሳ ብሄረሰብ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ የማንነት እና መገለጫ የሆነውን ባህላዊ ሕግ  "ሂር ሂሴ" በዩኔስኮ የሰው ልጆች ወካይ የማይዳሰስ ቅርስነት እንዲመዘገብ ለማስቻል በእሴቱ ላይ ያተኮረ ሰነድ ማዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ገልፃል።የማህበረሰቡ እሴት በተቋሙ የማይዳሰስ  ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ የብሄረሰቡ መገኛ የሆኑት ኢትዮጵያ ፣ ጅቡቲ እና ሶማሌላንድ በጋራ ጥያቄውን ያቀርባሉ ተብሏል።መሳይ ተክሉ ከድሬዳዋ ተጨማሪ ዘገባ አለው።
የብሄረሰቡ ባህላዊ ፣ መንፈሳዊና ፖለቲካዊ መሪ በማህበረሰቡ አጠራር "ዑጋዝ" ምርጫ ስርዓትን ጨምሮ ፍትህ እና ሌሎች በርካታ ኩነቶች የሚመሩበትን የማህበረሰቡ "ያልተፃፈ ህግ" በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ለተዘጋጀው ሰነድ መነሻ ምክንያቶችን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ገልፀዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ የዚህ ባህላዊ ሕግ በዩኔስኮ መመዝገብ የሚያስገኘውን ፋይዳም አስረድተዋል። በባለስልጣኑ ተዘጋጅቶ በድሬደዋ ውይይት የተካሄደበት ሰነድ ከውይይቱ የሚነሱ ሀሳቦችን አካቶ በያዝነው ወር ማጠቃለያ ጥያቄው ብሄረሰቡ የሚኖርባቸው ኢትዮጵያ ፣ ጅቡቲ እና ሶማሌላንድ በጋራ ለድርጅቱ ይቀርባል ተብሎ መታቀዱን ኃላፊው ጠቁመዋል።
የብሄረሰቡ ተወላጅ የሆኑት አምባሳደር መሀሙድ ድሪር በመድረኩ ህጉ በብሄረሰቡ ትልቅ ቦታ እና ተቀባይነት ያለው መሆኑን አንስተዋል።አቶ መሀመድ ሙሴ ጌሪ ለዶይቼ ቬሌ በሰጡት አስተያየት በባለስልጣኑ እየተደረገ ያለውን ጥረት አድንቀው ዛሬም ድረስ በስራ ላይ ባለው ሕግ ኩራት ይሰማኛል ብለዋል። 
የሶማሌ ሂሳ ብሄረሰብ ህጉን መሰረት በማድረግ የብሄረሰቡ ባህላዊ ፣ መንፈሳዊ እና ፖለቲካዊ መሪ አድርጎ የመረጣቸው ዑጋዝ ሙስጠፋ መሀመድን ጨምሮ ከጅቡቲ እና ከሶማሌላንድ የመጡ ተወካዮች እና ባለስልጣናት በውይይቱ ተገኝተዋል።
ሄር ሂሴን ጨምሮ ሌሎች በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ የማይዳሰሱ ሀብቶች ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲኖራቸው እየሰራሁ ነው ያለው የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን እስካሁን በሀገሪቱ የመስቀል በዓል አከባበር ፣ ጥምቀት ክብረ በዓል ፣ ፊቼ ጨምበላላ እና የገዳ ባህላዊ አስተዳደር ስርዓትን በዓለም አቀፉ ተቋም የማይደሳስ ቅርስ ሆነው እንዲመዘገቡ ማስቻሉን የተቋሙ መረጃ ይጠቁማል።
መሳይ ተክሉ
ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ
 

Äthiopien Addis Abeba | Diskussion zu Kulturgesetz "Xeer Ise"
ምስል Mesay Tekelu/DW