ትግራይ ክልል ከ5 ሺህ በላይ የቀድሞ ተዋጊዎች ወደመደበኛ ሕይወት መመለሳቸው
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 14 2017
በፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት መሠረት በቅርቡ መተግበር የተጀመረው በትግራይ ያሉ የቀድሞ ተዋጊዎች ወደተሃድሶ ተቋማት በማስገባት ስልጠናና የፋይናንስ ድጋፍ በመስጠት ወደሰላማዊ ሕይወት የመመለስ ተግባር፥ እስካሁን ባለው አፈፃፀም ከአምስት ሺህ በላይ የቀድሞ ታጣቂዎች ስልጠና ወስደው ወደ ኅብረተሰቡ መመለሳቸውን በብሔራዊ የተሃድሶ ኮምሽን በኩል ተገልጿል። በአራት ወራት ግዜ ውስጥ 75 ሺህ የቀድሞ ታጣቂዎች ወደ ሰላማዊ ሕይወት ለመመለስ መታቀዱን አስቀድሞ ገልጾ የነበረው ኮምሽኑ፥ ይህን የሚፈፀምባቸው ማዕካላት በመቐለ ጨምሮ በሌሎች የትግራይ አካባቢዎች ተቋቁመዋል።
የተሃድሶ ስልጠና ከወሰዱት የቀድሞ ተዋጊዎች እንደተሰማው፥ ከስልጠናው በኋላ 90 ሺህ ብር ገደማ እየተሰጣቸው ከተሃድሶ ማዕከላቱ ይሰናበታሉ። በርካቶች የቀድሞ የትግራይ ኃይል አባላትም ይህንኑ ይጠብቃሉ። በ2013 ዓ.ም. የትግራይ ሐይሎችን የተቀላቀለው የማነ ሕሸ፤ በብሔራዊ ተሃድሶ ኮምሽን በኩል ከሚሰጥ ስልጠና እና ማቋቋሚያ በኅላ ወደ ሰላማዊ ሕይወት ለመመለስ እየጠበቁ ካሉ የቀድሞ የትግራይ ሐይሎች አባላት መካከል ነው። የማነ እንደሚለው አስቀድሞ ወደ ተሃድሶ ማዕከላት ለገቡ የተሰጠው ማቋቋሚያ ብር አነስተኛ እንኳን ቢሆን፥ በስርዓቱ መሠረት ከሠራዊት ተሰናብቶ ወደ ሰላማዊ ሕይወት ለመግባት እርሱን ጨምሮ የበርካቶች ፍላጎት መሆኑ ያነሳል።
በተሃድሶ ማዕከላት ስለሚሰጠው ስልጠና እና የሚሰጠው ማቋቋሚያ ጉዳይ ከብሔራዊ ተሃድሶ ኮምሽን መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት፥ ኮምሽኑ በቀጣይ ቀናት ዝርዝር ማብራሪያ እንደሚሰጥ ጠቅሶ ለጊዜው አልተሳካልንም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የተጀመረው የቀድሞ ተዋጊዎች ወደ ሰላማዊ ሕይወት የመመለስ ሥራ በህወሓት በኩልም ቅሬታዎች እየተነሱበት ነው። የከፍተኛ አመራሮች፣ የወጣቶችና የሴቶች አደረጃጀት በሚል የተለያዩ የካድሬዎች ስብሰባ እያደረገ ያለው በዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል የሚመራው የህወሓት ቡድን፥ ሂደት ላይ ያለው የቀድሞ የትግራይ ተዋጊዎች ትጥቅ በማስፈታት እና ስልጠና በመስጠት ወደ ሰላማዊ ሕይወት የመመለስ ሥራ በእንግሊዝኛው ምህጻር DDR ላይ ያለው ተቃውሞ ገልጿል። በህወሓት ቡድኑ የከፍተኛ ካድሬዎች ስብሰባ ማገባደጃ የአቋም መግለጫ ያወጣው ፖርቲው የትግራይ ፍላጎቶች ባልተመለሱበት ሁኔታ፥ በDDR ስም ሠራዊታችን እየፈረሰ ነው ብሏል።
የህወሓት ቡድኑ «መሠረታዊ የትግራይ ፍላጎቶች ባልተመለሱበት ሁኔታ ላይ እያለን፥ የጥፋት ቡድኑ በDDR እና ሌሎች መንገዶች ሠራዊታችን ሆን ተብሎ እንዲበተን ተወስኖለታል። ስለሆነም የሠራዊታችን ህልውና ከፕሪቶርያው ስምምነት ሙሉ ትግበራ ጋር የሚያያዝ ስለሆነ ይህ የመመከት አቅም በተለያዩ መንገዶች ለመበተን እና ለማዳከም እየተደረጉ ያሉ የስም ማጥፋት ዘመቻዎች እና የተግባር እንቅስቃሴዎች በጥብቅ እንኮንናለን፥ ሁሉን አቀፍ ሰላማዊ ፖለቲካዊ ትግል እንደምናደርግም እናረጋግጣለን» ብሏል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የቀድሞ ተዋጊዎች ወደሰላማዊ ሕይወት የመመለስ ተግባሩ በውሉ መሠረት እየተፈፀመ ያለ እና በዶክተር ደብረፅዮን ቡድኑ ህወሓት እንደሚባለውም ስጋት የማይፈጥር ነው ብሎት ነበር።
ሚሊየን ኃይለ ሥላሴ
ሸዋዬ ለገሠ
ኂሩት መለሰ