1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካየመካከለኛው ምሥራቅ

ተቃውሞ የጠነከረበት የእስራኤል ወደ ራፋ የመዝመት ዕቅድ

ሰኞ፣ የካቲት 4 2016

እስራኤል በሐማስ ላይ የምታካሒደውን ወታደራዊ ዘመቻ ወደ ራፋ ለማስፋት አቅዳለች። ዕቅዱ አሜሪካ፣ ጀርመን፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ የአውሮፓ ኅብረት እና የተመ በሥጋት የሚመለከቱት ነው። በሐማስ እና በእስራኤል መካከል የተኩስ አቁም እንዲደረስ ግፊት ለማድረግ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ያቀኑት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ያለ ውጤት ተመልሰዋል።

https://p.dw.com/p/4cKJX
የጋዛ ጦርነት ራፋ
እስራኤል ወታደሮቿን በደቡባዊ ጋዛ ወደምትገኘው ራፋ በቀጥታ ከማሰማራቷ በፊት ኃይለኛ ድብደባ በመፈጸም ላይ ትገኛለች። ምስል SAID KHATIB/AFP

ተቃውሞ የጠነከረበት የእስራኤል ወደ ራፋ የመዝመት ዕቅድ

የሀማስ ታጣቂዎች የእስራኤልን ደንብር ጥሰው መስከረም 26 ቀን 2016 በሰላማዊ የእስራኤል ዜጎች እና  በሙዚቃ ዝግጅት ታድመው በነበሩ ወጣቶች ላይ ጭምር የፈጸሙትን ግድያ ያላወገዘና ያልኮነነ ነበር ማለት ያስቸግራል። ሁሉም ጥቃቱን በማውገዝ ለእስራኤል እና በተለይም ለጥቃቱ ሰለባዎች ድጋፉን እና አጋርነቱን በልዩ ልዩ መንገድ ሲገልጽ ተስተውሏል።

የእስራኤል መንግስት ጥቃቱን ፈጽሟል ባለው ሀማስ ላይ የአጸፋ እርምጃ እንደሚወስድ በመግለጽ ዘመቻ ሲያውጅም፤ ሁኔታውን በጥንቃቄ ከመመልከት በስተቀር የተቃወመ ብዙም አልነበረም።  ይሁን እንጂ የእስራኤል ጦር በጋዛ የከፍተውና እስካሁንም የቀጠለው ዘመቻ ያደረሰው ውድመትና ያጠፋው ነፍስ ብዛት አስደንጋጭ ሆኗል።

ማሕደረ ዜና፣ የጋዛ እልቂት፣ የምዕራባዉያን ድምፀት መለወጥ

ከተባበሩት መንግስታት የወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአራት ወራት ውስጥ ብዙዎቹ ህጻናት እና ሴቶች የሆኑ 28 ሺ ሰዎች ተገድለዋል። ብዙ ሺዎች  ደግሞ በህንጻና ቤቶች ፍርስራሾች ተቀበረው ቀርተዋል። 2.2 ከሚሆነው የጋዛ ህዝብ 85 ከመቶው ወይም 1.9 ሚዮን የሚሆኑት በግዳጅ ተፈናቅለዋል። በጋዛ ከሚገኙ ህንጻዎች እና ቤቶች 80 ከመቶ የሚሆኑት በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ፈርሰዋል።

ሰላማዊ ሰዎች የጦርነት ኢላማ እንዳይሆኑ የቀረበ ጥሪ 

ይህ የእስራኤል እርምጃ እንደተባለው የሽብር ጥቃት ፈጽመዋል የተባሉትን ብቻ ኢላማ ያድረገ ሳይሆን በአንዳንዶች ይልቁንም በሰላማዊ ፍልስጤሞች ላይ ያነጣጠረ የጅምላ ጥቃት ተደርጎ ተወስዷል። ብዙዎች መንግስታትና ሰብዓዊ ድርጅቶች እስራኤል በምታካሂደው ዘመቻ መሰረታዊ የጦርነት ህጎችን እንድታከብርና ሰላማዊ ሰዎችን ኢላማ ከማድርግ እንድትቆጠብ አሳስበዋል። የመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ጦርነቱ እንዲቆም እና የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ ከ193 አባላቱ በ153ቱ የተደገፈ ውሳኔ አስተላለፏል። ደቡብ አፍሪካ የእስራኤልን ድርጊት ከማውገዝ አልፋ እስራኤልን ዘሄግ በሚገኘው የአለም ፍርድ  ቤት ላይ በዘር ማጥፋት ወንጀል ከሳ ሞግታለች።

የጋዛ ጦርነት ተፈናቃይ በራፋ
እስራኤል በራፋ በምትፈጽመው ድብደባ በርካቶች ከቤታቸው ተፈናቅለዋል።ምስል AFP via Getty Images

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉቴረሽን ጨምሮ ሌሎችም የሀማስ ቡድን ላደረሰውና ለሚያደርሰው ጥቃት የፍልስጤም ህዝብ በጅምላ የበቀል በትር ሊያርፍበት አይገባም በማለት የሰጡትን ማሳሰቢያ አሜሪካዊው የምክር ቤት አባል ሴናተር በርኒ ሳንደርስም በቅርቡ ባደረጉት ንግግር ደግመውታል። “እስራኤል ከሀማስ የሽብር ጥቃት እራሷን የመካላከል መብት ቢኖራትም በጠቅላላው የጋዝ ህዝብ ላይ ጦርነት እንድታወጅና ጥቃት እንድትፈጽም ግን ሊፈቀድላት አይገባትም” በማለት ባለፉት አራት ወራት ከ27 ሺ በላይ ሰዎች ሲገደሉና  ከ67 ሺ በላይ ሲቆስሉ መንግስታቸው ተገቢውን እርምጃ ባላመውሰዱ ነቅፈዋል።

የተኩስ ማቆም ዲፕሎማሲው መክሸፍ 

ይሁን እንጂ እስራኤል እስካሁን ከየትኛውም አቅጣጫ የሚመጣውን የሰላምና የተኩስ ማቆም ጥያቄ ለመቀበል ፈቃደኛ መሆን አልቻለችም። የዋና ደጋፊዋ አሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የሰብዓዊ ተኩስ አቁም ስምምነት ተደርጎ ከፉኛ የተችገሩ፤ የቆሰሉና የታመሙ ሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርሳቸው፤ የታገቱ እስራኤላውያንም እንዲለቀቁና ለዘላቂ ሰላምም የፖለቲካ ምህዳር እንዲፈጠር ለማድረግ ያደርጉት ተደጋጋሚ ጥረት ሳይሳክላቸው እንደተመለሱ ነው የሚታወቀው። 

የጋዛ ጦርነት ራፋ
እስራኤል በራፋ ያቀደችው ወታደራዊ ዘመቻ የቅርብ አጋሮቿ የሆኑት አሜሪካ እና ጀርመንን ጨምሮ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ሥጋት ፈጥሯል። ምስል SAID KHATIB/AFP

ሀማስ ቀርቦለት ለነበረው የሰላም ሀሳብ የበኩሉን በሶስት ምእራፍ የሚተገበር የ90 ቀናት የተኩስ ማቆም ሀሳብ አቅርቦ የነበር ቢሆንም ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ማዘናጊያ በማለት ውድቅ ማድረጋቸው ታውቋል።  ኔታንያሁ ታጋቾች ሊለቀቁ የሚችሉት ከወዳጅ ጠላት በሚቀርበው የሰላም ሀሳብ ሳይሆን፤ በወታደራዊ ድል መሆኑን በመግለጽ ጦርነቱን እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል። “ለአጠቃላይ ድል ተቃርበናል። የድሉ ቀን ደርሷል፤ በአመታት ሳይሆን በወራት የሚቆጠሩ ቀኖች ናቸው የቀሩት” በማለት ለአጠቃላይ ወታደራዊ ድል የመጨረሻ የሀማስ ምሽግ ነው ባሉት የራፋህ ከተማ ዘመቻው የሚቀጥል መሆኑን በይፋ የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንከን እዚያው እንዳሉና አካባቢውን ሳይለቁ አስታውቀዋል።

ደቡብ አፍሪካ በእስራኤል ላይ የመሰረተችው ክስ

ይህ ኔታንያሁ አቋምና ደፋር እርምጃ ግን ከወዳጅ አሜሪካ ጋር ሳያቃቅራት እንዳልቀረ ነው የፖለቲካ ተንታኞች የሚናገሩት። አሜሪካ ለእስራኤል ሁነኛ አጋር እና የጦር መሳሪያ አቅራቢ፤ ባለማቀፉ መድረክ ደግሞ ቋሚ ጠበቃ ብትሆንም፤ አሁን ግን ልዩነቶች በግልጽ እየታዩ ነው እየተባለ ነው።  በጋዛ የደረሰው የውድመት መጠን እና የተገደሉ ሰላማዊ ሰዎች መጠን ማሻቀቡ ለአሜሪካ የውጭ ገጽታም ሆነ ለውስጥ ፖለቲካዋ በተለይም በምርጫ ዘመቻ ላይ ላሉት ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጥሩ እንዳልሆነ እየተገለጸ ነው። ጠቅላይ ሚኒስተር ኔታንያሁ ለምክክር ወደ እስራኤል ያቀኑት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ወዳገራቸው  ሳይመለሱ እንኳ የቀረበውን የሰላም ሀሳብ ውድቅ አድርገው ለሌላ ዙር ጦርነት እየተዘጋጁ መሆናቸው አሜርካንን ማስከፋቱ ግልጽ ሁኗል። ፕሬዝዳንት ባይደን እራሳቸው የእስራኤል እርምጃ ከመጠን በላይ ሆኗል ሲሉ መናገራቸውን ብዙዎች ለዚህ ማረጋገጫ ያደርጉታል።

የራፋ ዘመቻ እቅድ የፈጠረው ስጋት

እስራኤል በቀጣይ በራፋ እወስደዋለሁ ያለችው ወታደራዊ እርምጃ ግን ሌላ ቀጣይ የሆነ አስከፊ ቀውስ የሚታይበትና አሰቃቂ ድርጊቶች የሚፈጸሙበት እንዳይሆን ብዙዎችን  አስግቷል። የኔታንያሁ መንግስት ዘመቻውን ለመጀመር  በቅድሚያ ሰላማዊ ሰዎችን ከራፋህ ለማስወጣት እቅድ እንዲቀርብለት ማዘዙን አስታውቋል። ጥያቄው ግን ከሁሉም የፍልስጤም ከተሞች እና መንደሮች ውጡ ተብለው በራፋ የተከማቹት ፍልስጤሞች ከዚህ በኋላስ ውዴት ሊሄዱ ይቻላሉ? የሚለው ነው።

ራፋህ በደቡብ ጋዛ ክግብጽ ድንበር አቅርቢያ የምትገኝ ከ250 ሺሕ ህዝብ በታች የሚኖርባት ከተማ ነበረች። በአሁኑ ወቅት ግን ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ከሌሎች መንደሮች ተፈናቅለው ወደ ራፋ በተጓዙ ፍልስጤማውያን የተጨናነቀች ከተማ ነች። ከተማይቱ ለጋዛ ብቸኛ የእርዳታ መተላለፊያ በርም ነች። 

በጋዛ እና ዩክሬይን ጉዳይ የመከሩት የአዉሮጳ ኅብረት የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች

በእስካሁን የጋዛ እልቂት እና ሰቆቃ ምንም ማድረግ ያልቻለው ወይም ያልፈለገው ዓለም፤ አሁን ግን ሁሉም ማለት በሚቻል ደረጃ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ይህን ዘመቻ እንዳይገፉበት እያሳሰቡ ነው። የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን “ራፋህን በሚመለክት እስራኤል ሀላፊነት አለባት፤ የሰላማዊ ሰዎችን ደህንነት የማረጋገጥ ግዴታ አለባት፤ ማኛውም የሚወሰድ እርምጃ የሰላማዊ ሰዎችን ደህንነት ቅድሚያ መስጠት የኖርበታል” በማለት አስጠንቅቀዋል። የአሜሪካ የደህንነት ምክር ቤት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ  ከአንድ ሚሊዮን በላይ ስደተኞች የያሉባትን የራፋህ ከተማን ሁኔታ ያላገናዘበ ወታደራዊ እርምጃ እልቂት ሊያስከትል ስለሚችል ልንደግፈው አንችልም ሲሉ ተሰምተዋል። 

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን እና የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ
በሐማስ እና በእስራኤል መካከል የተኩስ አቁም እንዲደረስ ግፊት ለማድረግ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ያቀኑት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ያለ ውጤት ተመልሰዋል። ምስል Amos Ben-Gershom/dpa/picture alliance

የአውሮፓ ህብረት፤ ብሪታኒያ፣ የአረብ ሊግ፤ እስራኤል በራፋህ ያሉ ተፈናቃዮችን ዳግም እንዳታፈናቅል እና  በዚህች ብቸኛዋ  የሰብዓዊ እርዳታ መግቢያ በር ላይ  ጦርነት በማወጅ  ሌላ ሰብዓዊ  ቀውስ እንዳትፈጥር አሳስበዋል። ሳዑዲ አረቢያ እቅዱን ከማውገዝ አልፋ የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ዕቅዱን እንዲያውግዘው አሳስባለች።

የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ ልክ እንደከዚህ ቀደሙ ይህን የጦርነት ዕቅድም በመቃወም አበክረው ድምጻቸውን አሰምተዋል። “የእስራኤል ጦር በቀጣይ በሺ የሚቆጠሩ ስደተኞች ታጭቀው በሚኖሩባት የራፋ ከተማ ሊዘምት ነው መባሉ የሚያስደንግጥ ነው” በማለት ይህ ከሆነ ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ ሰብዓዊ ቀውስ ሊፈጠር እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

ማሕደረ ዜና፣ የICJ ዉሳኔ፣ የደቡብ አፍሪቃ ድልና የፍትሕ እንዴትነት

የእራኤል ፍልስጤምን ውዝግብ ወደ አካባቢው በመሄድ ጭምር በመዘገብ የምትታወቀው ጋዜጠኛ ሶፊ አማራ በበኩሏ ወደራፋ የሚደረግ ወታደራዊ ዘመቻ እዚያ ላሉት ፍልስጤማውያን የሞት ፍርድ ያህል እንድሆነ ነው የምትናገረው። “ይህ ማለት በፍልስጤማውያን ላይ ከፍተኛ የሞት እና የመቁሰል አደጋ ይደርሳል ማለት ነው። ምክንያቱም የከተማዋ ነዋሪ ባሁኑ ወቅት ስድስት ዕጥፍ ጨምሮ ባለበት ሁኔታ የሚከፈት ጥቃት ከዚህ ቀደም ካየነው የበለጠ ጉዳት ሊያደርስ ስለሚችል ነው” በማለት ስጋቷን ገልጻለች። 

እስራኤል ለሰላም ጥሪው አዎንታዊ መልስ ተሰጥ ወይንስ በጦርነት ዕቅዱ ትገፋ ይሆን?

እስራኤል በተለይም የጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ መንግስት በተለይ በራፋ ያቀደውን ጦርነት ይቀጥልበት ይሆን ወይንስ ከየአቅጣጫውና ከወዳጅ አሜሪካ ጭምር ለቀረበለት የሰላም ምክረ ሀስብ ጆሮውን ይሰጥ ይሆን? የብዙዎች ጥያቄ ነው። አንድንድ የፖለቲካ ታዛቢዎች ከአሜሪካ መንግስት የሚሰማው ከልብ ከሆነና የፕሬዝዳንት ባይደን አስተዳደር በትክክል የእስራኤል አካሄድ እንዲለወጥ ከፈለገ፤ እስራኤል ከአሜሪካ ውጭ አትሆንም በማለት  ኔታንያሁ ሀሳባቸውን ሊቀይሩ ይችላሉ ይላሉ። ዘ ሱፋን ቡድን የተሰኘው በጂኦፖለቲካ ላይ የሚያተኩረው መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ዳይሬክተር ዶክተር ኮሊን ክላርክ የመሳሰሉ “ጦርነቱ የፖለቲካ  ህይወት ማስቀጠያ መሳሪያም ነው” በማለት ኔታንያሁ ሊፈልጉት እንደሚችሉ ይናገራሉ።  “ጦርነቱ ከቆመ በአመራራቸው የተከፋው ከስልጣን ሊያወርዳቸው ይችላል” በማለት ተናግረዋል።

የጋዛ ጦርነት ተፈናቃይ በራፋ
ከግብጽ ድንበር አቅራቢያ የምትገኘው ራፋ የጋዛ ጦርነት የሸሹ ፍልስጤማውያን ማረፊያ ነበረችምስል Said Khatib/AFP/Getty Images

በጋዛ እየደረሰ ያለው እልቂት እና ውድመት ከዚህ በላይ እንዳይሄድ እየተሰማ ካለው ድምጽ እና እየተደረገ ካለው ጥረት ባሻገር ግን ግን ለዚህ በርካታ አስርት አመታትን  ላስቆጠረው የእስራኤል ፍልስጤም ችግር ዘላቂ መፍትሔ  ጉዳይ ብዙም እየተባለ አይደለም። የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በቅርቡ በዚህ ጉዳይ የሰጡት አስተያየት ግን የችግሩን ምንጭና ዘላቂ መፍትሄዎቹንም የሚጠቁም ነው።

“ይህ ሁሉ ሰብዓዊ ቀውስ እና ችግር እየደረሰ ያለው  ለበርካታ አስርት እመታት ለእስራኤልና ፍልስጤም ችግር ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የተደረጉ ጥረቶች ባለመሳካታቸው ነው። ለእስራኤል የደህንነት ዋስትና የሚሰጥና ህልውናዋን የሚያረጋግጥ፤ ለፍልስጤሞች ደግሞ ከአገዛዝ ነጻ የሆነች እና ፍልስጤሞች የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የሚወስኑበት የፍልስጤም ግዛት መመስረት” ሲሉ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ተናግረዋል።

ገበያው ንጉሴ

እሸቴ በቀለ